ተስፋዬ ገብረአብ

(አንዲት ቁራጭ “ወግ” ይዣለሁና እንደ መለስ ዜናዊ ቅንድባችሁን አሳምራችሁአንብቡኝ። “ጠቢቡ ሰለሞን” ለመሪያችን እንዳቀነቀነለት፣ “ውበት ቅንድቡ ላይ የፈሰሰለት - እውቀት ወደ አንጎሉ የዘለቀለት!” ተባለ። አልን! አስባልን! ይባላል! በምርጫው ዋዜማ አንድ ጓደኛዬ ዘንድ ቤቱ ሄጄ ሳለ፣

 

“ዘፈን ላሰማህ” አለና ከፈተልኝ።

 

በሳቅ ነው የፈነዳሁት።

 

ቀደምት የኢትዮጵያ መሪዎች እንዲህ አልተዘፈነላቸውም። መለስ ዜናዊ! ስለውበቱ ማማር የተዘፈነለት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ መሪ። ዳሩ ግን ስለ ቅንድቡ ውበት መዝፈን ለምን አስፈለገ? ለነገሩ ቅንድቡ ያምርበታል እንዴ? እንዲያውም ጃርት ነው የሚያስመስለው። የት ሃገር በተመረተ መነፅር አይተውት ይሆን ውበቱ የተከሰተላቸው? አዬ ሰለሞን! እንዲህ ሆኖ ቀረ?)

 

ዝኾነ ኮይኑ - ወሬዎች እንዲህ ቀጥለው ሰንብተዋል።

 

- ምርጫ 2002 ተካሄደ።

- ኢህአዴግ 99% አሸነፈ።

- ተቃዋሚዎች 99% ተረፈረፉ።

- ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ በጥቂት የድምፅ ልዩነት ለጥቂት ወደቁ።

- የፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ደጋፊዎች የምርጫ ከረጢት ሲሰርቁ ተያዙ።

- ኢንጂነር ሃይሉ አልሰማ ብለው ነው እንጂ፣ ህዝቡ “አንመርጥህምና አትድከም” ብሏቸው ነበር።

- ሰላማዊ ትግል አከተመለት። የዶክተር ብርሃኑ አማራጭ ልክ ነበር።

 

በዚህም ተባለ በዚያ ተቃዋሚዎች ሙልጫቸውን በመውጣታቸውና ወያኔ ፓርላማውን ብቻውን በመቆጣጠሩ በኔ በኩል ተስማምቶኛል። ይህ የበቀል ስሜት አይደለም። እነ ዶክተር ነጋሶ ፓርላማ ገብተው ወያኔን ከመጥቀም ባሻገር የሚያስገኙት አንዳችም ፋይዳ የለም ብዬ ስለማምን ነው። አሁን ትግሉ መልክ ይዞአል። የፓርላማው የማጭበርበሪያ አጎበር በመገፈፉ ኢህአዴግ ፓርላማውን ከኢሰፓ ፓርላማ ጋር ሙሉ በሙሉ አመሳስሎታል። ተቃዋሚዎች ወደዱም ጠሉም በአንድ ጎራ ለመሆን ይገደዳሉ።

 

“ወያኔ በ2002 ምርጫ ሙሉ በሙሉ ያሸነፈው ከቁጥጥሩ ውጭ በሆነ ሁኔታ ነው” የሚሉ የወያኔ ሰዎች አሉ። “እንዴት?” ሲባል፣ እንዲህ ያብራራሉ።

 

“ልደቱ፣ በየነ እና ነጋሶ ወደ ፓርላማው እንዲገቡ ይፈለግ ነበር። ከልምድ እንደታየው እነዚህ ሰዎች ለፓርላማው ቅመም እና ጌጥ ነበሩ። በለስላሳ ተቃውሞ የፓርላማውን ውይይት ያጣፍጡት ነበር። ስለዚህ ከላይ የተጠቀሱት ሶስቱ በምርጫው የወደቁት ባልተጠበቀ ሁኔታ ነው” ሲሉ ለማሳመን ይሞክራሉ።

 

