ኤፍሬም ማዴቦ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

በ1999 ዓ.ም. በተደረገው ህዝባዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ ይበጁኛል ብሎ የመረጣቸውን የህዝብ ተወካዮች በግፍ አስሮ ለሁለት ዓመታት ካሰቃየ በኋላ በይቅርታ ተለቃችኋል ብሎ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያሾፈው የመለስ ዜናዊ መንግሥት ከሰሞኑ ውዱን የኢትዮጵያ ልጅ ቴዎድሮስ ካሳሁንን (ቴዲ አፍሮን) ካለ በቂ ምክንያት አስሮ፣ ካለ በቂ ማስረጃ ጥፋተኛ ነህ ብሎ ፈርዶበታል።

 

ፍትህ በነገሠባቸውና ፍርድ በማስረጃ ተደግፎ በሚፈረድባቸው ሀገሮች ውስጥ በቴዲ አፍሮ ላይ የቀረበው የፖሊስና የዓቃቤ ሕግ ማስረጃ አንድን ሰው እንኳን በፍርድ ሊያሳስር ክስ ለመመስረትም በቂ አይደለም። ከሳሽና ዳኛ ሁለቱም አንድ በሆኑበት ሀገር ግን ዜጎችን ለእስር የሚያበቃው ጥፋት ሳይሆን መልካም ሥራ፣ ውሸት ሳይሆን እውነት በመሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ በመልካም ሥራውና እውነትን ሳይፈራ በመናገር የታወቀው ሸመንደፈሩ ቴዎድሮስ ካሳሁን እንደ ጥላሁን ግዛው፣ እንደ በዓሉ ግርማና እንደ አበራ የማነአብ የግፈኞች ሥርዓት ሰለባ ሆኗል።

 

የዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር እርዳው አሻግሬ ለፍርድ ቤት በሰጡት የምስክርነት ቃል የሟች አስከሬን ለምርመራ ወደ ሆስፒተል የገባው ጥቅምት 22 ቀን 1999 ዓ.ም. መሆኑን ሲናገሩ፤ ሌላው የሆስፒታሉ ዶክተር (ዶ/ር ካሳሁን አደም) ደግሞ የሟች አስከሬን ለምርመራ ወደ ሆስፒታል የገባው ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም. ነው ሲሉ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል።

 

ስለፍርድ ቤት አሠራር ትንተና የመስጠት ችሎታ የለኝም፤ ሆኖም እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ታዳጊ ሀገሮች ውስጥ ሰው በአደጋ ሲሞት (በተለይ ደኅና ዘመድ የሌለው ሰው) አስከሬኑ በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ላይላክ ይችላል፤ ነገር ግን ኢትዮጵያም ውስጥ ሆነ ሌላ ሀገር አንድ ሰው በዓመት ሁለቴ አይሞትም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ጥቅምት 22 ምሽት በመኪና ተገጭቶ ለሞተ ሰው ጥቅምት 23 ምሽት ከውጭ ሀገር የገባ ሰው ተጠያቂ ሊሆን አይችልም።

 

ኢህአዲግ እያጠረ የመጣውን የሥልጣን ዘመኑን ለማስረዘም ከሚወስዳቸው የቀቢፀ ተስፋ እርምጃዎች አንዱ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚወዳቸውንና የሚያከብራቸውን ሰዎች ሆን ብሎ ሰበብ እየፈለገ ማሰር ነው። ዛሬ የኢትዮጵያ ህዝብ ከሚወዳቸውና በኢህአዲግ እስር ቤት ከሚንገላቱት ታዋቂ ኢትዮጵያውያን አንዱ ቴዲ አፍሮ ነው። የቴዲ አፍሮ ብቸኛ ወንጀል እውነትን መናገሩ መሆኑን እንኳን ወዳጆቹ ነገር ቶሎ የማይገባቸው የኢህአዲግ ጀሌዎችም ካወቁ ውሎ አድሯል። ኢህአዲግ ቴዲን ያሰረው የዚህን ወጣት ድምፃዊ ሥነ-ልቦና የሰበረ፣ ልበ-ሙሉነቱን የሰለበና የህዝብ ተወዳጅነቱን ያደበዘዘ መስሎት ነው።

 

