ግርማ በላይ

Ethiopia and Eritrea
ኤርትዮጵያ

ግዕዝ/ትግርኛ ለማይረዱ አንባቢዎች ርዕሴን ግልጽ ላድርግ። ርዕሴ በቁሙ ወደ አማርኛ ሲተረጎም፤ “‹አትግደለው አታድነው› - የሻዕቢያ መመሪያ” የሚል ፍቺ ይሰጣል።

ሰሞኑን ከአንድ ትግራዋይና ከአንድ በቀድሞ አጠራር የኤርትራ ክፍለ አገር ተወላጅ ጋር የሞቀ ጭውውት ይዘን ነበር። የልብ ጓደኝነት ያህል በጣም ስለምንግባባ የሆድ የሆዳችንን ነበር የምንጫወተው።

እኛ ኢትዮጵያውያን በግል ደረጃ መተማመናችን የተሻለ ይመስለኛል። ወያኔ ከሆነ ሰው ጋር ራሱ በግል ጭውውት ብዙም አንለያይም። ችግሩ ወደ ቡድንና ወደ ጎሣ የጅምላ አስተሳሰብና አመለካከት ሲገባ ነው። ጎሣዊ የጅምላ አስተሳሰብ ሰውን ከሰውነት ደረጃ አውጥቶ ወደ ውሻና ጅብ የረከሰ የሆድ ተዝካር የሚለውጥ ትልቅ እርኩሰት ነው፤ በመሸታ ቤት ካንተ ተቀምጦ እየጠጣ ጋር የወያኔውን መንግሥት ተብዬ ተቋም በስድብና በዘለፋ ሲሞልጭ የነበረ ወያኔ ከቢጤዎቹ ጋር ሲሆን ደግሞ 180 ዲግሪ ተገምጥሎ ሌላ ሲያወራ ትታዘባለህ - ይቺ “ትንሽ ሥጋ እንደመፌር ትወጋ” የምትባል ተረት በዚህ ዘመን በጣሙን ሳትደምቅ አልቀረችም። ከዚህ የዘቀጠና ከውሻ እንኳን ከሚያሳንስ ቡድናዊ ስሜት መውጣት አለመቻል በ“ለምን ሰውን ፈጠርኩ” ጥያቄ ፈጣሪን ሳይቀር ለጸጸት የሚዳርግ ይመስለኛል።

እግዚአብሔር ሰውን ከጭቃ ጠፍጥፎና እስትንፋሱን እፍ ብሎ በመፍጠሩ እንደተቆጨ በንባብ ባላገኝም ከሰዎች አንደበት ሰምቻለሁና ያቺ ቅጸበት በሔዋን ጥፋት ወይም ከዚያን ዘመን እስከአሁን ድረስ ባለው ረጂም ጊዜ ውስጥ በሌሎች የዓለም ዜጎች በተሠሩ ወንጀሎችና በደሎች ተማርሮ ሳይሆን የሕወሓትን ዘግናኝ አጋንንታዊ ጭካኔና ቁሣዊ ገብጋባነት አስታውሶ ብቻ መሆን አለበት ብዬ አምናለሁ። ምክንያቱም የሕወሓትን የመሰለ ወንጀል በዓለም ውስጥ ማንም ሠርቶት አያውቅም፤ የነዚህን ሰዎች የመሰለ የገብጋባነት ጠባይ ያለው ፍጡርም እስካሁን በታሪክ ስለመመዝገቡ አላውቅም - በእምብርት የለሽነት የምትታማው ያቺ የፈረደባት አህያ ናት፤ እርሷ እንኳን ትጠግባለች፤ በቃኝንም ታውቃለች። እነዚህ መዥግሮች ግን ከ42 ዓመታት ለሚበልጥ ረጂም ዘመን በልተውና አገር ምድሩን ግጠው አሁንም ድረስ ከላስቲክ የተሠራ ሆዳቸው ይበልጥ ሲራብ እንጂ ገርገብ ሲል አይስተዋልም - ለነገሩ ከእግዚአብሔር የራቀ ስብዕና ከፀጋና ከበረከት የተለዬ በመሆኑ አብሯቸው ወደ ማዕድ የሚቀርበው የገደሉና የባሕሩ ጂኒ ነውና በምንም ነገር ሊረኩ አይችሉም። (በነገራችን ላይ በመብላታቸው በራሱ ቅሬታ የለኝም - ስለመብላት አለመብላት ማውራት ራሱ ወደ ተራ እንስሳነት መውረድ ነው፤ የነሱ የእንስሳቱ ትልቅ የሕይወት ተልእኮ ልክ እንደወያኔዎቹ ከዚህና ከመዋለድ አይዘልም። - እናም ስለሆድ ሳወራ ወደ ወያኔ ዝቅተኛ የስብዕና እርከን የወረድኩ ይመስለኛል …።

