የመለስን ልቃቂት አይቶ፣ ሰው እንዴት ያድራል ተኝቶ?!
ይገረም አለሙ

የፖለቲካ የበላይነትን በማረጋገጥ የሥልጣን ዕድሜን ለማራዘም ኢኮኖሚውን መቆጣጠር ወሳኝ መሆኑ ጥናትና ምርምር የሚጠይቅ የተለየ እውቀትም የሚሻ ጉዳይ አይደለም። ፖለቲከኞቹ ብቻ ሳይሆኑ ማንኛውም ሰው ሊያውቀው የሚችል ጉዳይ ነውና። አበውም "ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ" ይላሉ። ቁም ነገሩ ታዲያ ማወቁ ሳይሆን መተግበሩ ነው። እናም ወያኔ ይህን አውቆ ጠቀሜታና አስፈላጊነቱን ተረድቶ በኢኮኖሚ የበላይነት ፖለቲካውን ለመቆጣጠርና የሥልጣን ዕድሜውን ለማረዘም ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ባለሥልጣናት ለራሳቸው መጦሪያ ለልጆቻቸውም ተንደላቆ መኖሪያ የሚሆን ሀብት ማከበታቸውን የአቶ ኤርምያስ ለገሰ የመለስ ልቃቂት መጽሐፍ በመረጃና በማስረጃ አሳይቶናል።
የወያኔ እውቀት ይሁን የሌላው አስተውሎት ማጣት፣ የወያኔ ድፍረት ይሁን የሌላው ፍርሀት፤ የወያኔ ይሉኙታ ቢስነት ይሁን የሌላው አድር ባይነት፣ የትኛው ሚዛን ደፍቶ ለዚህ እንዳበቃን ባይታወቅም (እያወቅን ባናውቅም) አናሳው ወያኔ ኢትዮጵያውያንን በቁማችን ገፎናል፤ ዓይናችን እያየ ማስተዋል፣ ጆሮአችን እየሰማ ማዳመጥ ተስኖን ተቃውሞ ቁጣችን ከሰልስት ግፋ ቢል ከሳምንት የማያልፍ ሆኖ ኢትዮጵያን ያለማንም ሀይ ባይ ዘርፏታል።
ተጽፎልን አንብበን፣ ተነግሮን ሰምተን የማይቆጨን በመሆናችንም ሲሻው በሕግ ሽፋን ካልሆነም በምን ታመጣላችሁ እብሪት ዝርፊያውን በአይነትም በመጠንም እያሳደገና እያሻሻለ መጥቷል፣ ይቀጥላልም። "የናቁትን አገር በአህያ ይወሩታል" እንዲሉ አዩን ለዩንና ዝርፊያቸው ሳያንሰን ስለ መዝርፊያ ድርጅቶቻቸው ማንሳት መኃይምነት ነው በማለት እስከ መሳደብ ደረሱ።
በማላዘን - ምንም ነገር አይሆን፣
ሃያ አምስት ዓመት ሙሉ ወያኔ ዘረፈ፣ ገደለ፣ አሰረ፣ ወዘተ እያለ የሚያላዝነው ወገን በማላዘን አይደለም ነጻነትን ማግኘት ዝርፊያን ማስቆም እንደማይቻል እንዳልተቻለም መረዳት ባለመቻሉ፤ ወይንም ባለመፈለጉ ዛሬም እዛው ላይ ቸክሎ ማላዘኑን ቀጥሏል። "ውሾቹም ይጮኻሉ ግመሉም ይሄዳል" የሚለው አባባልም ድርጊትም እንደዚሁ ቀጥሏል። ወያኔ የሚፈጽመው ሁሉ መፈጸም ያለበትን ነገር ሆኖ ሳለ ወያኔ ለምን እንዲህ ያደርጋል እያሉ መጠየቅም ሆነ ተዘረፍን ታሰርን ተገደልን እያሉ ማላዘን "ከእባብ እንቁላል ርግብ መጠበቅ" የሚሉት አይነት ነው።
እኛስ ምን አደረግን?
