ኢትዮጵያን አትንኩ የምንለው ለዚህ ነው
አሁንም አይንኩን፤ እግራቸውን ከግዛታችን፣ እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ ያንሱ!
ኢትዮጵያን መንካት ዋጋ የሚያስከፍል መኾኑን ማሳየት ተገቢ ነው
ኢትዮጵያ ዛሬ (ርዕሰ አንቀጽ) - የሱዳን አፈንጋጭ የጦር መኮንኖች በግብጽ ተገፋፍተው ወታደሮቻቸው የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው ከገቡ ሳምንታት ብቻ ሳይኾን፤ ወራት እየተቆጠሩ ነው። ኢትዮጵያ ፍጹም ለኾነው የሱዳን ስሕተት ትዕግሥትን በማስቀደም ነገሩን ከጦርነት መለስ ባለ ሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ይሻላል በማለት በዚሁ አኳያ እየተንቀሳቀሰች ነው። ይህም ቢኾን ግን ከሱዳን ቀና ምላሽ ባለመገኘቱ የኢትዮጵያን ድንበር የተራመዱቱ የሱዳን ታጣቂዎች ከኢትዮጵያ ግዛት ከመውጣት ይልቅ ቆይታችንን እናራዝማለን በሚል አንዳንድ ግንባታዎችን እስከማካሔድ ደርሰዋል። ይህ ድርጊታቸው ደግሞ ነገሩን ይበልጥ እያከረረው በመኾኑ፤ በአካባቢው ጦርነት ይነሳል የሚል ሥጋት መፍጠሩ አልቀረም።
በአንጻሩ ሱዳን የግብጽ ተላላኪ በመኾን የወሰደችው ይቅር የማይባል ተግባር በዚሁ ከቀጠለ የኢትዮጵያ እርምጃ የበረታ ይኾናል የሚለው እምነት ጠንካራ መኾኑ አይታበልም።
ወደ ጦርነት ቢገባ የበለጠ ዋጋ ከፋይዋ ሱዳን ስለመኾኗ ባያጠያይቅም፤ ሱዳን ግብጽን ተማምናለችና የመጣው ይምጣ ማለቷ የት ድረስ እንደሚወስዳት ለማወቅ ይቸግራታል ተብሎ አይታሰብም። ምክንያቱም እርምጃዋ አደገኛ መኾኑ በግልጽ ይታወቃል።
ነገሩን ከኢትዮጵያ ታሪክና ካለው እውነታ አንጻር ስንመለከተው፤ “ኢትዮጵያን የነካ …” እንድንል ያደርገናል። የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግሮ የሚገኘው የሱዳን ጦር ወደነበረበት እንዲመለስ በቀጣይ ከኢትዮጵያ ወገን የሚሰጠው ምላሽ እንደተጠበቀ ኾኖ፤ ሱዳን እየገጠማት ያለው ቀውስ እንደማሳያ ነው። ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ በገባች ማግስት በአገር ውስጥ ጉዳይዋ ስትጠበስ መሰንበቷ፤ ኢትዮጵያን የነካ የእጁን ማግኘቱ አይቀርም የሚለውን እውነት የበለጠ ያረጋገጠ ነው።
ሱዳን በውስጥ ችግሯ በየዕለቱ የሚደመጡት ግጭቶችና ተቃውሞዎች፤ የሱዳን ጄኔራሎች በኢትዮጵያ ላይ የወሰዱት እርምጃ አግባብ ያለመኾኑን ማሳያ ነው ሊባል ይችላል።
