ኔልሰን ማንዴላ Nelson Mandelaመራራ ስንብት - ከመብራታችን ጋር ...
ሥርጉተ ሥላሴ

በዘመነ ወያኔ የተከበሩ ማንዴላ የተስፋዬ ሀገር የሚሏትን ሀገርና ህዝብ፤ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵውያንን ሳያዩ አረፉ። ስለ ምን? ለጥቁሮች የተፈሪነት ፍጹም ልዩ ዓርማ የሆነችውን የሀገራችንን ቀደምትነት፤ ያን የአፍሪካዊ የጥቁር ገድል፤ የቅኝ ግዛትን ቀንበር በምኞት ያስቀረ የፈካ ታሪክ በዕብሪትና በበቀል የጣሰው የወያኔ ሓርነት ትግራይ ማንፌስቶ አልተመቻቸውም ነበርና።

 

የፍቅር አባት የሆኑት የተከበሩ ኔልሰን ማንዴላ የወያኔ ድርጅት የወሰደውን ኢትዮጵያዊነትን የማፍረስ ዘመቻ ጠንቅቀው ያወቁ፤ የተገነዘቡ ስለነበር እየተቃጠሉ አምቀውና መስጥረው በመያዝ ለወያኔ ማንፌስቶ ፊት ሳይሰጡት፤ ጀርባቸውን እንደሰጡት ላይመለሱ አለፉ።

ለማየት አብዝተው የሚናፍቋት፤ የሚጓጉላት፤ የሚሳሱላት ሀገር ኢትዮጵያ ሆና፤ ግን ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድነቷን አጥታ፤ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ እንብርት የነበሩት ተቋማት ሁሉ በጠላትነት ተፈርጀው ሲፈርሱ፤ ሲናዱ፤ ዋጋ ሲያጡ እያዩና እየሰሙ ናፍቆታቸው ፈርሳ ከማየት እንደናፈቀቻቸው ማሸለብ ነበር ምርጫቸውና ፀፀታቸውን ይኸው በቃል ኪዳናቸው አጸንተው ቋሚ ዓምድ አደረጉት - ልዩ ባለውለታችን። በቀጥታም ኢትዮጵያዊነትን ለማሰንበት ሆነ ለማቆየት ያቀረቡት ጥያቄ ነበር። ምላሹ ሬት - ኮሶ ነበረና ውስጣቸው አምርሮ እንደ አዘነ፤ እንደ ተከዘ ለኢትዮጵያዊነት ሰግደው እንደ ተርመጠመጡ መራራ ስንብት እንሆ ሆነ።

እንደ እኔ የተከበሩት የሰላም መምህር ኔልሰን ማንዴላ በዘመናችን ከማንኛችንም በላይ ለኢትዮጵያዊነት የከፈሉት መስዋዕትነት፤ ለሀገራቸው ከከፈሉት መስዋዕትነት ቢዘል እንጂ አያንስም። የአብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገሮች መሪዎችና የኢትዮጵያን ፍርሰት ምኞታቸው የነበሩ ያአደጉ ሀገሮች መሪዎች ሁሉ አዲስ ዴሞክራሲያዊ ወጣት መሪ እያሉ ሀገር አፍራሹን ሄሮድስ መለስን ሲያንቆለጳጵሱ፤ ለሸሩና ለደባው ሲያሸበሽቡ፤ የምህረት ቀንዲል የሆኑት የተከበሩ ኔልሰን ማንዴላ ግን ለኢትዮጵያ አንድነትና ልዑላዊነት በፅናት እንደቆሞ እነሆ አለፉ። ለኢትዮጵያዊነትም በ21ኛው ምዕተ - ዓመት የፓን አፍሪካኒስትነትን ልዑቅነት በተግባር አቅልመው ... ቤዛ ሆኑ። የተከበሩት የነፃነት አርበኛ ኔልሰን ማንዴላ የታሪካችን ጠባቂ፤ ሁነኛ ባለሟል፤ ትንፋሽና ማህደርም ነበሩ ... አቅማቸው ኃይል ነበረው። ንጉሥ ዳዊት በምስባኩ "የቤትህ ቅናት በላኝ" እንዳለው ሁሉ ለነፃነት ዓርማቸው - ለክብራችን፤ ለእናት ሀገራችን ለኢትዮጵያ የወጣላቸው ቀናተኛ ነበሩ ማለት እችላለሁ ... ምልክታቸው ነበረችና ...

