የቴዲ ክስ - እኛ ሁላችንም ነው የተፈረደብን
ግርማ ካሣ (ከቺካጎ)
ሚያዚያ 8 ቀን 2000 ዓ.ም. ነበር ዝነኛው የኪነት ሰው ቴዎድሮስ ካሳሁን “ሰው ገጭተሃል” በሚል ክስ ነው ወህኒ የወረደው። እስር ቤት በገባ በስምንት ቀኑ “በርግጥ መንግሥት መረጃ ኖሮት ነውን? ወይስ ቴዲ የገዢው ፓርቲ ሰዎች ህዝብ እንዲሰማ የማይፈልጉትን መልዕክቶች በማቅረቡ? በርግጥ ሕግ የበላይ መሆን ስላለበት ነውን? ወይስ ሕግን እንደ ዱላ ተጠቅሞ የተቀየሙትንና የማይስማማቸውን ሰው ለማፈንና ለማስወገድ ስለተፈለገ ነውን? በኢትዮጵያ ፍትህ እንዲሰፍን፣ ሁሉም በሕግ ፊት እኩል ስለሆኑ ነውን? ወይስ በኢትዮጵያነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት?” የሚሉ ጥያቄዎችን በመጠየቅ መልሱን በቅርብ የምናየው እንደሆነ ገልጨ ነበር።
ቴዲ አፍሮ ከታሰረበት ቀን ጀምሮ፣ ሁልጊዜ በፀሎቴ እርሱንና እንደርሱ በግፍ የታሰሩ ወገኖቻችን ሳስባቸው ቆይቻለሁ። ኢትዮጵያ ዛሬ የተሰኘው ድረ ገጽ ብቃታዊ የሆኑ ዘገባዎችን በየጊዜው ለአንባቢያኑ ያቀርብ ስለነበረም በቅርብ የዚህን ወጣት የፍርድ ሂደት የመከታተል ዕድል አጋጥሞኛል።
በወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሰረት አንድን ዜጋ ጥፋታኛ ብሎ ለመፈረጅ ዓቃቤ ሕጉ ጥርጣሬ በማያስነሳ መልኩ ተጨባጭ መረጃዎቹን ማቅረብ አለበት። ፈረንጆች “ጊልቲ ቢዮንድ ሪዝናብል ዳውት” ይሉታል። አሁን ግን ያየነው ዳኛው አመዛዝኖ መፍረድ ሲገባው ከዓቃቤ ሕግ በላይ የዓቃቤ ሕግን ሥራ ሲሠራ ነው። በዓቃቤ ሕጉ የቀረቡት መረጃዎች የውሸት እንደሆኑ የሚያሳዩ ማረጋገጫዎች ቢቀርቡም ዳኛ ተብዬው እውነትን ለማወቅ ፍላጎትና የዳኝነት ብቃት ስለሌለው የፍርድ ሂደቱን ሲያዛባና ሲገለባብጥ ነው ያየነው። አንድ በሉ።
በዚህ ፍርድ ሂደት ውስጥ የቴዲ ጠበቃ የነበሩት አቶ ሚሊዮን መታሰራቸውን ማስታወስ እፈልጋለሁ። እስቲ አስቡት … ተከሳሽ በውሸት ክስ ተከሶ፣ ጠበቃው ደግሞ ወደ ወህኒ ሲወርድ … ይህ ብቻ አይደልም፤ ከቴዲ አፍሮ ጋር በተገናኘ በርካታ ጋዜጠኞችም የግፍ በትር ደርሶባቸው እስር ቤት ወርደዋል። ሁለት በሉ።
እንግዲህ በዚሁ ሁሉ ውስጥ ምንኛ የፍርድ ሂደቱ አሳፋሪ እንደሆነ ነው ለማየት የቻልነው። ቴዲ አፍሮ ጥፋተኛ መሆኑን በተጨባጭ የሚያሳይ አንድም ነገር አላየሁም። ስለሆነም ቴዲ ጥፋተኛ ነው ብዬ ለመናገር አልችልም።
በተቃራኒው ግን፣ መረጃ ስላላየሁ ጥፋተኛ አይደልም ብዬ የማምነው፣ ቴዲ ባላጠፋው ጥፋት “ወንጀለኛ ነው” ብለው ዳኛው እንደፈረዱ የሚገልጽ ዜና በየድረ ገጹ ወጥቶ አነበብኩኝ።
ይህ ወጣት ጥፋተኛ ሳይሆን ጥፋተኛ መደረጉ ደግሞ “ለምን?” የሚል ጥያቄ ያስነሳል። “ለምን?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመመለስ ስንሞክር ደግሞ በበርካታ ኢትዮጵያዊያን አዕምሮ ውስጥ ወዲያው የሚመጣው “ቴዲ ባቀነቀናቸውና በኢትዮጵያ ቴሌቭዥንና ራዲዮ እንዳይቀርቡ በታገዱት አንዳንድ ዜማዎቹ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ስለተናደዱ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ስለፈለጉ ነው” የሚል ነው።