ሰሞኑን በመገናኛ አውታሮች በተደጋጋሚ እንደተገለፀው የቴዲ አፍሮ ጉዳይ የመጨረሻውን ውሳኔ ከማግኘቱ በፊት በሽምግልና ስም ቴዲ ጥፋተኛ ነኝ ብሎ እንዲፈርም ከፍተኛ ጥረት ተደርጎ ነበር። ይህ ሁሉ ውጣ ውረድ ቴዲን ከእስር ለማስፈታት ወይም ይቅር ለማለት ሳይሆን ቴዲ ከእስር ቢፈታ እንኳን ከተፈታ በኋላ፣ የሚኖረውን ኑሮ የፍርሃትና የድንጋጤ ኑሮ እንዲሆን ለማድረግ ነበር። ሆኖም የቴዎድሮስ ካሳሁን ቆራጥነትና ልበ-ሙሉነት በኢህአዲግ ማስፈራራትና የወሬ ቱማታ የማይሰበር ዓለት ሆኖ ስለተገኘ ፍርደ ገምድሉ ዳኛ ልዑል ገ/ማርያም ንፁኁን ዜጋ ቴዲ አፍሮን ወንጀለኛ ነህ ብለው ፈርደውበታል። ዳኛ ልዑልና አለቃቸው አቶ መለስ አልገባቸውም እንጂ በቴዲ አፍሮ ላይ የተወሰነው ውሳኔ የእስር ቤት ለውጥ ነው እንጂ ቴዲን እስር ቤት የሚያስገባ ውሳኔ አይደለም።

 

የሰሞኑ የዳኛ ልዑል ውሳኔ ቴዲ አፍሮን ከሰፊው እስር ቤት ወደ ጠባቡ እስር ቤት ይሰደዋል እንጂ ቴዲም ሆነ የተቀረው የኢትዮጵያ ህዝብ በኢህአዲግ ተፈርዶበት እስር ቤት ከገባ 17 ዓመታት ተቆጥረዋል። የህዝብ ጠላት የሆነው መለስ ዜናዊ መሣሪያም ቢሆን ተጠቅሞ ቴዲ አፍሮን ከኢትዮጵያ ህዝብ መነጠል ይችል ይሆናል፤ ኢትዮጵያዊነትንና ቴዲን መነጣጠል ግን በፍፁም አይችልም።

 

እጅግ አሳሳችና አደገኛ ከሆኑ የኢህአዲግ ባህሪዎች ውስጥ አንዱ እንደ እስስት በፍጥነት መልኩን መቀያየር መቻሉና አንዳንዴ የዋህ ዜጎችን ብቻ ሳይሆን አንቱ የተባሉ ምሁራንን ጭምር ግራ ማጋባት መቻሉ ነው። ኢህአዲግ ቂመኛነቱንና የጥላቻ ፊቱን በይቅርታ ሸማ ሸፋፍኖ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማታለል ተደጋጋሚ ሙከራዎች አድርጓል። የይቅር ባይነት መንፈስ በግለሰብ ደረጃም ሆነ ወይም በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በሀገሮች ደረጃ ያለውን የተበጠሰ የግንኙነት ሰንሰለት የሚቀጥል መንፈስ ነው።

 

“ይቅርታ” ኢየሱስ ክርስቶስ እራሱ ያስተማረን ከልብ የሚመነጭ የፍቅርና የሠላም ምልክት እንጂ፤ ቂምን በሆድ ይዞ ለግብር ይውጣ ከአፋችን የሚወረወር የቃላት ድርድር አይደለም። የይቅርታ ትልቁ ቁም ነገር በሌሎች ይቅር መባላችን ብቻ ሳይሆን እኛ ሌሎችን ይቅር ማለት መቻላችን ነው። ይቅርታ የተፈፀመ ጥፋትን ወይም ያለፈ በደልን አይቀይርም። የኢህአዲግ መንግሥትም ሆነ ሽምግልና እያለ የሚጋልብባቸው ፈረሶቹ የሚገባቸው ከሆነ ይቅርታ ይቅር ባይና ይቅርታ ተቀባይ ስላለፈው በደል ሳይሆን ወደፊት ስለሚኖራቸው መልካም ግዜ በጋራ እንዲያስቡ የሚያደርግ ኃይል ነው እንጂ አንደኛውን አሳብጦ ሌላኛውን ጫማ የሚያስም የበቀል መወጫ አይደለም።

 