እጅግ የማከብራችሁ የጹሑፌ አንባቢዎች የሀገሬ ልጆች ... ውለታው ... ሸቀጥ አልነበረም። ውለታው የሚሸጥ የሚለወጥ የከንቱንት ክምር አልነበርም። የእኛነታችን ጠንካራ ሚስጥር በውስጣቸው በአጽህኖት የጸነሱ፤ ያረገዙ ግን ሳያገላገሉ ከነህምሙ ያሸለቡ የፍቅር አባት አካላችን ናቸው ኔልሰን ማንዴላ። በዚህ በከፋን ጠቀራማ ዘመን በህማማታችን ሳይለዩን በመንፈስ አብረውን የሆኑ፤ ሰንደቅ ዓላማችን የመንፈሳቸው ማህተም ያደረጉ አርማችን ናቸው ኔልሰን። ክቡርነታቸው ... በኢትዮጵያዊነት በተፃራሪነት የቆመ ኃይል ሁሉ መስጥረው በጥርሳቸው እንደነከሱት አረፉ። የነፃነት አርበኛው ... ለኢትዮጵያዊነት ተንገበገቡ። የቅኔው ልዑል ሎሬት ጸጋዬ ገ/መድህ በእሳት ወይ አባባ መድብሉ "የወንድ ልጅ እንባው በሆዱ" ነው ያለው ትንቢት ይፈጸም ዘንድ ...

እርግጥ ይህ ለተዋህዶ አማንያን የሚስጥረ ሥላሴ ያህል ጥልቅ ሲሆን፤ ኔልሰን በመንፈሳቸው መስጥረው በተግባር ያሳዩና ያስመሰከሩ ድንቅ የእኛነታችንና የማንነታችን ጠበቃ አባታችን ነበሩ። የተከበሩ ክቡር ኔልሰን ማንዴላ ለእኔ ትርጉም ነበሩ። ቅኔ ነበሩ። ውስጣቸው የምህረት ልዩ ሰፊ አንባ ነበረው፤ ለወልዮሽ የእኩልነት ማዕድ የማዬት ህልምና እውንነት ትግላቸው ለሰው ልጆች ሁሉ ነበር። እርግጥ ነው ይቅርታቸው ንዑድ ሆኖ፤ ግን በውስጣቸው የመሰጠሩትን የሰው ልጆች የእኩልነት፤ የነፃነት፤ የወንድማማችነት መብታዊ ጉልላት የሚያጎላ፤ እንዲያፈራ፤ እንዲለመልምልም በትህትና የሚያደርግ እንጂ የሚያከስም በፍፁም አልነበረም። ለግል ሕይወታቸው ያልተጨነቁ አበው ብዙኀን፤ አበው ግፉዓን ነበሩ ... ዕንባ አባሽ።

በድርጊት የበለጸጉት ክቡር ኔልሰን ማንዴላ ሆነው - መሆንን ለፅናት ሸለሙ። ሀገር መውደድ ምን ማለት እንደሆነ ተንትነውና በትነው እራሳቸውን አሳለፈው በመስጠት አተረፉ። ድንቁ ነገር የትርፉ ዕሴት ርትህን ወልዶ ትውልዱን ከጥፋት በማዳን አዲስ መርኅና መንገድ በነፃነት ዜማ ቀይሶ እኩልነትን አበቅለ። ዘረኝነትንም ነቀለ - ከሥሩ። የክብር ምንጩ ሀገርን ከማፍቀር፤ የሕይወት ዋጋ ተሽቀዳድሞ ከመክፈል የሚነሳው ከራስ ነውና እንሆ እሳቸው በተግባር ስለ አማረባቸው፤ ፍቅር ካለገደብ ስለተሸለሙ አርያነታቸው ዛሬ ዓለምን በተደሞ አስለቀሰ። የኃያሉ መንግሥት የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ ለበርካታ ቀናት ተውለበለበ። ዓለም በሙሉ በአኃቲ ድምጽ ኀዘኑን ተጋራ ...። ስኬቱ ውጤትን አዝምሮ የጥቁርነትን አንገት አቀና። የኔልሰን የኣርነት እንቅስቃሴ የመከራ ዘመን ያመረተው ፍሬ፤ ብሔራዊነትን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊነትን ያጸደቀ - ድንቅ ሐዋርያነት ነበር። ሁለመናው ቆሞ እንሆ ይመሰክራል። ተቋምነቱ ሳይደክመው ይሰብካል በቋሚነት - ለዘለዓለም።

