ግርማ ካሳ

Geez
በተለምዶ ግዕዝ ፊደል ተብሎ የሚጠራው የሁሉም ኢትጵያያውያን ፊደል

የተከበሩ የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ ማሩ (የመርካቶ ልጅ፣ ኩሩ የኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ) እንዲህ ብለው ጦመሩ፤

“እነዚህ ትምህርት ቤቶች (በአፋን ኦሮሞ የሚሰጡ) በጥራት ትምህርት ሊሠጡ የሚችሉት በኦሮሚያ መስተዳድር አዲስ አበባ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች በሙሉ፣ እንዲሁም በፌዴራል መንግሥት ውስጥ የሚሰሩ የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ እና የዚህ ፖሊሲ ደጋፊ ሰራተኞች ቢቻል በፈቃደኝነት ካልሆነ ግን በግድ ሁሉም ልጆቻቸውን እነዚህ ትምህርት ቤቶች ውስጥ መላክ እንዳለባቸው ይሰማኛል”

“ፊንፊኔ የሚለውን ቃል ቦይኮት ማድረግ ያለብን ይመስለኛል” (አዲስ አበባን ፊንፊኔ ማለቱ)

እስማማለሁ። ነገር ግን አንድ የኦህዴድ ባለስልጣን ሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ሰራተኛ በፍቃደኝነት ልጆቹን ይልካል ብዬ አላስብም። ግዴታ ከተባለም ሽምጥጥ አድርጎ ነው የሚዋሸው፣“ፖሊሲውን አልደገፍም ነበር” ብሎ። ሁሉም በአማርኛ ት/ቤት እንጅ በአፋን ኦሮሞ ት/ቤት ልጆቻቸው እንዲማሩ አይፈልግም። ከዚህ በፊት ተሞክሮ አልሰራም። ይሄም ከዘር ወይም ከብሔረሰብ ጋር የተገናኘ ሳይሆን ከኢኮኖሚና ከሥራ እስድል ጋር የተናኘ ነው። ልጆቻቸው አማርኛ እንዲማሩላቸው ስለሚፈለጉ፣ ወደ አዲስ አበባና ወደ አዳማ፣ ብዙ ከኦሮሚያ (ወለጋ፣አርሲ ...) የመጡ ኦሮሞዎችን አውቃለሁ። (በነገራች ላይ በአዳማ በአማርኛና በኦሮሞኛ በሁለትም የሚሰጡ ት/ቤቶች አሉ። ግን ብዙ ሰው በፍቃደኝነት ወደ አማርኛ ት/ቤቶች ነው ልጆቹን የሚልከው። በሌሎች የኦሮሚያ አካባቢዎች ግን እነ አዳማ ያላቸው አይነት እድል የላቸውም)

እንዲህ ስል አፋን ኦሮሞን መማር አያስፈልግም ማለቴ አይደለም። አፋን ኦሮሞን መማር ጥቅም አለው። አፋን ኦሮሞን ኦሮሞው ብቻ ሳይሆን ሁሉም ሊማረው፣ ሊናገረው ቢችል በጣም ይረዳል። በግሌ በሁሉም የአዲስ አበባ ት/ቤቶች እንደ ሰብጀክት መሰጠት አለበት ባይ ነኝ። ግን አፋን ኦሮሞ አማርኛን ሊተካ እንደማይችል መቀበል ያስፈለጋል። ፀረ-አማርኛ አቋም በመያዝ መንቀሳቀስ ጎጂ ነው። በአማርኛ፤ ላይ ጥላቻ ስላለ ብቻ አማርኛ ዜጎች እንዲማሩ አለመደረጉ፣ በነዚህ ወገኖች ላይ ትልቅ የኢኮኖሚክ ጉዳት ነው የፈጠረው።

ይሄን በማለታችን አዳንድ አክራሪዎች ፀረ-ኦሮሞ ሊሉን ይሞክራሉ። ነገር ግን እርግጠኛ ነኝ ከስሜት በጸዳ መልኩ ረጋ ብለው ሐሳቦቻችን የተከታተሉ፣ የኛ አቋም pro-oromo አቋም እንደሆነ ይረዳሉ።