የኔ ችግር ታዲያ የሚበሉትን እንዴት ያገኙታል? ለምንስ ዜጎችን ይጨፈጭፋሉ? ወዘተ. ለሚሉት ጥያቄዎች የምናገኘው መልስ የሚሰቀጥጥ መሆኑ ነው)። በጥቅሉ ወያኔዎች የክፋት፣ የዐረመኔነት፣ የአስመሳይ ጎሠኛነትና የስግብግብነት ቁንጮ እንደሆኑ የተፈቀደላቸውን ጊዜ አገባደዱ። አስመሳይ ጎሠኛ የምለው ለትግሬው ለራሱም የማይመለሱ ጨካኞች መሆናቸውንና ትግሬንና ትግራይን ከአንደበታቸው የማይነጥሉት ይበልጡን ለስትራቴጂ እንጂ ከአንጀታቸው እንዳልሆነ ከአመጣጣቸው መረዳት ስለሚቻል ነው - የወባ ክኒን ያደሉ መስለው ታሪክ ዐዋቂና አገር ወዳድ ትግሬዎችን በሥውር የጨረሱ ከሃዲዎች መሆናቸውን እኮ መዘንጋት የለብንም። እነዚህ ጭራቆች በትግሬነት ስለትግሬ ይጨነቃሉ ብሎ ማመኑ ይቅርና ሚስትና ልጃቸውንም ለሰይጣን ገብሩ ቢባሉ የሚመለሱ አይደሉም። ለነገሩ ሆዳም ሰው ፍቅር አያውቅም - እንኳንስ ጎሣውን። ይህንንም ስል ታዲያ ትግሬነትንና ትግራይን ለዕኩይ ዓላማቸው አልተጠቀሙም ወይም አይጠቀሙም እያልኩ እንዳልሆነ በድጋሚ ማስረገጥ እፈልጋለሁ። በሚገባ ይጠቀሙባቸዋል። እንዲያውም ሕወሓት ከሌለች ትግራይና ትግሬ እንደሚጠፉ ያህል ሕዝቡ አምኖ እንዲቀበል ከጽንሰታቸው ጀምሮ ብዙ ሠርተዋል - “ተደጋግሞ የተነገረ ውሸት እንደ እውነት ይቆጠራል” ይባላልና ይህም ስብከት በአብዛኛው አልተሳካላቸውም አይባልም። ወያኔ ቢወገድ ሕይወቱ ጨለማ የሚሆን የሚመስለው፣ ሕወሓት አራት ኪሎን ቢለቅ ትግራይ ከምድረ ገጽ የምትጠፋ የሚመስለው ሞኛሞኝ የትግራይ ሰው ለማግኘት በተለይ አሁን አሁን ብዙ መንከራተት አያስፈልግም - በየአንድ ሜትሩ ታገኛለህ። ነገ በሻንጣው ይዞ የሚጠብቀን ብዙ ሥራ አለብን።

