ነቢዩ ሲራክ

* የጎዳን የመብት አስከባሪ ማጣት እንጅ ዐረቦች ከፍተው አይደለም
* ዐረብ አሰሪዎች ግፍ ፈጽመው የሕግ የበላይ አይሆኑም
* ሦስት ዓመት ያለ ደመወዝ አሰሯት፣ የመብት አስከባሪ ተገኘና ተከፈላት

ከሦስት ዓመት በፊት ያኔ "ሕጋዊ" በተባለው የኮንትራት ሠራተኞች ወደ ሳውዲ ከጡት ዕድሜያቸው ለሥራ ካልደረሱት መካከል ስለአንዷ እኅታችን ነው ዛሬ የማወጋችሁ። ለሥራ በተሰማራችበት የምሥራቅ ሳውዲ አንድ ትንሽ መንደር ከሳውዲ አሰሪዎቿ ጋር ለሦስት ዓመታት ከሰራች በኋላ አሰሪዎቿ ደመዎዝ ሳይሰጡ ወደ አገር ለመላክ ወደ ጊዜያዊ መጠለያ እስር ቤት ያስገቧታል። ደማም ውስጥ ባረፈችበት ማቆያ እስር ቤት በተመሳሳይ ሁኔታ በኮንትራት መጥተው ወደ አገር ለመግባት የቆረጡ እኅቶችን ታገኝና እያነባች የደረሰባትን ድካምና ለዓመታት የሠራችበትን ደመወዝዋን አለመቀበሏን ላገኘቻቸው ሐበሻ እኅቶቿ ታጫውታቸዋለች። ይህን አሳዛኝ ታሪኳን የሰሙት እኅቶች መረጃውን ተቀባብለው "በዜጎች ጉዳይ ያገባኛል" ለሚሉ ወገኖች የደረሰባትን በደል ያደርሱታል ...

መረጃው በምሥራቅ ሳውዲ በደመማም ለሚገኘው አዲስ ተቋቋሚ የኮሚኒቲ አባላት ደርሶ ክትትሉ ተጀመረ። ብርቱዎቹ አዳዲስ ተመራጭ የኮሚኒቲ አመራሮች ጉዳዩን ይዘው ወደ ሳውዲ መንግሥት በማቅረባቸው አሰሪው በፖሊስ ተጠርቶ ያልተከፈላትን ደመዟን ሙሉ በሙሉ እንድትረከብ ተደረገ ... እነሆ በልጅነት ጉልበቷ በላቧ የሠራችው ገንዘቧን ተቀብላለች፣ የለፋችበት የሦስት ዓመት ደመወዝ ገንዘቧን መረከቧን እነሆ በደስታ እየተፍለቀለቀች ትናገራለች! ... ደስ ሲል!

አዎ! ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው እኅቶች በተመሳሳይ ሁኔታ የሰሩበትን ደመወዛቸውን መነጠቁ ሳያንስ ግፍ እየተፈጸመባቸው ተሸፋፍኖ ወደ አገር ለመሸኘታቸው ምስክሮች አለን! ይህ የሆነበት ዋና ምክንያት የሳውዲ አሰሪዎች ከሕግ በላይ ሆነው፣ ለዝርፊያ ሕጉ የሚፈቅድላ ቸው ሆኖ ሳይሆን የዜጎችን ጉዳት ወደ ሚመለከተው የሳውዲ አካላት አድርሶ መብታቸውን የሚያስከብርልን የመንግሥትና የማኅበረሰብ ተወካይ በማጣታችን ብቻ ነው! ይህን የምለው እንደ እድል ሆኖ ጉዳያቸው ተይዞና ክትትል ተደርጎላቸው የለፉ የደከሙበትን፣ የተጎዱ የተበደሉበትን ጉዳይ ፍትህ አግኝተው የጉልበት፣ የላብ ድካም ውጤት ደመወዝና የበደላቸውን ዋጋ ተከፍሏቸው ወደ አገር የተሸኙትን ጥቂቶች አውቃለሁና ነው!