በተከበሩ የኔልሰን ማንዴላ ዘመን ምንም የባከነ ጊዜ አልነበረም። ታሪካቸው መከራን አስመችቶ በመቀበል ትዕግስትን አበራ፤ የእኩልነት የተጋድሎ ጊዜያቸው በሆደ ሰፊነት ሁሉንም የአሳር ቁልል ያስተናገደ ልዩ ትዕይንት ነበር። ስለሆነም ትርፉ መንፈስ ሆነ። በመሆኑም ጥቁርነት የቀፈፈውን ... ሥር የሰደደው ዘረኝነትን አልደፈረም ቢልም አለሰለሰ፤ የከረረውን ትዕቢት አረገበ፤ የዘረኝነት በሽተኞችን ፈቅፍቆ ፈወሰ - ልዩ መድኃኒት ነበረውና፤ ተጋድሎውም ትውልዱን በፍቅር አጋባ። ስለሆነም ያ ሁሉ ግፍ ተቀብሮ ብሔራዊ ክብርን ወለደ። መገለሉ ከስሞ ብሔራዊ መገለጫን አዘከረ። ስለሆነም የምልዓቱ ግራሞት ያስባለ እንዲሆን አደረገ። ማየት ማማን ነውና መስዋዕትነቱ ጭብጥ ሆነ። ስለሆነም የኀዘኑ ታዳሚዎች ሁሉ ከውስጣችን አዘን። ብዙም አትኩሮትን የማይለግሱ ሀገሮች እንኳን በሚዲያ የሚሰጡት አስተያየት ሳዳምጥ ተግባር ምን ያህል የቅዱስ መንፈሥ ኃይልና መስህብም እንዳለው ተረዳሁ። ተገነዘብኩ። የተከበሩ ኔልሰን ማንዴላ የላቀ የተግባር ቅዱስ መንፈሥ ነበሩ። ስለዚህም ኔልሰን ማንዴላ አልሞቱም አረፉ እንጂ።

እኔ እንደማስበው የተከበሩ ኔልሰን ማንዴላ ቅንም ነበሩ። አምላካችን ቅኖችን ይወዳልና መስዋዕትነታቸውን በድል ቋጭቶ የዓለምን ልብ በፍቅር እንዲሰግድ እንሆ አደረገ። ደቡብ አፍሪካም ዕድለኛ ነው። ይህን መሰል እግዚአብሔርና የሰው ልጆች የሚወዱት የእርቅ ልዩ የወርቅ ድልድይ፤ የተመረቀ ሙሴ ሰጣቸው። እርግጥ ነው የተከበሩ ኔልሰን ማንዴላ ከእኛዎቹ ቀደምት አርበኞቻችን ጋር የትውፊት ቅብብል አድርገዋል እላለሁ፤ ከዓፄ ቴዎድሮስ፤ ከአፄ ዮሐንስ ሆነ ከአፄ ሚኒሊክ እንዲሁም ከአፄ ኃይለሥላሴ። በተጨማሪም ከመጀመሪያው አፍሪካዊ የሽምቅ ውጊያ "ከጥቁር አንበሣ" ጋራ የአደራ ውርስ እንደ አደረጉ ይሰማኛል። ያነሳሳቸው፤ የቀሰቀሳቸው ውስጣቸውን ለነፃነት ትግል ተክል እንዲያቆጠቁጥ፤ በፀጋ ያበረከተው ይህ አፍሪካዊ የአርበኝነት፤ የተፈሪነት፤ የመቻል ቅምጥ ጥሪትና ቅርስ ነው ብዬም አምናለሁ። የዛሬን አያድርገውና የነፃነት ትርጉም በኽረ እናት ኢትዮጵያ ክብርት ሀገራችን ነበረችና።

እኔ እንደሚሰማኝ የመጀመሪያ የነፃነት ፍለጋ ጽንሰት በኔልሰን ማንዴላ የወጣትነት ዘመን ህሊና የተጠነሰሰው፤ ፊደል የቆጠረው ኢትዮጵያ ቅኝ ካለመሆኗ የሚነሳ ይመሰለኛል። ያ ... ለእንግሊዞች፤ ለደርቡሾች፤ ለፋሽስቶች ያልተንበረከከ ኢትዮጵያዊነት በመላ አካላታቸውና ደማቸው ውስጥ ቦታ ሰጥቶ ትርጉም መሆኑን ነጥሮ እነሆ ለዓለም አስነበበ ... እላለሁ።

ሄሮድ መለስ ዜናዊ በማንአለብኝነት የገፉት፤ በእብሪት የጠቀጠቁት፤ በግፍ የጨፈለቁት፤ በትዕቢታቸው የደፈጠጡት፤ በበቀል የጨቀጨቁት፤ የናቁትና ያዋረዱት የኢትዮጵያዊነት ቅዱስ መንፈሥ ሰንደቅነቱ ወይንም መንበርነቱ በብሔራዊነት ብቻ የተወሰነ አልነበረም። ... ለአህጉራችን ለአፍሪካ ሆነ ለዓለም ፋና ወጊና መሪ እጬጌም ነውና። ይህ ዘመን የሰጣቸው ያደጉ ሀገሮች የሚፈሩት ቢሆንም፤ አሁንም እንደ እኔ ዕይታ የተከበሩ ኔልሰን ማንዴላ ግን ለኢትዮጵያውያን የተለየ ፍቅርና አክብሮት ነበራቸው እላለሁ። 

