በምርጫ ብቻ

“በምርጫ ብቻ!”

በሠለጠነ መንገድ ተወዳዳሪም፣ መራጭም፣ ታዛቢም፣ ደጋፊም እንሁን!

ኢትዮጵያ ዛሬ (ርዕሰ አንቀጽ) - የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ (ምርጫ 2013) ቦርድ የዘንድሮውን አገራዊ ምርጫ በተያዘለት ጊዜ ለማከናወን የሚያስችሉ ሥራዎችን እየሠራ ነው። እያጋጠሙት ያሉትን ችግሮች እያሳወቀና የመፍትሔ አቅጣጫ እያስቀመጠ እየተጓዘ መኾኑንም ቦርዱ በተከታታይ ከሚያወጣቸው መግለጫዎች ለመገንዘብ ይቻላል። ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ባይኾንም ምርጫውን ለማካሔድ ጥረቱን ቀጥሏል።

በአንዳንድ ወገኖች እየገጠመኝ ነው ያለው የትብብር ጉድለት ግን በቶሎ መታረም ያለበት ነው። በሌላ በኩል ግን ሚዛናዊ ውሳኔዎችን በመስጠት ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሔድ ያለውን ቁርጠኝነት በተለያየ መንገድ እየገለጸ መኾኑንም እያሳየ ነው።

በምርጫው የሚሳተፉ ፓርቲዎች በምርጫው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ወደ ምርጫ ቅስቀሳ ሙግታቸውን ይፋ እያደረጉ በመኾኑም፤ ምርጫው በሰላማዊ መንገድ ሊካሔድ እንደሚችል እምነት እያሳደረ ነው።

ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ከዚህ ቀደሞቹ “ምርጫዎች” በተለየ ይካሔዳል የሚለው አመለካከት የብዙዎቹ የባለድርሻ አካላት አመለካከት እየኾነ መምጣቱ ተስፋ ሰጪ ነው። ሁሉም የተሻለ ምርጫ እንሻለን እያሉም ነው፤ መኾንም ያለበት ይህ ነው።

ለዚህ ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የየራሳቸው ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆን፤ ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ይኾን ዘንድ፤ እንዲሁም ከቀደሙት ምርጫዎች የተሻለ እንዲኾን ከተፈለገም ሕግና ሥርዓትን ማክበር ግድ ይላል። ይህ ደግሞ ለተወሰኑ ወገኖች የሚተው አይደለም።

ከቀድሞ የተሻለ ምርጫ ይኑረን ከተባለ፤ ሁሉም ወገን ከቀድሞው በተሻለ አመለካከትና አካሔድ መጓዝ ይኖርባቸዋል ማለት ነው። ምርጫው ተአማኒነት ያለው እንዲኾን የምርጫ ቦርድ ብቻ ኃላፊነት አይደለም። ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሚፈለግ ከኾነ፤ ሁሉም ተወዳዳሪ ፓርቲዎች የውድድር መንፈስ ፍጹም ሰላማዊ በኾነ መንገድ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል።

ከቀደመው ጊዜ የተሻለ ምርጫ ያስፈልገናል ብለን ከተነሳን፤ ከዚህ ቀደም ይደረግ እንደነበር አጉራ ዘለል ከኾኑ ንግግሮች ተቆጥበን፣ አማራጭ ፖሊሲዎችን በማቅረብ ጥሩ ተወዳዳሪ ኾኖ መቅረብ ምርጫውን የተሻለ ያደርጋል።

ከመንግሥት አንጻር እንደ ቀድሞ ጡንቻ አለኝ ብሎ ሌሎችን ለመጫን ከመሞከር ተቆጥቦ በሕግና በሥርዓት ምርጫው እንዲካሔድ ቁርጠኛ መኾን ይገባል። ፍትሐዊ ምርጫ እንዲካሔድ እፈልጋለሁ ያለውን ቃል በተግባር ማሳየት አለበት።

ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በሚረባው በማይረባው ጉዳይ መንግሥትን በመክሰስ ብቻ ምርጫን ማሸነፍ እንደማይቻል መገንዘብ አለባቸው። በምርጫ ሒደት ከምርጫው ጋር የተያያዙ ችግሮችን በምክክር ለመፍታት መሞከር፤ ይህ አልኾነም ከተባለ ሕግን ተከትሎ መጠየቅና ፍትሕ ለማግኘት እንችላለን ብሎ ራስን መግዛት ከተቻለ፤ የተሻለ ምርጫ የማየት እድላችን ሰፊ ነው።

በሠለጠነ መንገድ ተወዳዳሪም፣ መራጭም፣ ታዛቢም፣ ደጋፊም እንሁን። ይቺን አገር የተሻለ ለማድረግ በአመጽና በጉልበት ከመንቀሳቀስ ተቆጥቦ፤ ነገራችን ሁሉ በምርጫ ብቻ ይሁን! አዎ! በምርጫ ካርድ ብቻ ይሁን!ኢትዮጵያ ዛሬ