- እነርሱ ኦሮሞው ከአማርኛ ጋር ተጣልቶ፣ የመሻሻል እድሉ ጠቦ እንዲኖር ነው የሚፈልጉት።ትልቁ ቀጣሪ በሆነው በፌዴራል መንግስት፣ በአማራው፣ በደቡብ፣ በቤኔሻንጉል፣በጋምቤላ ክልሎች፣ በአዲስ አበባና በድሬዳዋ ከተሞች … ሥራ እንዳያገኝ። እኛ ኦሮሞው የአገሪቷን ዋና ቋንቋ አማርኛ ተምሮ፣ መጻፍና ማንበብ ችሎ በሁሉም የአገሪቷ ክፍል ያለ ምንም የቋንቋ ተጽኖ እንዲሰራ ነው የምንፈልገው።

- እነርሱ አፋን ኦሮሞ እንደማንነት መገለጫ ነው የሚያዩት። ከዚህም የተነሳ አማርኛ በመናገራቸው ኦሮሞነታቸውን ያጡ ይመስላቸዋል። እኛ ቋንቋ የማንነት መገለጫ ሳይሆን መግባቢያ ነው ባዮች ነን። አሁን አላውቅም እንጅ፣ በፊት ግን በሐረር ያሉ ኦሮምኛም፣ አማርኛም አንዳንዶቹ አደርኛና ሶማሌኛም ይናገሩ ነበር። በወልቃይት ትግሪኛ፣ አማርኛ አንዳንድ ቦታም ዐረብኛ ይናገራሉ። ቋንቋ የማንነት መገለጫ ተደረጎ መወሰድ ሲጀመር ግን፣ ትግሪኛ የተናገረ ትግሬ ነው ሲባል ግን ችግር ተፈጠረ።

- እነርሱ ልጆቻቸውን ደህና ት/ቤት እያስተማሩ ነው፣ ለርካሽና የኋላ ቀር የፖለቲካ አይዲዮሎጂያቸው ብለው፣ አማርኛ እንዲጠላ በማድረግ በድሃው ኦሮሞ ልጅ ሕይወት ነው የሚጫወቱት ። እኛ ልጆቻችን ጥሩ የወደፊት እድል እንዲገጥማቸው እንደምንፈልገው የኦሮሞም ልጅ ብሩህ ሕይወት እንዲኖረው ነው የምንፈልገው። ስራ አጥቶ እንዲጎሳቆል አንፈልግም።

- እነርሱ በዘረኛና ጠባብ ፖሊሲዎቻቸው በኦሮሞው ማኅበረሰብና በሌላው መካከል መቃቃርና ልዩነት እንዲፈጠር ይሰራሉ። ከዚህ የተነሳ ኦሮሞው በብዛት በሚኖርባቸው ከአዲስ አበባ ራቅ ባሉ አክባቢዎች የንግድ፣ የቱሪዝም የመሳሰሉ እንቅስቅሴዎች በስፋት ሊስፋፋ አልቻለም። እስቲ አስቡት አሁን ማንነው የዓኖሌ ሐውልት ያለበት አካባቢ ሳይፈራ የሚሄደው? ሕዝቡ ደግና እንግዳ ተቀባይ ሆኖ፣ በሌላው አይምሮ ውስጥ ግን ከኦሮሞው ጋር በጭራሽ የማይገናኝ አስተሳሰብ እንዲገባ፣ እንዲፈራ ከመደረጉ የተነሳ፣ እንደ አዋሳ፣ ባህር ዳር ያሉ አሶሳ ሳትቀር ሲሻሻሉ እንደ ነቅምቴ፣ መቱ ... ያሉ ግን ወድቀዋል። እኛ ዘረኞች የዘረገቱ የመፈራራት ግንብ ፈርሶ ኦሮሞው በባህሉ እንግዳ ተቀባይ ሌላው የሚያቅፍና እንድ እራሱ አድርጎ የሚቀበል (በጉዲፍቻ ባህል እንዳየነው) መሆኑን፣ ኦሮሞው ሌላው ጠላቱ ሳይሆን፣ ከሌላው ጋር የተዋለደና የተዛመደ መሆኑን እያስረዳን፣ ሁሉም ዜጎች ወደ ባህር ዳርና ወደ አዋሳ ሲሄዱ ነጻነት እንደሚሰማቸው ወደ ሁሉም የኦሮሚያ ግዛቶች ለመሄድም ነጻነት እንዲሰማቸው ለማድረግ ነው የምንሰራው። እነ ነቀምት፣ እነ አሰላ እነ መቱ በንግድ በቱሪዝም እንዲያድጉ፣ እንዲሻሻሉ ነው የምንፈልገው።