ዛሬ በወርቃማ ፈገግታው ቀልባችንን ስቦ ቁም ነገርን በዜማ አስውቦ በኢትዮጵያ አደባባዮች ላይ ያለ ጠብታ ፍርሃት እውነትን የተናገረው ቴዲ አፍሮ በእውነት ጠላቶች ተከስሶ፣ በውሸት ምስክሮች ተመስክሮበትና ወንጀለኛ ነህ ተብሎ የግፈኞችን ፍርድ በመጠባበቅ ላይ ይገኛል። አዎ! ቴዲ ታሰረ ሲባል ለአንድ ሰሞንም ቢሆን እውነት ትርቀናለችና ብዙዎቻችን አዝነናል፣ ነዶናል፣ አምርረናል፤ ሆኖም ሀገራችን ኢትዮጵያ ለእውነት የሚሞቱ ጀግኖች ዘወትር የሚፈጠሩባት ሀገር ስለሆነች ሺ-ልዑሎች ተሰባስበው እያሰሩ ቢውሉና ቢያድሩ የኩነኔያቸው ብዛት የእጃቸውን ያሳቅፋቸዋል እንጂ እውነትን ማሰር አይችሉም። ኢትዮጵያውያን በያለንበት የቴዲ ለእስር መብቃት ሊነደንና ሊቆጨን ይገባል፤ ሊያስገርመን ግን አይገባም። ሐቅና ፍትህ የኢህአዲግ ሥርዓት ገፅታዎች አይደሉምና ሊገርመንና ሊደንቀን የሚገባው ቴዲ በነፃ ተለቋል ቢባል ነበር።

 

የመለስ ዜናዊ መንግሥት ቴዲ አፍሮን ወንጀለኛ ነው ብሎ ለማሰር ከቆረጠ ቆይቷል። ባለፉት 6 ወራት በየችሎቱ የታዘብነው የእዩልኝ ትርዕት የኢህአዲግን ሴራ ለመሸፈን የተደረገ ጉድ ጉድ ነው እንጂ ኢህአዲግማ ቴዲን ወንጀለኛ ካደረገው ቆይቷል። የቴዲ ችግር እውነት መናገሩ ነው፤ የቴዲ ጥፋት በህዝብ መወደዱ ነው፤ የቴዲ ወንጀል ኢትዮጵያዊነትን መስበኩ ነው።

 

ባለፉት አምስት ዓመታት እኛ ኢትዮጵያውያን በተመሳሳይ የጋራ ሃሳቦች ዙሪያ ተሰባስበን አንድ ላይ በመቆም በሀገራችን ጉዳይ ሁሌም የምንተባበር ህዝቦች መሆናችንን አስመስክረናል። ከግንቦት 97ቱ ምርጫ በፊትና በኋላ፣ እንዲሁም የቅንጅት መሪዎች ሲታሰሩና ኢህአዲግ ሠላማዊ ዜጎችን ሲገድል ያሳየነው መተባበርና መደጋገፍ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው። መቼም የኢህአዲግ ጉድ አያልቅምና ይኼውና ዛሬም እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ንስኀ ግቡ እያለ በኢህአዲግ የሐሰት አደባባዮች “ጃ ያስተሰርያል” ብሎ የሰበከው ቴዲ አፍሮ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን “ሄሮድሶች” ታስሮ ወህኒ ቤት ተጥሏል።

 

ኢትዮጵያውያን በያለንበት ”በነ ሶሎሜ” ሳንቀደም ለዚህ የወጣትነት ሕይወቱን ለቸረን የእውነት መልዕክተኛ በጋራ ልንቆም ይገባል። ኢህአዲግና የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያካሄዱትን የሞት ሽረት ትግል በዓይናችን እያየን ከደሙ ንፁኅ ነን ብለን እንደ ጲላጦስ እጃችንን ብንታጠብ፤ እጃችን ከፈሰሰው ደም ለግዜው ቢነፃ እንጂ ልባችን ውስጥ የታተመው ክህደት ግን ምን ግዜም ቢሆን ሊነፃ አይችልም። ፍርድ ሲዛባ፣ መብት ሲረገጥና ህዝብ ሲበደል መሀል ቆሞ መመልከት አይቻልም። ጠላት ሲበረታ ከጠላት ጋር ሲሸነፍ ደግሞ ከህዝብ ጋር የሚቆም እሱ ከጠላቶች ሁሉ የከፋ ጠላት ነው። አንዳንዶቻችን የትግሉ ውጣ ውረድና ዋጋ የመክፋሉ ዕዳ ሲታየን “እኔ ብቻዬን የማደርገው የለም” እያልን ወደ ኋላ እናፈገፍጋለን፤ ሐቁ የሚታየንና የሚገባን ከሆነ ግን ሀገርን ያክል ትልቅ ነገር በጎርፍ ተጠርጎ ሲወሰድ በኃላፊነት የሚጠየቀው ወንዙ ብቻ ሳይሆን ወንዙ ላይ የወደቀው እያንዳንዱ የዝናብ ጠብታ ነው።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