ወያኔ ዓላማ ያደረገውን፣ ለግቤ ይበጃል ያለውን፣ ያመነበትን ዝርፊያም ሆነ ግድያ፣ ማሰርም ሆነ ማሰደድ ፈጽሟል እየፈጸመ ነው፣ ወደ ፊትም ይቀጥላል። ይህን እያነሱ የአዋጁን በጆሮ እንዲሉ ከመጮህና ከማላዘን እኛ ምን አደረግን ምንስ አላደረግንም ብሎ ራስን መጠየቅና ወያኔን መገዳደር የሚያስችል አቅም በመፍጠር ትግሉንና በእምነት በጽናት መያዝ ነበር የሚሻለው። ግና በአብዛኛዎቻችን ዘንድ ይህ የለም። ነገረ ስራችን ወያኔ በአደባባይ የሚፈጽማቸውን ነገሮች የተደበቁና የማይታወቁ ይመስል እነርሱን እያነሳን ብሶት ማውራት፣ ማላዛን በዚህም ትልቅ ገድል የፈጸምን ያህል ረክተን ለሽ ብለን መተኛት ነው። እኛ ያልተዘረፍን ማን ይዘረፍ? እኛ ያልተናቅን ማን ይናቅ?፣ እንደውም አንዳንዶቻችን "የአባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ" የሚለውን ብሂል ተከትለን ለሚጣልልን ፍርፋሪ የአገር ሀብት በማዘረፍ ተባባሪ ሆነን እንሰለፋለን።
በኤርምያስ ለገሰ የመለስ ልቃቂት መጽሐፍ በበቂ ማስረጃ የተገለጸውን ዘረፋ በምንም ተአምር ወያኔ ብቻውን ሊያከናውነው አይቻለውም። አንድም ራሳቸውን ለወያኔ አሳልፈው በሰጡ ሆድ አደር ሎሌዎች ተባባሪነት ሁለትም በብዙሀኑ (እኛ) ግዴለሽነት ነው ጠመንጃ ነካሾቹ ባለ ቢሊዮን ብር ጌቶች ለመሆን የበቁት። ስለሆነም አስር ጣታችንን ወደ ራሳችን አዙረን ማየትና መጠየቅ እስካልቻልን ድረስ ብሶት በማውራትና በማላዘን ሃያ ስድስት ዓመት ያመጣነው ነገር የለም ወደ ፊትም አናመጣም። ወያኔ ማድረግ ያለበትን ነው የሚያደርገው፣ እኛስ? ለዚህ ድፍረቱ ሊኖረን ይገባል።
ከቢቢኤን ራዲዮ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረጉ የወያኔ ሁለት የቀድሞ ጀነራሎች የተናገሩት ራሳችንን ለማየት ችግራችን በአብይና ወቅታዊ ማስረጃነት ሊቀርብ ይችላል። ቃለ ምልልሱን ጨርሶ የማደመጥ ትእግስቱም አቅሙም አልነበረኝም‹። ከወያኔ ከተለዩ ከአስር ዓመት በላይ የሆናቸውና ይህንንም ግዜአቸውን በአስመራ ከትመው ያሳላፉት እነዚህ ጀነራሎች እንደ ጦር መኮንነታቸውና አንደ ወያኔም ተቀዋሚነታቸው ይሄ ነው የሚባል ነገር ስለመስራታቸው ሳንሰማ ስለ ወያኔ ማንነትና ምንነት ስለሕዝቡ ድካም ሊነግሩን ይዳዳቸዋል።