እንግዲህ ከስምንት ወራት በፊት የቴዲን መታሰር በተመለከተ “በኢትዮጵያዊነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ነውን?” ብዬ ለጠየቅሁት ጥያቄ መልሴ “አዎን! በኢትዮጵያዊነት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ነው!” የሚል ነው። በቴዲ አፍሮ ክስ ቴዲ አፍሮ ብቻ ሳይሆን የተከሰሰው “ኢትዮጵያዊነት፣ ፍቅርና አንድነት” ናቸው የተከሰሱት። እኛ ሁላችንም ነው የተከሰስነው።
ቴዲ አፍሮ ጥፋተኛ ተደርጎ ሲፈረጅ ደግሞ በእኛ ሁላችንም ላይ ነው የተፈረደው። ኢህአዴግ በቴዲ አፍሮ ላይ የወሰደው እርምጃ ቴዲ አፍሮን የፍትህ፣ የነፃነትና የኢትዮጵያዊነት ምልክት አድርጎታል። አሁን የቴዲ ክስ የአንድ ሰው ክስ አይደለም። የአንድ ሰው ጥያቄ አይደለም። የፖለቲካ ክስ ሆኗል። የህዝብ ጥያቄ ሆኗል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ብዙ ችግሮች አሏት። አብረን በጋራ ተያይዘን ብዙ መሥራት ሲጠበቅብን እንደገና የሚከፋፍለንና ወደ ኋላ የሚመልሰንን ነገር ለምን ኢህአዴግ እንደሚያመጣ፣ አመራሮቹም ማስተዋል ለምን እንደሚጎድላቸውና ለምን ግትር እንደሚሆኑ አይገባኝም። ይልቅስ ለነርሱም ለሁላችንም የሚበጀው መግባባቱና አብሮ መሥራቱ ነበር። ከህዝብ ጋር ተቀራርቦ ህዝብን ሳያስቀይሙ መንቀሳቀስ ጥበብና መልካም ፖለቲካ አድርጌ ነው የማየው። በቴዲ ዙሪያ እያየነው ያለ ነገር ቢኖር ግን ኢህአዲግ አብዛኞቻችን ወደማይፈለገው አቅታጫ እየገፋን እንዳለ ነው።
እንደዚያም ሆኖ ግን አሁንም ነገሮችን ለማስተካከል ይቻላል የሚል ግምት አለኝ። አሁንም ኢህአዴግ ውስጥ ጥሩ ልብ ያላቸው ዜጎች እንዳሉ አስባለሁ።
“አይጋ ፎረም” የተሰኘው ድረ ገጽ ላይ በቴዲ ክስ ዙሪያ የቀረቡትን አስተያየቶች ሳነብ በርካታ ኢህአዴግን የሚደግፉ በፍርድ ቤቱ ውሳኔ እንደ እኔው የተናደዱና ቴዲ አፍሮ በአስቸኳይ እንዲፈታ የሚጠይቁ እንዳሉ አይቻለሁ። ይህ አበረታች ነው።
ኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ከፍተኛ አመራር አባላት ከሁሉም አቅጣጫ (ከነርሱም ደጋፊዎች መካከልም) እየመጡ ያሉትን ተቃውሞዎችና ቁጣዎች ከግምት በማስገባት የሚከተሉትን እርምጃዎች በአስቸኳይ እንዲወስዱ በአክብሮት እመክራለሁ።
• በአስቸኳይ ዳኛ ልዑል የሚመሩት ችሎት እንዲፈርስና ዳኛውም ዳኝነትን ያዋረዱ በመሆናቸው እንዲባረሩ፣
• ቴዲ አፍሮም ሆነ ማንም ሰው ከሕግ በላይ ስላልሆነ ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ጥፋተኛ አለመሆኑን የሚያረጋገጠበት፣ ጥራትና ብቃት እንዲሁም ገለልተኝነት ባላቸው ዳኞች የሚመራ አዲስ ችሎት እንዲቋቋም ማድረግ፣ …
ኢህአዴግ ከላይ የተጠቀሱትን ቢያደርግ የቴዲ አፍሮ ክስ በኢትዮጵያዊነት ላይ ያነጣጠረ እንዳልሆነ ተደርጎ እንዲወሰድ ማድረግ ይችላል። በዚሁ አጋጣሚ የተበላሸውንና የበሰበሰውን የፍርድ ሥርዓት ለማሻሻል መልካም አጋጣሚ ይፈጥርለታል።
እግዚአብሔር በግፍ የታሰሩትን የሚያይ አምላክ ስለሆነ ለቴዲ አፍሮም ብርታቱንና የመንፈስ ጥንካሬውን ይሰጠው። እኛም በሥጋ ነፃ ሆነን የምንንቀሳቀስ፣ ከታሰርንበት ፍርሃት፣ ዝምተኝነትና ራስ ወዳድነት ወጥተን ለቴዲ አፍሮና እንዲሁም በግፍ ለታሰሩ ወገኖቻችን ያለንን ድጋፍ በተጨባጭና በሥራ ለማሳየት እንድንችል እግዚአብሔር ጽናቱንና ብርታቱን ይስጠን! - አሜን!!! መናደድ ብቻ አይበቃም። ሥራ ያስፈልጋል።
ግርማ ካሣ (ከቺካጎ)
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ኅዳር 24 ቀን 2001 ዓ.ም.