የመብት ጥበቃ ጉድለት በሁሉም ዐረብ አገራት በሚባል ደረጃ ይስተዋላል። ጉዳዩ በአብዛኛው የመብት ረገጣ በመሆኑ ተመሳሳይ ነው። ከግማሽ ሚሊዮን የማያንሱ ኢትዮጵያውያን የኮንትራት ሠራተኞች "በኮንትራት ሥራ" ስም በተሰደዱባት ሳውዲ ዐረቢያ ከሌሎች አገራት የበለጠና የከፋ መጠነ ሰፊ ችግር መኖሩ ደግሞ እውነት ነው። ችግሩን በሳውዲና በቀሩት ዐረብ አገራት ያሉ ኢንባሲና ቆንሰላ መ/ቤቶች አብጠርጥረው ያውቁታል። ዳሩ ግን እየሠሩ ያለው መሆን ያለበትንና የሚጠበቀውን ያህል አይደለም፣ በዚህ ጉዳይ ዙሪያ የሚሞግተኝ ካለ ከጥላቻ ለጸዳው ውይይት ሁሌም ዝግጁ ነኝ! መረጃ ማስረጃ እያቀረብን መነጋገር እንችላለን ...

ወደ መብት ማስጠበቁ መክሸፍ ስናመራ በእርግጥ ለክሽፈቱ አስተዋጽኦ ወደ ሳውዲም ሆነ ወደ ቀሩት አገራት የሚላኩት ዲፕሎማቶች ዲፕሎማሲያዊ ልምድ አልያም ጉዳይን የማስፈጸምና የመምራት አቅሙ ያላቸው አለመሆኑ እንደሆነ በርካታ ማሳያዎችን ማሳየት ይቻላል። ሌላው ሁሉ ቀርቶ እነሱ አቅምና ባጀቱ ቢያንሳቸው በመብት ማስከበሩ ክሽፈት የተጎዳው፣ በሚሠራው ልቡ የሚደማውን ዜጋ ማስተባበር ቢችሉ፤ ነዋሪው ገንዘብ አዋጥቶ ጠበቃ እስከመቅጠር ቀናኢነት ለመሆኑ ከጥያቄ አይገባም። ከነዋሪው ባለፈ ሰፋ ባለና በተደራጀ መንገድ ችግሩን ለመቅረፍ በየአገሩ ያሉትን ኮሚኒቲ ማኅበራት በማደራጀትና በማቀናጀት ጠቃሚ ሥራ መሥራት ይችሉ ነበር። እያወቁ አጥፊዎች ናቸውና ይህን ግን አያደርጉትም።

ከተባበሩት ኢምሬት እስከ ኩዌት፣ ከኳታር እስከ ባህሬን ከሳውዲና ሊባኖስ ኢንባሲና ቆንስሎች የሚከተሉት የፖለቲካ ድርጅትን በውስጠ ታዋቂነት ያማከለ አዲስ የኮሚኒቲ አወቃቀር ደግሞ እንደ መፍትሔ ቢጀመርም ወደ ለየለት አዘቅት ከመወርወር አላዳነንም። ነባርና መጠነኛ እርዳታ ያደርጉ የነበሩ ማኅበራትን በማፈራረስ በአዲስ መልክ የሚመሰርቷቸው ማኅበራት ለነዋሪው የሚፈይዱት ነገር የለም። የማኅበራቱ አደረጃጀት ለሰብዓዊ እርዳታ ሳይሆን ለፖለቲካ ፍጆታ እና ለገንዘብ መሰብሰቢያ በመሆኑ ሰው ወደ ተቋማቱ መቅረብ አይሻም፣ በዚህ ምክንያት ከድጡ ወደ ማጡ እያደርን ለመዘፈቃችን ሁነኛ ምክንያት ነው!