- እነርሱ አፋን ኦሮሞ በኦሮሚያ ውስጥ ብቻ ተወስኖ፣ ኦሮሞው ከሌላው ጋር እንዳይገባባና እንዳይነጋገር፣ እንዲለያይ ነው የሚሰሩት። እኛ አፋን ኦሮሞ ከኦሮሚያም አልፎም በሌሎች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ እንዲነገር፣ ከኦሮሚያ ውጭ ባሉ ትምህርት ቤቶች እንደ ሰብጀክት እንዲሰጥ ነው የምንፈልገው። ከዚህም የተነሳ ለምሳሌ ከአዲስ አበባ ውጭ ያሉ ኦሮሞ አማርኛን በደንብ አውቀው አዲስ አበባ ሲመጡ በነጻነት ከከተሜው ጋር እንዲግባቡ፣ የአዲስ አበባ ልጆችም ወደ ገጠር ሲሄዱ በአፋን ኦሮሞ ከገበሬው ጋር እንዲግባቡ ነው የምንፈልገው።

- እነርሱ ኦሮሞውን በጠባብነት ጆንያ አሳንሰው ነው የሚያዩት። መገንጠልን፣ ልዩነትን፣ ጥላቻን፣ ቁርሾች ነው የሚያስተምሩት። እኛ የኦሮሞውን ግንድነት፣ አሁን ያለችዋን ኢትዮጵያ በማቅናት ዙሪያ የኦሮሞውን ጉልህ ሚና ነው የምንናገረው።

- እነርሱ አገር አስገንጣይ፣ የውጭ ወራሪዎች ተባባሪዎችን፣ ዘረኞች ነው እንደ ሞዴላቸው የሚያዩት፤ እንደ ዋቆ ጉቶ ያሉትን። እኛ እንደ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ አብዲሳ አጋ፣ ጀነራል ጃጋማ ኬሎ፣ አባመላ ፊታወራሪ ሃብቴ ዲንግዴን፣ ጀነራል ደምሴ ብልቱ፣ አቡነ ጴጥሮስ (አባ መገርሳ) ... ያሉትን፣ አገር ያቀኑ የሕዝብ ኩራት የሆኑ የኦሮሞ ጀግኖችን ነው የምንዘክረው።

- እነርሱ የኢትዮጵያው ብቻ ሳይሆን የአፍሪካ ሃብትና ቅርጽስ የሆነው የግዕዝ (ሳባ) ፊደል በመጸየፍ፣ ፍረንጆችን እንደ ጌታ የማየት የባሪያነትና የበታችነት መንፈስ ስለተናወጣቸው፣ ከአፋን ኦሮሞ ሆነ ከኦሮምሞ ጋር ምንም ያልተገናኘ የላቲን ፊደል በሕዝቡ ላይ የዘረጉ ናቸው። እኛ የቀደምት የኦሮሞ ልሂቃን፣ እንደ አናሲሞስ ያሉ፣ የተጠቀሙበት የኦሮሞውን ኩራት የሆነው ኢትዮጵያዊ ፊደል እንጠቅም ባይ ነን።

- እነርሱ ኦሮሞውን በማጣላትና በመነጠል ለውጥ ይመጣል ባዮች ናቸው። እኛ ኦሮሞው ትግሉን ከሌላው ኢትዮጵያዊ ወንድሙ ጋር በማቀናጀት በኢትዮዮጵያዊነት ጥላ ስር ቢያደርግ፣ ከሌላው ጋር እጅ ለእጅ ቢያያዝ ተዓምር መስራት ይችላል ባዮች ነን።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!