የተፎካካሪ ፓርቲ ደጋፊዎችም ለዚህ ምርጫ የተሻለ መኾን ከፍተኛ ኃላፊነት አለባቸው። ድጋፍና ተቃውሞዋቸው ምክንያታዊ መኾን እንዳለበት በማመን፤ ጨዋ ደጋፊዎች በመኾን፤ በጋራ ታሪክ መሥራት እንደሚቻል በማመን፤ ለምርጫው ስኬት መትጋት አለባቸው።

በተለያየ መንገድ ምርጫውን ለመታዘብም ኾነ፤ በምርጫው የሚሳተፉም፣ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ዜጐች መብትና ግዴታዎቻቸውን እንዲያውቁ በማንቃት ኃላፊነት ያለበቸው የሲቪክ ማኅበራትም እንቅስቃሴያቸውን በታማኝነት እንዲከውኑ ሁኔታዎች ሊመቻችላቸው ይገባል።

የሲቪክ ማኅበራቱ ዋነኛ ኃላፊነት ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሔድ፤ ዜጐች መብትና ግዴታቸውን እንዲወጡ፤ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግና ሥርዓትን ተከትለው እንዲንቀሳቀሱ ማስተማር ነውና፤ በዚሁ አግባብ ተግባራቸው ተፈጻሚ የሚኾን ከኾነ፤ የተሻለ ምርጫ ሊካሔድ ይችላል።

የጸጥታና በአጠቃላይ የፍትሕ አካላትም፤ ሰላምና ጸጥታውን በመጠበቅ ረገድ የበኩላቸውን መወጣት ከቻሉ የሚፈለገውና ብዙዎች ሊስማሙበት የሚችል ምርጫ አካሒዶ፤ አገር ስትታመስበት የቆየችውን የፖለቲካ አረም መንቀል የሚቻልበት እድል ሊፈጠር ይችላል። የተረጋጋ አገር እንዲኖረንም ያስችላል።

የሚዲያ ተቋማት ሚዛናዊ ዘገባም ለዚህ ምርጫ ስኬት ጉልህ ድርሻ አለውና፤ ሁሉንም በኩል በማየት ዘገባቸውን ለሕዝብ እንዲያቀርቡ ማገዝ ያሻል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ ያስፈልጋል። የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችም በምርጫው ሒደት ላይ የሚፈጸሙ አፈንጋጭ ተግባራትን በማጋለጥ እርምት እንዲወሰድበት በማድረግ፤ ኢትዮጵያ የተሻለ ምርጫ ማድረግ አለማድረጓን በአግባቡ በማንጠር መግለጽ ይኖርበታል።

በአጠቃላይ ስለቀጣዩ ምርጫ ካሰብን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአመለካከትም ኾነ በተግባር ተሽለው መገኘት ይጠበቅባቸዋል። ሕዝቡ ያሻውን እንዲመርጥ እና የተሻለ አገር ለመፍጠር፤ በትክክለኛ ምርጫ አገር አስተዳዳሪዎችን ለመምረጥ ቁልፉ ጉዳይ ሁሉም ተባብሮና ተግባብቶ መሥራት ነው። የምርጫው ሌላው ወሳኝ ጉዳይ ደግሞ ፓርቲዎች መፎካከሪያቸውን በዝርጠጣና በስድብ በመግለጽ ሳይኾን፤ ሲያሸንፉ አገር የሚያስተዳድሩበትን ፖሊሲ ማቅረብ ብቻ ሊኾን ይገባል።

ዜጐችም ሲመርጡ በመወዳደሪያ ፖሊሲዎቻቸው ምዘና የመምረጥ መብታቸውን መጠቀም አለባቸው። ተራ የቃላት ውርወራና ብሽሽቅ መወዳደሪያ አይኾንም። የተሻለ ምርጫ ከተፈለገ በሁሉም ወገን ተሽሎ መገኘትን ይጠይቃልና ለዚህ ሁሉም መተባበር ግድ ይለዋል። ሁሉም የየራሱን ኃላፊነት ባለው የኃላፊነት ልክ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል። ኃላፊነቱን ካልተወጣ ግን፤ አሁንም የተሻለ ምርጫ ላይመጣ ይችላል። በዚህ ሰዓት የአገሪቱን የወደፊት ጉዞ ይወስናል ተብለው ከሚጠበቁት አማራጮች አንዱ ምርጫ ቀዳሚው ነውና፤ ለምርጫው ስኬት ሁሉም የበኩሉን ያድርግ። ይህን አጋጣሚ እንደ መልካም መጠቀምም ያስፈልጋል። ለምርጫው ስኬት በብዙ እየደከመ ያለው ምርጫ ቦርድ “በምርጫ ብቻ” የሚለውን መሪ ቃሉን ሁሉም ይተግብረው።

በሠለጠነ መንገድ ተወዳዳሪም፣ መራጭም፣ ታዛቢም፣ ደጋፊም እንሁን። ይቺን አገር የተሻለ ለማድረግ በአመጽና በጉልበት ከመንቀሳቀስ ተቆጥቦ፤ ነገራችን ሁሉ በምርጫ ብቻ ይሁን! አዎ! በምርጫ ካርድ ብቻ ይሁን! (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