ከወሬያችን ውስጥ አንዱ ኤርትራ ውስጥ ስለመሸጉ “ኃይሎች” ነበር። ‹ኃይሎች›ን “ኃይሎች” ያልኩበት ምክንያት ለብዙዎች ግልጽ ቢሆንም ለአንዳንዶች ግልጽ ላይሆን ይችላልና “ድንቄም ኃይል!” ብዬ ለማሽሟጠጥ መፈለጌን በዚህች አጋጣሚ ሳልጠቅስ ማለፍን አልወደድኩም። በአጭር አገላለጽ ኢትዮጵያን የሚያጠፋ እንጂ ኢትዮጵያን ነፃነት የሚያቀዳጅ ምንም ዓይነት ኃይል ኤርትራ ውስጥ የለም። የአንድ ችግር መንስኤና መፍትሔ በአንድ አእምሮ ውስጥ ሊኖር ከቻለ ያ አእምሮ ጤናማ አይደለም - ይህን ድምዳሜ የሥነ ልቦናው የሙያ ዘርፍም የሚያጸናው ይመስለኛል። ጨለማና ብርሃን ኅብረት እንደሌላቸው ሁሉ ነፃነትና ባርነትም የጋራ ጉዳይ የላቸውም። የባርነታችን አምባሳደሮች የነፃነታችን ፋና ወጊዎች ሊሆኑ አይችሉም።

እርግጥ ነው አንድ ወቅት መስሎህና አምነህበት አንድ ነገር ልትጀምር ትችላለህ። በጊዜ ሂደት ግን ትምህርት ቀስመህ ርምጃህን ማስተካከል ይኖርብሃል። ያን ማድረግ ካልቻልክና በካፈርኩ አይመልሰኝ የደንቆሮ ልቅሶ መመሰጥን የምትመርጥ ከሆነ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለምትደርሰው የሕጻናት ማስተኛ ማባበያ ዘፈንህ ብቸኛ አድማጭ አንተው ራስህ ሆነህ ታርፈዋለህ። በዚህ የዕውቀትና የሥልጣኔ ዘመን ሰው ዝም አለ ተብሎ የቁጭ በሉ ቱማታ ዝንታለሙን (indefinitely) ሊቀጥል አይችልም፤ አይገባምም። ቢያንስ ማታ ስንተኛ የሚሞግተን የውስጣችን ዳኛ የሆነ የገዛ ኅሊናችን አለ። የሁሉም ነገር ዕድሜ (expiry date) አለው። የማታረጅ ብቸኛ ነገር እውነት ብቻ ናት።

ከሰሜን ኮሪያ ባላነሰ ሁኔታ ሕዝቡና ሀገሪቱ በአፋኝ ግለሰባዊ ጁንታ ተይዛ በምትሰቃይ አገር ውስጥ ተሸጉጠህ አሠርት ዓመታትን የተስፋ ዳቦ እየገመጥክና እያስገመጥክ ብትኖር የተደገመብህ አገልጋይ ባሪያ ሆነሃል፤ ስለዚህም ስለነፃነትና ዴሞክራሲ አንደበትህን ልትከፍት አትችልም - ማፈርን ማወቅም ብልኅነት ነው፤ ይሉኝታቢስነትና ሀፍረተቢስነት ሲጋባብህ ወደህና ፈቅደህ ከተቀበልክ ቢሳካልህ እንኳ በነገው ዘንድሮ የዛሬን የታሪክ ግርፋት የምትቀበለው አንተ ራስህ ነህ። ሕዝብ በሚስቅበትና በሚያፍርበት ቲያትር የምትደሰትና ጮቤ የምትረግጥ ከሆነ ሌላው ቦካሳና ሌላው ኢዲያሚን ወይም ሌላው ጋዳፊና ሌላው መንግሥቱ በቤተ ሙከራ ውስጥ በመሠራት ሂደት ላይ ይገኛሉ ማለት ነው። የኤርትራውን ታሪክና የ “ጦር ሜዳ” ውሎ በዚህ ብዘጋው በወደድኩ። የባሰ ሥጋት ስላለኝ ግን ወደዚያ ገብቼ ትንሽ ማለትን ፈለግሁ።