"ወያኔ በሰራለት ከረጢት ውስጥ ተከቶ የሚገኘው ሰራዊት" ሲሉ ከረጢቱን በመስፋቱ የእነርሱ ድርሻ ስለመኖሩ የሚያስታውሱ አይመስሉም፤ ጦር አስከትለው አስመራ ገብተው አስር ዓመት ምንም አለማድረጋቸው ሳይታወሳቸው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠንክሮ ባላተቋረጠ ሁኔታ ትግሉን ቢያቀጣጥል ሰራዊቱን ወደ እርሱ ማምጣት እንደሚችል ይናገራሉ። ጠያቂውም እናንተ ምን አደረጋችሁ፣ ለትግሉ ከሕዝቡ በፊት እናንተ አትቀርቡም ወይ፣ ስንቶች የተደላደለ ህይወታቸውን ጥለው ለትግሉ ራሳቸውን አሳልፈው ሲሰጡ እናንተ የጦር መኮንን ሆናችሁ ከትግሉ ርቃችሁ ወያኔን ለማውገዝም ሆነ ሕዝቡ እንዲህ ቢያደርግ ብሎ ለመምከር የሞራል ብቃት ይኖራችኋል ወይ ወዘተ ብሎ መጠየቅ በተገባው ነበር። ራስን የማየት፣ የመጠየቅ ብሎም የድርሻ ተጠያቂነትን የመውሰድና ይቅርታ የመጠየቅ ነገር እንዲለመድ ጋዜጠኞች ትልቁ ሀላፊነት አለባቸው። ወያኔን ማውገዝ የተቀዋሚነት መገለጫ መሆኑም ማብቃት አለበት። ከብዙ ውግዘት ዋይታና ጩኸት ትንሽ ተግባር ነው ውጤት የሚያስገኘው። ለዚህ ደግሞ ወያኔን ለአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ያበቃውን ድርጊት መለስ ብሎ ማስታወስ በቂ ነው።
ሌላው በየትኛውም የለውጥም ሆነ የነጻነት ታሪክ ሕዝብ ሆ ብሎ ወጥቶ የታገለበት አገርም ዘመንም የለም ሊኖርም አይችልም፣ ጥቂት የቆረጡ የጸና ዓላማና እምነት ያላቸው ግንባር ቀደሞች ባደረጉት ትግል እንጂ። ስለሆነም የድርጅት መሪ ተብሎ አንድም ተግባር ሳይፈጽሙ እንዲሁም የወያኔ ተቀዋሚ ነን ብለው የትከሻ ማእረግ ደርድረው ከሹመቱ ጫፍ ጀነራልነት ደርሰው ብዙ ሲጠበቅባቸውና ሊያደርጉ ሲችሉ ምንም ሳያደርጉና አለማድረጋቸውንም ከምንም ሳይቆጥሩ ሕዝብን ለመውቀስና ለመክሰስ የሚደፋፈሩበት ሁኔታ መገታት አለበት፣ ለዚህ ደግሞ ጋዜጠኞች ትልቅ ድርሻ አላቸው።
በወያኔ ተበልጠናል፣
አመንም አላመንም በወያኔ ተበልጠናል። ሃያ አምስት ዓመት ቀጥቅጦ እየገዛን ያለን ድርጅትና መሪዎችን እንዲሁም አቶ ኤርምያስ በመጽሐፉ የነገረንን ዘረፋ የፈጸሙ ሰዎችን የተለያየ ስም እየሰጠን ስንሳደብና ስንዘልፍ ራሳችንን እየሰደብንና እየዘለፍን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ለምሳሌ ብዙዎች የወያኔ ባለሥልጣኖችን መኃይሞች በማለት ይገልጹዋቸዋል። እነርሱ መኃይም ከሆኑ እኛ በመኃይም የምንገዛውስ? እነርሱ ምንም እንበላቸው ምን እየገዙን ነው፣ አገሪቱን ዘርፈው የሀብት ጣራ ላይ ደርሰዋል። እኛ ደግሞ ተበልጠናልና ዘረፋውን ማስቆም አገዛዙን መገላገል አልቻልንም። ምንም ይሁን የበለጠን ኃይል በመስደብ በማንቋሸሽ በመዘለፍ አለያም በማላዘን የሚመጣ ነገር የለም፤ በልጦ በመገኘት እንጂ።