የሁለት ኢትዮጵያውያን ሁለት አንቀጽ ወግ እና እኔ
አቤ ቶኪቻው
ዳዊት ከበደ እና ተስፋሁን ጫመዳ
ተስፋሁን ጫመዳ የተባለ አንድ ወጣት ኢትዮጵያዊ ነበር። የገዢው ግንባር ኢህአዴግ ነገረ ሥራ አልመችህ ቢለው በተለያየ አጋጣሚ "ተው!" ማለት ጀመረ። ኢህአዴግዬ ግን ተው ባይ አይወድምና በክፉ ዓይኑ ተመለከተው። ይሄኔ ተስፋሁን የሚመጣበትን ጦስ ሸሽቶ መጪው ጊዜ መልካም እንደሚሆን ተስፋ አድርጎ 'እስኪያልፍ ያለፋል' ብሎ ሀገሩን ትቶ ተሰደደ።
ኢህአዴግ ግን ዝም አላለውም ከተሰደደበት ሀገር አፍኖ ወደ ሀገር ቤት መለሰው። መመለስ ብቻም አይደለም እስር ቤት ዶለው። መዶል ብቻም አይደለም በቅርቡ ተስፋሁን በእስር ቤት በቂ ሕክምና አጥቶ ሕይወቱን ተነጠቀ።
ዳዊት ከበደ የተባለ ሌላ ኢትዮጵያዊ ወጣት ነበር። እርሱም የገዢው ግንባር ኢህአዴግ ነገረ ሥራ አልጣመውም እና መምከር ጀመረ። ኢህአዴግዬ ግን በሚመክሩት ላይ መከራ የሚያበዛ ነውና በክፉ ዓይኑ ተመለከተው። ይሄኔ ዳዊት ከጎልያድ ጋር ይጋፈጥበት ወንጭፍ በእጁ አልነበረምና ቀን እስኪልፍ ብሎ ሀገሩን ትቶ ተሰደደ። ኋላ ላይ ግን እንደ ተስፋሁን አፍነው ሳይወስዱትም ራሱ "እንደውም አልፈራችሁም!" ብሎ ወደ ሀገር ቤት ተመለሰ።
"ይገሉኝም እንደሁ
ይሰቅሉኝም እንደሁ
ይሄው መጣሁልዎ
ያለምጣም ኢህአዴግ ብዬ ሰደብኩዎ" ብሎ ሁሉ ልክ ልካቸውን ነገሯቸዋል ነው የሚባለው ... ነገር ግን እንደ ተስፋሁን እስር አልጠበቀውም። እንኳንስ ሕይወቱን ሻንጣውም አደጋ ላይ አልወደቀም።
ሦስተኛ አንቀጽ እኔ
"አውቶብሱ መጣ ጎማው ሸተተኝ
እኔም ከሰሞኑ ተሳፋሪ ነኝ" ብዬ ዥው ብዬ ወደ ሀገሬ ብሄድ የሚጠብቀኝ ምን ይሆን? ... እንደ ተስፋሁን ታስሮ ሕይወት ማጣት፣ እንደ ውብሸት ታስሮ ይቅርታ ማጣት፣ እንደ ርዕዮት ታስሮ ጠያቂ ማጣት፣ እንደ እስክንድር ታስሮ ቤተሰብ ማጣት ወይስ እንደ ዳዊት ታስሮ አሳሪ ማጣት!? (በቅንፍም፣ የሆነውስ ሆኖ ግን ስንት ዓመት ሰው ሀገር እቆያለሁ? የሆነ ቀንማ ሄጄ መቀወጤ አይቀርም። (በሌላ ቅንፍም፣ ደግሞ ሳላግጥ፤ ቢያንስ ግን ለጨዋታም ለቃለ ምልልስም እንዲመች የባቡር ግንባታው እንኳ ይለቅና እንተያያለን ...!))



