አቶ አንዷለም አራጌ “ቪዛ’ ተከለከለ
Ethiopia Zare (ረቡዕ መጋቢት 15 ቀን 2002 ዓ.ም. March 24, 2010)፦ የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ አቶ አንዷለም አራጌ “ጠንካራ ህዝባዊ ድጋፍ ሊያገኝ ይችላል” ከሚባሉት ፓርቲዎች አንዱ የሆነውን መድረክን በመወከል በቅርቡ ከአዲስ አበባ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ያቀናል የተባለው የልዑካን ቡድን አባል ሆነው ቢመረጡም፤ የመውጫ ፈቃድ (ቪዛ) መከልከሉ ተገለጸ።
የልዑካን ቡድኑ አባላት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፣ አቶ ገብሩ አሥራት፣ አቶ ስየ አብርሃ፣ ኢንጂንየር ግዛቸው ሽፈራው፣ አሁን በአሜሪካ የሚገኙት ዶ/ር መራራ ጉዲና እና “የጉዞ ፈቃድ ተከለከለ” መባሉ መጋቢት 14 ቀን 2002 ዓ.ም. ምሽት ላይ የተሰማው አቶ አንዷለም አራጌ ናቸው።
ወጣቱ የፖለቲካ ሰው አቶ አንዷለም ፈቃድ የተከለከለበትን ምክንያት ፓርቲው ለዜና ምንጮች ባያብራራም፤ ከኢትዮጵያ የስደተኞችና የዜግነት ጉዳይ መ/ቤት (ኢሚግሬሽን) በኩል ቢሮክራሲያዊ ችግር የገጠመው መሆኑን ተገልጿል።
የ2002 ዓ.ም. ምርጫን ቅድመ ዝግጅት በተመለከተ ከኢህአዲግ ሰዎች እና ከህዝብ ጋር መድረክ በሚያደርገው ወይይት አቶ አንዷለም አራጌ ቆንጣጭና ጠንካራ የሚባሉ ሃሳቦችን በመወርወር በኩል ዓይን ውስጥ የገቡ መሆኑን የገለጹት ምንጮች፤ የተቀሩት የልዑካን ቡድኖች ዝግጅታቸውን እንዳጠናቀቁ ጠቁመዋል።