የተለኮሰውም እሳት ከዚህም በላይ ዋጋ ሊያስከፍላቸው ይችላል። አሁን ደግሞ እየተሰማ እንዳለው የግብጽን አጀንዳ ለማስፈጸም ቆርጠው ተነስተው የነበሩት የሱዳን ጄኔራሎች ኢትዮጵያን መንካት ምን ያህል አደገኛ መኾኑን ማሳያ የሚኾን ነገር ተፈጥሯል።
ይህም ሱዳንን ከጀርባ ግፋ በለው ስትል የነበረችው ግብጽ ምክንያቱን ፈጣሪ ይወቅና መለስ ብላ ሱዳን ላይ ዞራለች።
ወትሮም ሐቅን ስቶ የሚፈጸም ድርጊት ይቆይ እንጂ ዋጋ ማስከፈሉ የማይቀር በመኾኑ ኢትዮጵያ ቃታ ሳትስብ በሆደ ሰፊነት የዘለቀችበት ትዕግሥቷ ላኪና ተላኪን ወደማናቆር እየገባ ነው።
በግብጽና በሱዳን መካከል የተጫረው እሳት የምር ይሁን አይሁን በኋላ የሚለይ ቢኾንም የሱዳን ጄኔራሎች ግብጽ ላይ ከንፈር ነክሰው በቃላት መውቀጥ ይዘዋል።
ሁለቱን አገሮች ዓይንና ናጫ ያደረጋቸው ሰሞናዊ ጉዳይ ግብጽና ሱዳን የይገባኛል ጥያቄ የሚያቀርቡባቸው ኃይላትና በሸላቲን የተባሉ ግዛቶችን ግብጽ ጠቅላላ ለመውሰድ ያላት ፍላጎት ማሳየትዋ ነው።
ግብጽ በእነዚህ ይገባኛል ጥያቄዎች የሚነሳባቸውን ግዛቶች የያዘ አዲስ ካርታ አዘጋጅታ የአፍሪካ ሕብረት ያጸድቅላት ዘንድ ግብጽ ማመልከቷ፤ የአገራቱ መነታርኪያና ጣት መቀሳሰሪያ ኾኖ እንደአዲስ ብቅ ብሏል። ይህ ሰሞናዊ የግብጽ እንቅስቃሴ ደግሞ ለሱዳን የተመቸ አይደለም። ያለመመቻቸት ብቻ ሳይኾን፤ ሱዳንም በፊናዋ ግዛቶቹ የእኔ ናቸው በማለት አደባባይ ወጥታለች። እንዲያውም አንድ የሱዳን ቱባ ጄኔራል ብቅ ብለው ከእነዚህ ግዛቶች አንድ ኢንች መሬት አንሰጥም በማለት እስከመናገር መድረሳቸው የጉዳዩን ግለት ያሳያል።
ይህ ጉዳይ በአገራቱ መካከል ንፋስ መግባቱን ከማመልከቱም በላይ፤ ኢትዮጵያን ለመጫን ያሳዩትን ትብብር እንዳይገፉ ያደርጋል የሚል እምነት አሳድሯል። ወትሮም ትብብሩ ኢትዮጵያን ለመጫን ነበር። ኾኖም ሁለቱን አገራት እርስ በእርስ የሚያናክስ ነገር መምጣቱ፤ አሁንም ኢትዮጵያን የነካ ፈጣሪ ዝም አይለው የሚለውን እምነት ያጠናክራል።
ለዚህም ነው አሁንም ኢትዮጵያን የነካ የእጁን ማግኘቱ አይቀርም የምንለው። አሁንም አይንኩን፤ እግራቸውን ከግዛታችን፣ እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ ያንሱ! የኢትዮጵያ መንግሥትም ነገሩን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያደርገው ጥረት እንደተጠበቀ ኾኖ፤ በእብሪት የተደፈረውን ድንበር የሚያስከብርበትን መላ ከማሰብ መቆጠብ የለበትም። የሱዳንና የኢትዮጵያ ሕዝብ ወዳጅነት ግን ይቀጥል። ኢትዮጵያን መንካት ዋጋ የሚያስከፍል መኾኑን ግን መጨረሻ ላይ ማሳየት ተገቢ ነው።
- ኢትዮጵያ ዛሬ