አያይዘውም፣ “… በምርጫ 2002 ወደ ፓርላማው እንዳይገቡ በድርጅት ደረጃ ውሳኔ የተላለፈው ስዬ፣ ገብሩና አረጋሽ ላይ ብቻ ነበር። እነዚህ ሶስቱ የሚመረጡ ከሆነ ተሃድሶው ተቀለበሰ ማለት ስለሚሆን በማንኛውም መንገድ ድምፅ እንዳያገኙ መደረግ አለበት’ የሚል ጥብቅ መመሪያ ተላልፎ ነበር። ሌሎቹ ላይ ግን በራሳቸው ጊዜ ድምፅ አጊኝተው ይገባሉ ተብሎ ታስቦ ነበር” ሲሉ ያክሉበታል።

 

የወያኔ የውስጥ ሰዎች እንደሚሉት፣ ቀደም ሲል ኢህአዴግ ከተቃዋሚ ወገኖች ወደ ፓርላማ እንዲገቡ ሆን ብሎ ወንበር የሚለቅላቸው ግለሰቦች ነበሩ። ለአብነትም በድሩ አደምና ሻለቃ አድማሴ ዘለቀን ይጠቀሳሉ። ማብራሪያቸውን ሲቀጥሉም፣

 

“… በምርጫ 97 ባልተጠበቀ መንገድ ሁሉም ከቁጥጥር ውጭ ስለነበር፣ ሆን ተብሎ ወንበር የተለቀቀላቸው ዶክተር ነጋሶ ብቻ ነበሩ። በ2002 ምርጫ ልደቱ አያሌው ቡግና ላይ አሸንፎ እንዲገባ ይፈለግ ነበር። ስለሆነም ልደቱን ማሸነፍ የማይችል ደካማ ሰው ነበር የተመደበለት። ቡግና ላይ ልደቱ የተሸነፈው ያለአንዳች ማጭበርበሪያ ነው” ሲሉ ይሟገታሉ።

 

የሆነው ሆኖ ምርጫ 2002 ለወያኔ አስጊ ነበር ማለት አይቻልም።

 

ወያኔ ከምርጫ 97 በቂ ትምህርት ስለቀሰመ ጥሩ ዝግጅት አድርጎ ነበር። አንድ ዓመት የፈጀ የፖሊስ ስልጠና አካሂዶ 50 ሺህ የፌደራል ፖሊሶችን አስመርቆ ነበር። የፖሊስ ትጥቅ በግዢና በእርዳታ ከቻይና በስፋት አስገብቶአል። የጥይት መከላከያ ጃኬት፣ ጋዝና ውሃ መርጫዎች አስገብቶአል። የምርጫውን ሜዳም አደላድለውት ነበር። ቀዳሚው ርምጃ ብርቱካን ሚደቅሳን ማግለል ነበር። ከብርቱካን መታሰር በሁዋላ አንድነት ፓርቲን ለመከፋፈል ምቹ ሆኖ ተገኘ። የስዬ አብርሃ ወደ ግንባር መምጣትም “መድረክ” ጠንካራ ተቃዋሚ መስሎ እንዲታይ ያደረገ ሲሆን፤ በዚህም የመለስ ቡድን ተጠቃሚ ሆኖአል። መለስና ስዬ የሞት ሽረት ትንቅንቅ ያደርጋሉ ብሎ ተስፋ ያደረገም አልታጣም። የዋህ ፖለቲከኞች “ለስዬ እድል እንስጠው” ሲሉም ወትውተዋል። ስዬ ግዙፍ መስሎ እንዲታይ የመለስ ቡድን አስተዋፅኦ አድርጎለታል። ገና ከመነሻው ብርቱካን ባትታሰር ኖሮ ስዬ በዚህ ደረጃ መተወን ባልቻለ።

 

ግንቦት 15፣ 2002 ሃገራዊው ምርጫ ተካሄደ።

 

የአውሮፓ ህብረት እና የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ድርጅት ምርጫው ነፃና ፍትሃዊ እንዳልነበር ገለፁ። የአፍሪቃ አንድነት እንደለተለመደው ዘላበደ። የአህጉራችን ተወካዮች ቅንድባቸውን በጨው አጥበው፣ “ምርጫው እንደ ጋና ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ነበር” ሲሉ ገለፁ።