መቋጫ

ሰማዕቱ፤ መምህሩ፤ ሐዋርያውና ሰባኪው ቅዱስ ጳውሎስ ... ወደ ቆላስያስ በላከው በአንደኛይቱ መልዕክቱ ምዕራፍ 4 ቁጥር ከ11 እስከ 12 "ይህንን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ ይበቃኛል ማለትን ተምሬያለሁና። መዋረድንም አውቃለሁ፤ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም፣ መብዛትንና መጉደልን ተምሬያለሁና" ይላል።

ሥልጣን ትወደዳላች፤ ክብርም ከሁሉ በላይ ትፈቀራለች፤ የሥልጣን ዘመናቸውን ሊደግሙ ቢፈልጉ የሚያግዳቸው አልነበርም። እሳቸው ግን አላደረጉትም። ከዚህም አንጻር ኔልሰን ማንዴላ የይበቃኛልም ልዑል ነበሩ፤ እንደ መምህሩ ቅዱስ ጳውሎስ። በሌላ በኩል የተከበሩ ኔልሰን ማንዴላ፤ በቀልን ያሸነፉና የረቱ የአንደበተ - እግዚአብሔር ሰማዕትም ናቸው። የፈጣሪያቸውን ፈለግም የተከተሉ ማህሪ። ዓለምን የሚካልለው ዝቀሽ ተምክሮና ብቃታቸው ደግሞ ከመከራቸው ፈቅደው የተቀለቡ ስለሆኑ የነፃነት ብርቅዬ ትምህርት ቤት ነበሩ።

ኔልሰን በየትኛውም አጋጣሚ በሚዲያ ሲመጡልኝ ሁሉ ፊታቸው ፈክቶ፣ ውስጣቸውን ፈቅደው በፍቅር እንደ አስጎበኙን ... ተሰናበትን። ገፃቸው አዘውትሮ በትጋት አስተማረን፤ በጽናት ባትለው ዘመኑን በሥልት በፍቅር ገሩት። ምህንድስናቸው ሰባኪ ... ትንግርትን መስካሪ ነበር፤ እውነትንም ... አፍላቂ። የምዕተ - ዓመቱ የነፃነት ሊቅ፤ ትውልድ ሊተካቸው የማይችሉ ዕንቋችን ነበሩ። ፅናትን በልጅነት ሸምተው ፅናትን ለሁላችን በቅንነት አቅንተው፤ ፅናትን አንግሠው ከፅናታቸው ጋር በፅናት - ድንግልና ...ትምህርት ቤት ሆነው አረፉ። በወጣትነት በዕድሜ መጥ የሆኑትን ፈተናዎች ሁሉ አንበርክከው ከወርቅ በተሰራ ብርታታቸው የነፃነት ወተት በድንበር አልቦሽ ቀለቡ።

የዘመናችን ... የኢትዮጵያዊነት መሪዎች ትምህርት ቤቱን በመሆን ካዘመሩት ማሳው ለፍሬ ይበቃል። ውዳሴ መልካም ቢሆንም፤ በመሆን ካልቀለመ ... መዘክር ብቻ ሆኖ ይቀራል። ... እራሳቸውን ሳይዋሱ፤ ሳይበደሩ፤ እንደ ተፈጥሯቸው ሆነው ከተለዩን የአፍሪካ ብርሃን የኛዎቹም ዓለም ዓቀፍ ተቀባይነትን በመስዋዕትነት ይሸምቱ ዘንድ በርከክ ብዬ እለምናቸዋለሁ ... አምላካችንም ይርዳን። ... ካለጠበቂ፤ ካለአጃቢ የሚሄድ የጓደኛ መሪ ... መከፋቱ - መካፋታችን፤ ሕምሙ - ሕመማችን፤ ሞቱ - ሞታችን የሚሆን እረኛ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ መርቆ ይስጠን - አሜን! የናፈቀኝ እሱ ነውና ...

ጌጣችና ውዳችን የተከበሩ ኔልሰን ማንዴላ መከራዎትን በምድር ጨርሰውታል። ጽድቅ ለዕልፎች መቃጠል ነበርና አድርገውታል። ... መልካም የጽድቅ ጉዞና የእረፍትም ጊዜ። ለነፃነት ቤተኞች ሁሉ መጽናናትን እመኛለሁ። ከድርጊት ለተማርነው መልካም የኔልሰን ተመክሮ ውስጣችንን ሳንሸፍን ወይንም ሳንከናንብ ገልጠን በንጽህና እንፍቀድለት - እላለሁ።

አራት ዓይናማው መንገዳችን ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው።

እግዚአብሔር ይስጥልኝ!


ሥርጉተ ሥላሴ
07.12.2013

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