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በሚኖሩበት በዋና ከተማዋ ሪያድ ኢንባሲው በፈለገው መንገድ ማደራጀት ያልቻለው ኮሚኒቲ ከፈራረሰና ድብዛው ከጠፋ ዓመታት ተቆጥሯል። በጅዳም ኮሚኒቲው በተፈለገው ድርጅት ቀመስ አወቃቀር በጣም ጥቂት ነጻ የተባሉ ተመራጮች ቢገቡበትም ድምጽ የላቸውምና፤ ኮሚኒቲው የሚተነፍሰው በቆንስሉ ፖለቲከኞችና በተሰገሰጉት የድርጅት ጉዳይ ፈጻሚዎች ሳንባ ሆኗል። ኮሚኒቲው ከቆንስሉ መሳ ለመሳ የዜጎችን መብት ማስከበሩ ቀርቶ ከ3000 በላይ ታዳጊዎች የሚማሩበት በአገር ወዳድ ዜጎች የተመሰረተው የትምህርት ማዕከል እያደር አደጋ የሚሰማበት ተስፋ አስቆራጭ ማዕከል ሆኖብናል። ወደ ኩዌት ብንዘልቅ የምናገኘው እውነት ተመሳሳይ ነው! ኢንባሲው ኮሚኒቲውን አደራጅቶ የዜጎችን መብት ለማስከበር ተስኖት ዜጎች ለመብት ረገጣ ተጋልጠዋል።

ከሁሉም የሚያሳዝነው በተጠቀሱት አገራት የሚገኙ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን "የዜጎች መብት ይከበር፣ ለተገፋው ዜጋ ዋስ ጠበቃ ሁኑለት!" ብለን ስንጠይቅ እንደ ተቃዋሚ ያዩናል። የተበዳይ ዜጎችን ሮሮ ስናሰማ "ድብቅ አላማ አላቸው!" እያሉ የዜጎችን ድምጽ ለማፈን ያሻቸውን ተቃዋሚ ስም እየለጠፉ ያሸማቅቁናል። ይህ ግን መፍትሔ አይደለምና ችግሩ እያደር ተባብሷል! የዐረብ አገራት ያሉ ኢንባሲና ቆንስሎች ድክመት መጠነ ሰፊ ነው፣ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤትና ማዕከላዊው መንግሥት ምድር ላይ ያለ እውነቱን አምኖ በመቀበል ማሻሻል አልቻለም! የሳውዲም ሆነ የዐረብ አገር ስደተኞችን የጎዳን የመብት አስከባሪ ማጣት እንጅ የዐረቦች ከፍተው አይደለም፣ ዐረቦች ግፍ ፈጽመው ለሕግ የበላይ ሆነው አይደለም፣ ድክመቱ የእኛ ተቆርቋሪና መብት አስከባሪ ማጣት ነው፣ ደረቅ እውነቱ ይህ ነው!

በየትኛውም የዐረብ አገር የመብት አስከባሪ ማጣት እንጅ የጎዳን ዐረቦች ከፍተው፣ ግፍ ፈጽመው ለሕግ የበላይ ሆነው አይደለም ለሚለው የምታዩት የተገፊዋ እኅት የተቀማችውን የዓመታት ደመወዝ መቀበሏ እንደ ትኩስ ማስረጃ ውሰዱት። ይህ ቅንጫቢ መረጃ በምሥራቅ ሳውዲ በደማም ከሳምንታት በፊት የሆነ ነው፣ ለስኬት የበቃውም በዜጎች ጠቋሚነትና በኮሚኒቲ መብት ማስከበር ትጋት የታከለበት ክትትል ነበር፣ እናም ይህች አንድ ፍሬ እኅት የሠራችበትን ደመወዝ መቀበሏ ለአባባሌ ሁነኛ ምስክር ነው! በዚህ አጋጣሚ ጉዳዩን ተከታትለው ጥቆማውን ላቀረቡት ወገኖችና ላስፈጸሙ ለደማም ኮሚኒቲ አመራሮች የላቀ ምስጋናዬን ማቅረብ እወዳለሁ!

ቸር ያሰማን!

ነቢዩ ሲራክ
ኅዳር 17 ቀን 2009 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