 

ማክሰኞ እለት ህዝቡ መስቀል አደባባይ ወጥቶ፣ “ድምፅ ይከበር” ስለማለቱ ዜና ሰማን። መለስ መስቀል አደባባይ ወጥቶ፣ ጥይት የማይበሳው መስታወት ውስጥ ተሸሽጎ ባደረገው ንግግር ቀጣይ አካሄዱን የሚጠቁም ፍንጭ ሰጠ። (ድምፁ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር። ጃንሆይ የ80ኛ ዓመት የልደት በአላቸው ላይ ካደረጉት ንግግር ጋር የሚመሳሰል ሆነብኝ። ፈርቶ ይሆን?)

 

ከዚህ ሁሉ በሁዋላ መለስ በአንድ ታላቅ ስራ ተጠምዷል።

 

ይህም አመፅ ሳይነሳ፣ ግርግር ሳይኖር፣ የፍርድ ቤት ጣጣ ሳይጀመር ምርጫ 2002 ህጋዊ ይሆን ዘንድ ተመኝቶ እየባተለ ነው። ይህ ምኞቱ ተሳክቶ በቀጣዩ አምስት አመታት ስልጣን ላይ ለመቆየት ደግሞ ማንኛውንም አይነት መስዋእትነት ለመክፈል እየተሯሯጠ ይገኛል። በመግቢያዬ “አንዳንድ ነጥቦች” ያልኳት ወግ እንግዲህ እዚህ ላይ ትቋጠራለች።

 

ግንቦት 25፣ 2002 በፕሮፌሰር ይስሃቅ ኤፍሬምና በአትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ የሚመራው የሽማግሌዎች ኮሚቴ መለስ ዜናዊን አጊኝቶ አነጋግሮት ነበር። ሽምግልናው ተቃዋሚዎችንና የመለስን ቡድን ማቀራረብ የሚል ነው። ኮሜቴው በራሱ ተነሳሽነት ተንቀሳቀሰ ወይስ በመለስ የእጅ አዙር ግፊት አይታወቅም። መለስ ዜናዊ ግን ለሽማግሌዎቹ ኮሚቴ የሚከተለውን ቃል ሰጥቶአል።

 

1. ተቃዋሚዎች ‘ምርጫው ተጭበርብሮአል’ ብለው ወደ ፍርድ ቤት ለመሄድ የሚያስቡትን በመተው፣ የኢህአዴግን ማሸነፍ በይፋ እንዲቀበሉ።

 

2. ይህን ከፈፀሙ አንዳንድ የሚንስትርነትና የአምባሳደርነት ቦታዎችን ሊያገኙ እንደሚችሉ።

 

3. ይህን ድርድር ከተቀበሉ ብርቱካን ሚደቅሳም ከእስር እንደምትለቀቅ።

 

ፖለቲካ ቁማር ነው። የሽማግሌው ቡድን ከተቃዋሚዎች ጋር የሚያደርገው ውይይትና ድርድር ወዴት እንደሚያመራ በቅርቡ የምንሰማው ይሆናል። መለስ ከሽማግሌዎቹ ጋር ባደረገው ቆይታ፣

 

“መረራን አጥብቃችሁ ምከሩት!” ሲል ለይቶና አፅንኦት ሰጥቶ መናገሩን ሰምቼያለሁ።

 

ርግጥ ነው፣ መረራ አስቸጋሪ ሰው ነው። ለመለስ ኩርንችት ሆኖበታል። ማስረጃ ባይኖረንም በዚያን ሰሞን መረራ ላይ የተለጠፈችበት የነፍስ ግድያ ውንጀላ አርፎ የማይቀመጥ ከሆነ፣ ለማሳረፊያ መጠባበቂያ ትሆን ዘንድ የተፈበረከች መሆኗ ምንም አያጠራጥርም። መረራ ጉዲና አንድ ተራ ሰው በማስገደል የምርጫውን ውጤት ለመለወጥ ይሞክራል ብሎ የሚያስብ የለም። ይልቁን መግደልን የለመዱትና ባህል ያደረጉት ቅንድባሞቹ ናቸው። መረራ ጉዲና “የኢህአዴግን ማሸነፍ አልቀበልም” ብሎ የሚያንገራግር ከሆነ ግን፣ ይህቺው የፈጠራ ክስ ወደ ፍርድ ቤት ልትመራበት ትችላለች። መንገዱ ወዴት ያደርሳል?

