Prof. Fikre Tolossa new book

”የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” የተሰኘውን የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳን መጽሐፍ የምትተቹና የምትቃወሙ፤ ኢትዮጵያን ባለማወቅ፣ ከቅናትና ምቀኝነት በተነሳ ሃሰት ነው

ይሁነው አሰፋ

አስተያየትና መተቸት አግባብ ያለው ተመክሮ ሆኖ ሳለ በተለይ ሦስት ሰዎች የተቻችሁትና ያቀረባችሁ ነቀፌታ ከእውነትና ሃቅ እጅግ የራቀ ከመሆን ጋር፤ ከቅናትና ምቀኝነት የተነሳ ውሸትና ሃሰትን ያካተተ ለመሆኑ በጉልህ አሳይቶባችኋል። እውነትን ፈላጊ ትክክለኛ ነገሮችን የሚሻ፣ እንዲሁም የተማርንና አወቅን ከሚሉ፣ እኩል የትምህርት ችሎታና ማዕረግ፣ ኢትዮጵያንና ታሪኳንም እናውቃለን ከምትሉ፤ በተለይ ከፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌና ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልክያስ በመጽሐፉ ላይ የሰነዘራችሁት አስተያየት እጅግ በጣም ዝቅ ያለ ትምህርታዊ ተመክሮን፣ ክብርና ማዕረግን ያልተከተለ ሥነ-ምግባርና ፕሮፌሽናሊዝምን ያጓደለ ነው። ከዚህም የተነሳ የሰነዘራችሁት ትችት፣ አስተያየትና ተቃውሞ ትምህርታዊ እርማትን የሚያመጣ ሳይሆን፤ አሉባልታና ተራ ነቀፌታ፣ ቅናትና ተንኰልን የሚያንጸባርቅ በመሆኑ በብዙ ታዛቢዎች ዘንድ ቅሬታንና ኀዘንን አሳድሮብናል።

የፕሮፌሰር ጌታቸውን ትችትና ነቀፌታ በተመለከተ እራሱ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ በሰፊውና አግባብ የሆነውን መልስ ሰሞኑን ስለሰጠበት እኔ በዚህ ላይ ብዙ አልልም። ይህን ጉዳይ የተከታተላችሁ ትረዱታላችሁ ብየ እገምታለሁ። ነገር ግን ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ በተደጋጋሚ ብዙ ጊዜ የሚሰጧቸው አስተያያቶች እጅግ የተሳሳቱ፣ ግራ የሚያጋቡና ከእኝህ ፕሮፌሰር ነኝ ከሚሉ የሚጠበቁና ትምህርት የሚሰጡ ሆነው አይታዩም። ከእውነት የራቁና ፈር የለቀቁ፣ መፍትሄ እማይሆኑ አስተያየቶችና አሳቦች ናቸው። ለምሳሌ ከብዙዎቹ ጥቂቶቹን ልጥቁስ፤

1ኛ/ ከዚህ ከአሁኑ ጉዳይ ብጀምር፣ ይህ መጽሐፍ ከ45 - 63 ቢብሊወግራፎች ከነ ገጻቸው እያጠቀሰና የጥንታዊ መጻሕፍት ግኝት ከሆነው እያቀናበረ የጻፈውን ተረት ተረት ነው ብሎ፣ ብርቅየ የኢትዮጵያን የቤተክርስቲያንና የሕዝቧን ታሪክ ማናናቅና ለማራከስ መሞከር። ይህን መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን እየነቀፉ ያሉት ሬፈራንሶችንና ከአምሳ ዓመት በፊት በመሪራስ አማን በላይ የተገኘውን ማስረጃና እውነተኛ ታሪክነቱ ተረጋግጦ ተመዝግቦ በታሪክ ሰነድነቱ የተቀመጠውን ጭምር ነው።

2ኛ/ ከባንዳው ወያኔ ጋር ያለውን ትግላችንን “ወያኔን የተቃወመውን ሁሉ ደግፉ ብለው” ትግላችን ከባንዳውና ከተገንጣይ ድርጅቶች ጋር እንዲተራመስ ይሰብካሉ።

3ኛ/ የተደራጀና ሊመራ የሚችል ድርጅት ሳይኖር የቀረን ክተት ነው ብለው ቅስቀሳ ጀምረው ነበር። ሌሎች ብዙ ማሳሳቻዎችን በየጊዜው ይሰጣሉ በውጭ ያለውን ስደተኛ ሕዝብ ያሳስታሉ። ይህን ህዝብ የሚያቀው ሲሆን በአጠቃላይ ከፕሮፌሰሩ የሚጠበቅ ትምህርት ሰጭና የምንከተለው አስተያየት የተዛባ ነው።

ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልኪያስ ያቀረበው ትችትና ነቀፌታ የመሰለ ተቃውሞ አዘል ነው። በጠቅላላው አሳቡና የሰነዘረው አስተያየት ሲገመግም፣ ለምን ፕሮፌሰር ፍቅሬ ኢትዮጵያን በተመለከተ፣ የህዝብን ስሜትና ቀልብ የሚስብና ተወዳጅ መጽሐፍ ጻፈ ብሎ ቅናት ያለበት መስሎ ከመታየቱም በላይ፤ ተበለጥኩ ብሎ የተናደደ ይመስላል እንጂ የመጽሐፉን ስህተት ወይም ሶርሱን ጠቅሶ ለአንባቢና ለጸሃፊው ትምህርታዊ እርማት እንዲያገኝ የሰጠው ማሳሰቢያነት የለም። መጽሐፍ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ በብዛት በመነበብ ላይ ያለና ህዝቡን በኢትዮጵያዊነቱ እጅግ እያቀራረበው ነው። ከዚህም የተነሳ ወያኔ እገበያ ላይ እንዳይውል ከልክሎታል።

በሦስተኛ ደረጃ ተችና ተቃዋሚ ሆኖ የቀረበው ምትኩ አዲስ ተብየው ሲሆን፣ መጽሐፉን “ልብ ወለድ” ነው ይላል። ይህ ሰው ከተገንጣዎች ወገን የሆነ የሚናገረውና ሊያስተላልፈው የሚፈልገው የወያኔን ፀረ-ኢትዮጵያ አቋም የያዘ ዓይኑን ጨፍኖ ለመቃወም ብቻ የተነሳና የተላከ ግብዝ ሰው ነው። ኢትዮጵያና ህዝቧን አይደለም እራሱን እኔ ማነኝ ብሎ በመጠየቅ ያወቀና የተረዳ አይደለም። ባቀረባቸው ተራና መናኛ አስተያየቶች የእራሱን ዝቅተኝነትና አለማወቅ ከማጸባረቁ ባሻገር፤ በዚህ ድርጊቱ አዝኛለሁ። ኢትዮጵያን ያወቀውና የተረዳው ወያኔና ኦነግ በነገሩትና ባስተማሩት ነው ያየው። ለኢትዮጵያ ስም የሰጧት ግሪኮች ናቸው ብሎ ያመነ፤ በውጭ በጠላት ወሬ የሚያምን ነው። የወያኔን ሃሰትና ግልብጥ ታሪክ አፍቃሪዎች (የአኖሌን፣ ፕሮቻስካን ከፋፋይና ፀረ-ኢትዮጵያ ታሪክና ተገንጣዮች እንዲሁም አማራ የሚባል ጎሣ የለም፣ ኦሮሞ መጤ ነው፣ መሬት የለውም ቅዠት) ውስጥ የገቡና በወያኔ ርዕዮተ-ዓለም የሚመሩ፤ እውነተኛውን የኢትዮጵያ እና የሕዝቧ ታሪክ አይዋጥላቸውም። የዚህ ውጤቶች ናቸው እነዚህ ተችዎች።

ኢትዮጵያ ጥንታዊት፣ ረዥምና ሰፊ ታሪክ ያላት አገር ከመሆን ጋር በዓለም በቀደምትነት መንግሥት መስርተው ከኖሩት ውስጥ አንዷ እንደሆነች በብዙ የዓለም ታሪኮች ተመዝግባና ተነግሮላት እንደሆነና በሳይንስ ሊቃውንትም የሰው ልጅ መገኘትም በዚቹ ኢትዮጵያ መሆኑ የተረጋገጠና የታተመ መረጃ አለ። ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳም ይህን እያጣቀሰ ሃቁን አስቀምጦታል። ፕ/ር ፍቅሬ የጻፈው እውነት ሃቁን እኛነታችንን የሚገልጸውን፣ ኢትዮጵያን ይቺ ናት ለማለት እንጂ ማንንም የማቀራረብ፣ ሰላምና ፍቅርን ለመፍጠር የተደረገ ልብ ወለድ አይደለም። ነው ማለትም የኢትዮጵያ ጠላቶች ተራና እርካሽ ወሬ ነው።

ስለዚህ እነዚህ ከዚህ በላይ የጠቀስኳቸው ሰዎች በፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ “የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” በተሰኘው መጽሐፍ ላይ የተሰጡት ትችትና ተቃውም ፈጽሞ ከእውነት የራቀ አሉባልታና ፍሬቢስ ወሬ ስለሆነ፤ ይህን መጽሐፍ አንብባችሁ ሃቁን የኢትዮጵያን ታሪክ በመረዳት ከየት መጣን፣ የት ነው ያለነው፣ ወዴት ነው የምንሄደው ብለን እራሳችን እንድናውቅና እንድንረዳ ጠቃሚና አስፈላጊ ስለሆነ፤ አንብቡትና የራሳችሁን ግምጋሜ አድርጉ እያልኩ የግሌን አስተያየት አቀርባለሁ።

በመጨረሻ ለፕሮፌስር ፍቅሬ ቶሎሳ እጅግ ብዙ መጻሕፍትን አንብቦና ጨምቆ ለእትም በማብቃት የኢትዮጵያን ብርቅዬ ታሪክ ለንባብ አብቅቶ ስላስተማረን እጅግ ልባዊ አክብሮቴንና ምስጋናየን አቀርባለሁ።

ኢትዮጵያ ምንጊዜም አኩሪ ታሪክ አላት!

ይሁነው አሰፋ
ታህሳስ 26፣ 2009 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