ከሳሽ አቶ አየለ ጫሚሶ ናቸው

Ethiopia Zare (ዓርብ ሚያዝያ 3 ቀን 2000 ዓ.ም. April 11, 2008) ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማሪያምና ጋዜጠኛ ዳዊት ከበደ በአውራምባው ጋዜጣ የካቲት 25 ቀን 2000 ዓ.ም. ቁጥር አንድ ዕትም ላይ ባካሄዱት ቃለምልልስ፤ ዶ/ር ያዕቆብ ቅንጅት አግብብ ባልሆነ መልኩ ለመንገደኛ ተሰጠ ሲሉ በሕጋዊ መንገድ የተሰጠንን ፓርቲ አናንቀዋል ሲሉ አቶ አየለ ጫሚሶ ለፍርድ ቤት ክስ ማቅረባቸውን ዛሬ ከአዲስ አበባ የደረሰና ዘገባ አስረዳ።

 

አቶ አየለ ሕጋዊ መብታችን ተነክቷል ሲሉ በጠያቂው ጋዜጠኛና በዶ/ር ያዕቆብ ላይ ክስ ከመመስረታቸው ቀደም ሲል ማናቸውም ግለሰብ ወይንም ቡድን ቅንጅትን በሚመለከት ለመናገርም ሆነ ማናቸውንም አስተያየት ለመስጠት መብት የለውም ይህንን ሲያደርግ ባገኘነው ላይ አስፈላጊውን እርምጃ እንወስዳለን በማለት ሲዝቱና ሲያስፈራሩ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው።

 

አቶ አየለ መቀመጫውን ቦሌ አካባቢ ባደረገና ቅንጅትን ከህዝቡ ልብ ለማውጣት ከፍተኛ ተልዕኮ በተሰጠው የኢህአዴግ ካድሬ እየታዘዙ የሚሰሩ መሆኑን ባደረግነው ክትትል የደረስንበት ሲሆን፣ ግለሰቡ ጉዳዩን በሚያውቁ ሰዎች 'የአየለ ጫሚሶ ጠርናፊ' በመባል ይታወቃል። የአቶ አየለን ቡድን ፈጣሪ፣ አቅጣጫ ጠቋሚና መግለጫዎችንም ጭምር የሚያዘጋጅላቸውና ለዚህ ተግባር (ሚሽን) ብቻ ገንዘብ የተመደበለት መሆኑን ለማወቅ ችለናል።

 

"በቅንነት በኅብረተሰቡ ልብ ውስጥ የገባን ፓርቲ በቀላሉ መንቀል ከቶ የማይቻል ነው ..." የሚሉ አንድ የፓለቲካ ጠበብት እንደሚሉት "... ህዝብ ዝም አለ ማለት ቅንጅት የአቶ አየለ ነው ብሎ አመነ ማለት እንዳልሆነና ወያኔ/ኢህአዴግ የሚፈጽማቸውን ደባና ተንኮል አያውቅም ማለት እንዳልሆነ መታወቅ ይገባዋል" ሲሉ በአጽንኦት ገልፀዋል።

 

አክለውም "... በእንደነ አየለ ጫሚሶ ባሉ ግለሰቦች ህዝብን ማምታታት የማይቻልና አገዛዙም ባሳለፋቸው የአስራ ሰባት የአገዛዝ ዓመታት የተከናወኑትና የህዝብ ዝምታ ውጤቶች ማገናዘብ ያልቻለ ነው" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!