ከፍ ሲል እንዳልኩት የኢትዮጵያ መድኅን ኃይል ኤርትራ ውስጥ የለም፤ ሊኖርም አይችልም፤ እንዲኖር መጠበቅም ከጅልነት አያልፍም። በተቃራኒው ግን ሽንፈትን መቀበል ሞት የመሰለው፣ አቋምን በማስተካከል ተነሳሁበት ያለውንና የሚሊዮኖችን የነፃነት ፍላጎት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማርካት የገባውን ቃል መተግበር ያቃተው ፀረ-ኃይል የሆነ ቡድን አለ። አፍራሽ ኃይል ማለቴ ነው። “ጣፋጭ ፍሬ በዛፉ ላይ ሳለ ይታወቃል” – “የሚያጠግብ እንጀራ”ም “ከምጣዱ ላይ እያለ ይታወቃል። ” ሰዎችን/ዜጎችን ጡት እንዳልጣለ ሕጻን መቁጠር በቲቪና በኢንተርኔት ሳቢያ ካለዕድሜው የበሰለው የስድስት ዓመቱ የልጄ ልጅ አቡጡ በወንድሙ የሞባይል ስልክ የሚሠራውን ከተዓምር የማይተናነስ ቴክኖሎጃዊ ምጥቀት ለመቀበል እንዳለመፈለግ ያለ የዋህነት ነው። የዘመኑ ደናቁርት አምባገነኖች አፋችንን ስለያዙት፣ አእምሯችንን በአፍዝ አደንግዝ ፖለቲካዊና አፓርታዳዊ ትብታባቸው ስለቀፈደዱት እንጂ “አናውቅም፣ ቂሎች ነን” ማለት አይደለም።

ለማንኛውም በተሰባበረ እንግሊዝኛ ማውራት ቢፈቀድልኝ እንዲህ እላለሁ - What exists there, what we have in Eritrea, is an antidotal bunch of zombies used by EPLF to smother any move that tries to liberate Ethiopia from the yoke of TPLF and its masters; the souls of thousands, if not millions, of especially Amharic speaking people who lost their lives there in unwisely trusting those zombies and their lunatic master , Isayas Afeworki, in the past 26 years are fresh examples. As a matter of fact, and to the best of my little knowledge too, Ethiopia’s freedom or any positive opportunity for that matter has never come from the North; rather, the North has been the source of her suffering and eternal cries and tears thereof due to the time bomb her enemies buried. The atrocities being carried out by both EPLF and TPLF are the extension of the international mega project designed by ‘the lords of poverty’ few centuries back to destroy one of the greatest nations on planet Earth. But we have to realize that every morning has its own evening as every childhood has its own old age. It is a matter of time. We are nearing, I think, to see the final scene of the tragic drama composed by the West which has been performed by both EPLF and TPLF in the stages of theatrical Ethiopia. God will bless this nation abundantly very soon.

በጣም ይቅርታ። ወዳልፈለግሁት አቅጣጫ ነጉጄ ጊዜያችሁን በከንቱ አባከንኩ። እናላችሁ ከነዚህ ጓደኞቼ አንዱና ከኤርትራ የመጣው እዚያ ስለመሸጉት “ነፃ አውጪዎቻችን” እንዲህ አለን፤ “ ማንም ተቃዋሚ ነኝ ባይ ስትፈልግ በቁጥር ጥራው፤ ስትፈልግ ደግሞ በቃላት ጥራው፤ ካልፈለግህም ደግሞ በጎሣና በነገድ ጥራው የሁሉም እዚያ መገኘት ዋና ዓላማ የወዲ አፈወርቂ መጫወቻ ካርድ ሆኖ ማገልገል ነው፤ ሁሉም ሰው ይህን በደምብ ያውቃል። እንዲያውም ሕዝቡም መንግሥትም ‹አይትቅትሎ አይትህድኖ” እያለ ነው የሚቀልድባቸው። ‹አትግደላቸው አታድናቸው› ማለት ነው። እግር አውጥተው እንዲሄዱ አይፈቀድላቸውም፤ እንዲጠፉም አይፈለግም። ወያኔን የሚያስፈራራባቸው ቅን ታዛዦቹ ናቸው። ምንም ዓይነት መብት ደግሞ የላቸውም። የኤርትራ ባለሥልጣኖች የፈለጉትን ነገር ያሠሯቸዋል - ወላ ኃላፊ በለው ተራ ተዋጊ በለው የሚታዘዙት ወይ የሚዘወሩት በኤርትራ ባለሥልጣኖች ነው። ለዚህም እኮ ነው መኖራቸውን በሚዲያ ከማስማት ውጪ አንድም ፍሬ ያለው ነገር ሠርተው የሕዝቡን ቀልብ ሊገዙ ያልቻሉት፤ አሁን አሁንማ እናንተም እየረሳችኋቸው መሰለኝ። ኢሳይያስ በኢትዮጵያ ከወያኔ ሌላ አስተሳሰብ ያለው መንግሥት እንዲመጣበት በጭራሽ አይፈልግም። ከወያኔ የሚሻል መንግሥት እንደማይመጣለት የኤርትራ መንግሥት በደንብ ያውቃል። ሌላ መንግሥት ቢመጣ ብዙ ጣጣ ሊያመጣ ይችላል። የወደብ ነገር አለ። የሕዝብ ስደትና ፍልሰት አለ። የዘመዳሞች እዚያና እዚህ መኖር አለ። የሥልጣን ጉዳይ አለ - የአምልኮት ያህል የሚሰገድለት ሊያውም። በነዚህና በሌሎች ተያያዥ ምክንያቶች የተነሣ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት ኢሳይያስ እንደጦር ነው የሚፈራው። አበደም ሰከረም አሁን እንደልቡ ኤርትራን በፈለገው አቅጣጫ እንደጋሪ ፈረስ እየነዳ ነው - ለይምሰል ያህል እንኳን ምርጫ ብሎ ነገር በኤርትራ አይታወቅም። ለገዛ ሕዝቡ የሚጨክን ዐውሬ እንዴት በጠላትነት ፈርጆ 30 ዓመታት የተዋጋውን ሕዝብ ለነፃነት ሊያበቃ ይችላል? ሞኞች ናችሁ እንዴ? ጥቂት አታስቡም? እዋይ! …”

