Tsion Girma, journalist
ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ

ለቅጣት ውሳኔ ነገ ተቀጠረች

5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስራ እንድታድር ተደረገ

Ethiopia Zare (ሰኞ ጥቅምት 24 ቀን 2001 ዓ.ም. November 3, 2008)፦ የቴዲ አፍሮን ችሎት እንዲዳኙ ተመድበው የነበሩትን ዳኛ የአባት ስም በመሳሳትዋ ተከስሳና ታስራ የነበረችው ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ ዛሬ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት ለአራተኛ ጊዜ ቀርባ ጥፋተኛ የተባለች ሲሆን፤ የቅጣት ውሳኔ እስኪሰጣት በእስር እንድትቆይ ተደረገ።

 

እንቢልታ ጋዜጣ በቅጽ 1 ቁጥር 041 የመስከረም 23 ቀን 2001 ዓ.ም. ዕትሙ ”የቴዲ አፍሮን ጉዳይ የሚያስችሉት ዳኛ ከችሎት ተነሱ” በሚል ርዕስ ባወጣው ዜና ላይ የዳኛውን የአባት ስም በመሳሳቱ ዓቃቤ ሕግ ”የሐሰት ወሬ በመፃፍና በማሰራጨት በህዝብ ዘንድ ጥርጣሬ እንዲስፋፋ በማድረግ” በሚል ጥቅምት 13 ቀን ክስ መመስረቱ አይዘነጋም። የተመደቡት ዳኛ መሐመድ ዑመር ሆነው ሳለ፣ ጋዜጣው ”ዳኛ መሐመድ አሚን ሳኒ” በማለቱ ሲሆን፣ ዳኛ መሐመድ አሚን ሳኒ ደግሞ በቅንጅት መሪዎች ክስ ላይ ከሦስቱ ዓቃቢያነ ሕጎች አንዱ የነበሩ ናቸው።

 

የጋዜጣው አሣታሚና ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ በዛሬው ዕለት ካለጠበቃ ነበር የቀረበችው። ዳኛው አብርሃም ተጠምቀ ”ክሱን ከጠበቃ ጋር ሆኜ አስተያየት እንስጥበት ብለሽ ተቀጥሮ ነበር፤ አስተያየት መስጠት አልቻላችሁም። የመከላከያ ማስረጃ እንድታቀርቡ ተጠይቃችሁ። የመከላከያ ማስረጃ በተጠየቃችሁበት ችሎት ’የክስ ማስረጃውን ተመልክቶ ውሳኔ ይስጠን’ ብላችሁ ነበር። ... ” በማለት በጥቀምት 13፣ በጥቅምት 18 እና በጥቅምት 20 ተከሳሽዋ ተቀጥራ ችሎት ቀርባባቸው በነበሩት ቀናት የነበረውን ችሎት አስታውሰዋል።

 

በመቀጠልም ዳኛው ተከሳሽዋ ለችሎቱ ”ሆን ብዬ አይደለም፤ በስም ስህተት የመጣ ነው” ማለትዋን አውስተው፤ ”መከራከር የምትችይበት ሁኔታ ላይ አልነበርሽም፣ ያቀረብሽውም የመከላከያ ማስረጃ ባለመኖሩ ችሎቱ የጥፋተኝነት ውሳኔ አቅርቧል። ጥፋተኛ ነሽ!” በማለት ውሳኔውን አስተላልፈዋል።

 

ከዚያም በመቀጠል ዓቃቤ ሕግ የቅጣት አስተያየት እንዳለው ዳኛ አብርሃም ተጠምቀ ጠይቀዋል። ዓቃቤ ሕጉም ”ተከሳሽዋ በተደጋጋሚ ጥፋት ሠርታ አታውቅም። በመሆኑም አስተማሪና ቀለል ያለ ቅጣት ይሰጣት” በማለት የቅጣት አስተያየቱን ሰንዝሯል።

 

ጋዜጠኛ ጽዮን በበኩሏ ”የተከሰስሁበት ክስ በስም ስህተት የመጣ ነው። ከዚህ በፊትም እንደመከላከያ አቅርቤው ነበር። በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ለረዥም ዓመታት ስሠራ በምንም ዓይነት በዘገባዎቼ ላይ ማረሚያ የሚፈልጉ ስህተቶች ያልሠራሁ መሆኔ ታይቶ፤ ከ15 በላይ ሠራተኞችን የማስተዳድርና የቤተሰብ ኃላፊነቴ ታውቆ ቀለል ያለ ቅጣት እንዲሰጠኝ እጠይቃለሁ” ስትል ቅጣቱ እንዲቀልላት ችሎቱን ጠይቃለች።

 

ዓቃቤ ሕግ ጋዜጠኛዋን የከሰሰው ”የወንጀለኛ ሕግ ቁጥር 431ሀ እና 486ለ”ን በመጥቀስ ሲሆን፣ በተጠቀሰው አንቀጽ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀለኛ ሕግ ቁጥር 431ሀ እና 486ለ፤ ”በማናቸውም አይነት ማሳጣት ወይም ሌላ ዘዴ ጥርጣሬን ያስፋፋ፣ ጥላቻን ያነሳሳ ወይም የኃይል ድርጊት ወይም የፖለቲካ የዘር ወይም የኃይማኖት ኹከት የቀሰቀሰ እንደሆነ፤ በቀላል እስራት ወይም በመቀጮ ወይም ወንጀሉ ከባድ በሆነ ጊዜ ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል” የሚል እንደሆነ ከዚህ በፊት መዘገባችን አይዘነጋም።

 

ችሎቱም የግራ ቀኙን የቅጣት አስተያየት ተመልክቶ በአዳሪ ለቅጣት ውሳኔ ለነገ ማክሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2001 ዓ.ም. በመቅጠር፤ ጋዜጠኛዋ በችሎት ፖሊሶች ወደ ማረፊያ ቤት እንድትቆይ አዟል።

 

በዚህም መሠረት ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ በፖሊስ ታጅባ ወደ 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ተወስዳ ታስራ እንድታድር ተደርጓል። 5ኛ ፖሊስ ጣቢያ በልደታ ክፍለ ከተማ የሚገኝ ሲሆን ሚሸል ኮስት አካባቢ ይገኛል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!