 

ዶክተር በየነ ጴጥሮስ ለዚህ አይነት ጨዋታ የተመቸ ሰብዕና እንዳለው ካለፈ ታሪኩ ታዝበናል። በየነ ጴጥሮስና ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ወዳጅ ናቸው። ዶክተር ቆስጠንጢኖስ የስዩም መስፍን የቀድሞ ሚስቱ ወንድም ሲሆን፤ ከውጭ ጉዳይ ዳጎስ ያለ ዶላር እየተከፈለው በምስጢር የሎቢ ስራ ይሰራል። የስራ ቦታው ሂልተንና ሼራተን ሲሆን፣ ምሽት ላይ ከማንም ያልወገነ ነፃ ምሁር መስሎ በመጠጥና በባንኮኒ ዙሪያ ሎቢ ያደርጋል። በምርጫ 97 ዶክተር በየነ ለኢህአዴግ እጁን የሰጠው በዚሁ በዶክተር ቆስጠንጢኖስ በኩል ነበር። በየነ የሁኔታዎችን መለዋወጥ ሲመለከት ሸርተት ብሎ በቆስጠንጢኖስ በኩል ከስዩም መስፍን ጋር በቀጠሮ ተገናኘ።

 

እና ቃል በቃል እንዲህ አለው፣

 

“ነፍጠኞች ወደ ስልጣን ከሚመጡ እናንተ ትሻሉናላችሁ!”

 

ከዚያም በሚቀጥለው ቀን፣ እነ ብርሃኑ ነጋን “መጣሁ! ጉዳይ አለችብኝ” ብሎአቸው ሲያበቃ፣ እነሱ ይመጣል ብለው እየጠበቁት እሱ ጠጉሩን አበጥሮ ፓርላማ ውስጥ ተገኘ። ዶክተር በየነ አሁንም ተመሳሳይ መድረክ ገጥሞታል። በርግጥ ፓርላማው አምልጦታል። አምባሳደርነት ወይም ሚንስትር ዴኤታነት እጁ ላይ አሉ። እነዚህን ለማግኘት ግን “ተሸንፌያለሁ!” ብሎ ማወጅ አለበት። የመለስ ቡድን ይህቺን ቀውጢ ጊዜ ለማለፍ በጥብቅ እየጣረ ነው። ለዚህ ደግሞ ማንኛውንም አይነት ጥቅማ ጥቅም ለተቃዋሚዎች ይሰጥ ይሆናል።

 

ብርቱካን ሚደቅሳ ከመነሻውም የታሰረችው ምርጫውን ታደናቅፋለች ተብሎ ተፈርቶ እንጂ በተናገረችው ንግግር አለመሆኑ ተወቅጦና ተፈጭቶ ያበቃለት ወግ ነው። መለስ በዚህ በኩል፣ “መረራ ጉዲና በሰው ግድያ እጁ እንዳለበት መረጃ ቢኖረንም ምህረት አድርገንለታል” ይለናል። “ለብርቱካን ደግሞ እድሜ ልክ!” ቅንድቡ ያማረው መሪ - ካሰኘው ይቀነድባል - ካልመሰለው ቅንድቡ እንደመራው። በመጪዎቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ መለስ ብርቱካንን ከእስር ለመልቀቅ መደራደሪያ ሊያደርጋት መሞከሩ አይቀሬ ይሆናል። በርግጥም ብርቱካን በቅርቡ ትፈታ ይሆናል። ርግጥ ነው፣ ከባዱ ማእበል አልፎአል። ያቺ ብርቱ ሴት አሁን አስጊ አይደለችም …


ተስፋዬ ገብረአብ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