ብዙ ነገር አጫወተን። ሁሉንም መናገር አይጠቅም ይሆናል፤ መነገር የማይኖርበትም ሊሆን ይችላል።

ግን ተስፋችን ማን ነው? ከወዴትስ ነው? ብለን እንጠይቅ። ተስፋችን ያለው በፈጣሪ እጆች ውስጥ ነው። ከሰው ብዙ ጠብቀን አልሆነልንም። ኢዮብ በቁስል በነፈረበት የመከራ ሰዓቱ ተስፋውን ያደረገው በእግዚአብሔር ነው። ዳንኤል በሰውኛ አቅሙ ከአንበሣ ጋር ታግሎ ማሸነፍ አይችልም - ከአንበሣው መንጋጋ ያወጣው ታዲያ የሚያምነው እግዚአብሔር ነው። ሦምሶን በአህያ መንጋጋ መቶዎችን የረፈረፈው በእግዚአብሔር ኃይል ነው። ሠለስቱ ደቂቅ ከእሳት የወጡት የእግዚአብሔር ቀኝ መልአክ በሆነው በቅዱስ ገብርኤል ረድኤት ነው። አፎምያን በቅዱስ ሚካኤል አማካይት ከዘንዶ አፍ ያዳነ እግዚአብሔር ነው። ከሁሉም ደግሞ ሁሉንም ሀብትና ንብረቱን ቤተሰቡን ጭምር አጥቶ እንደኢትዮጵያ በቁስል ነድዶ መለመላውን ቀርቶ የነበረው ኢዮብ በዕጥፍ ድርብ ፀጋ የተሞላው በእግዚአብሔር ነው። … ለርሱ የሚሣነው የለም።

በድጋሚ እንጠይቅ። እኛስ ረዳታችን ማን ነው? ረዳታችን ኢትዮጵያን ጥሎ የማይጥላት የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ነው። ተስፋችን እርሱና እርሱ ብቻ ነው። እርሱ ፊቱን ሲመልስልን የጨለመው ይነጋል፤ የተበጠሰው ይቀጠላል፤ የተዘጋው ይከፈታል፤ የተበተነው ይሰበሰባል፤ የደነቆረው ይማራል፤ የራቀው ይቀርባል። …

አሁን ግን ምንም የለንም። ተቃዋሚም የለንም። ራስ ወዳድና ከሕይወት ተሞክሮ መማር የማይችሉ ደናቁርት ተቃዋሚ ተብየዎች እዚህና እዚያ ቢኖሩም ለነሱ አልተፈቀደላቸውምና ከድጥ ወደ ማጥ እንደዓሣማ ከመንደባለል በስተቀር ፍሬ ያለው ነገር ሲሰሩ ማየት አልቻልንም - ነገሩ ሁሉ “ከዝንጀሮ ቆንጆ” እንዲሉ ነው። ከሆዱ ያለፈ ሰው ፈጣሪ ሲሰጠን፤ ለሆዱ ከመጨነቅ ባለፈ ማሰብ የሚችል ሙሤ ሲሰጠን፤ ከቦርጩ ባለፈ ሩቅ የሚመለከት ሰው ሲልክልን ያኔ ኢትዮጵያ ከሞተችበት ትነሳለች። አሁንማ የሃይማኖት አባት የለንም። ሁሉንም እነሱ ተቆጣጥረውታል። ቤተ ክርስቲያንን የሚፈነጭባት የበግ ለምድ የለበሰ ምድረ ተኩላና ቀበሮ ነው። ፖለቲካችን ከሀገራችን ጠላቶች ጋር ተቆራኝቶ ለጥፋታችን እንጂ ለልማታችን ሲሰራ አይታይም። ግም ግምኛ ሆነን ለተመልካችም ሳናስጠይፍ አልቀረንም። ከሞቶች ሁሉ አስቀያው ሞት ደግሞ የቁም ሞት ነው። የቁም ሞት ለቀብር አይመች፣ ለአስተዛዘን አይመች፣ ዕድር አይገባለት፣ … ችግር ነው።

ተቃዋሚ አፍ የለህምና ዝም በል። ዝምታ ሁሉ ወርቅ ባይሆንም አንዳንዴ አለመናገር ከመናገር የሚበልጥበት ጊዜ አለ። ሁሉ ነገር ታወቀ። ወደፊት ደግሞ ገና ብዙ ነገር ይታወቃል። ማን ለዚህች አገር ደማ? ቆሰለ? ማን ሞተ? ማን እያታለለ ንጹሓን ዜጎችን ለከፋ አደጋ አጋለጠ? ማን ለምን ምን አደረገ? ማን ነው አጭበርባሪና አታላይ? ማን ነው የጠላት አሽከር? ማንስ ነው የድርጎ ወይም የመቅቡጥ ባሪያ? የትኛው ዜጋ ነው በየትኞቹ ጎሣዎችና ነገዶች ላይ ዘመቻ ከፍቶ/አስከፍቶ ዕልቂት የፈጠረ? …. ብዙ ጥያቄዎች አሉ። ጊዜ የሚመልሳቸው ጥያቄዎች ናቸው። የደፈረሰ ይጠራል። የወጣም ይወርዳል - የወረደም ይወጣል። ጊዜ ወርቅ ነው፤ በርግጥም ጊዜ መስታወት ነው። ሁሉን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። አሥርና ሃምሳ ዓመት በተቃዋሚነት ተሰልፎ ከወሬና ከአሉቧልታ በዘለለ፣ ከስድብ ፋብሪካ መክፈት ባለፈ ምንም ያልፈየደ ሁሉ ጊዜው ሲደርስ እንደ አራሙቻ ተጠራርጎ ከቢጤዎቹ ጋር ወደሚገባው የታሪክ መዝገብ ቤት ይጣላል። እንዲህ ነበር፤ እንዲሁም ይሆናል። ጊዜው የሀገራዊ ሙሾና የትርምስ ቢሆንም አንድ ዘፈን መጋበዝ ሳይኖርብኝ አይቀርም። እኔ ልጀምረውና ሙሉውን ክሊፕ ከስቱዲዮ ይለቁላችኋል።

እንዲህ ጨሶ ጨሶ የነደደ እንደሆን፤

ያመዱ ማፍሰሻ ሥርፋው ወዴት ይሆን።

ፍቅር ያዘኝ ብለሽ አትበይ ደምበር ገተር፤

እኛም አንድ ሰሞን እንዲህ አርጎን ነበር።

ለገምቢ አስተያየት - This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!