አብርሃም ቀጄላ

Prof. Getachew Haile

ውድ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ስለ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ ታሪክ በሚለው መጽሐፍ ላይ በሰጡት አስተያየት የሚከተለውን ቅን ሃሳብ አቀርብሎታለሁ።

የአማን በላይ መጻሕፍት አንዳቸውም ... አልፎ አልፎ በእውነት ታሪክ የተቀመሙ ናቸው ... ብለዋል።

እዚህ ላይ ታዲያ እርስዎ እንዳሉት አልፎ አልፎ የእውነት ታሪክ ካለባቸው ያንን የእውነት ታሪክ ሃቅ አዲስ በሚፃፍ መጽሐፍ ቢጠቀስ ክፋቱና በደሉ ምንድነው? እንዲሁም እርስዎ ፕሮፌሰር ፍቅሬን በአማሪኛ ስነ ጽሁፍ ስም ያወጣ የምናደንቀው ደራሲያችን ነው ሲሉ ገልፅዋል፤ ነገር ግን ዶ/ር ፍቅሬ እርስዎ ከገለጹት በላይ በእንግሊዘኛም በጀርመንኛም በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀና የተከበረ ሁለገብ ፀሃፊ መሆኑ አይዘነጋም። እርስዎም አብዝተው እንደሚያውቁት አንዳንድ ሰዎች የብዙ ሙያ ችሎታ፣ ብቃትና ስጦታ እንደሚኖራቸው ሁሉ፤ ፕሮፌሰር ፍቅሬም እንደዚሁ እንደሆኑ የእርስዎና የበርካታ የሌሎች አንጋፋ ምሁራን የብቃት ምስክርነት እንደተቸራቸው ያውቁታል። እርስዎም ቢሆኑ የተካኑበት ዋናው የቋንቋ ዘርፍ ሆኖ ሳለ ባለዎት ብዙ የችሎታ ስጦታ ይሄው አንዳንድ የታሪክ መጻሕፍት ፀሃፊና ተርጓሚ መሆንዎ ይታወቃል።

ታዲያ ፕሮፌሰር ፍቅሬም እንደዚሁ እንደርስዎ ሁሉ የብዙ እውቅና ችሎታ ባለቤት በመሆኑ የታሪክ መጽሐፍ ቢጽፍ ምን ያስነውራል? ምንስ ያስነቅፋል። እነ ክቡር ተክለፃዲቅ መኩሪያ፣ እነአለቃ ታዬ፣ እነጻውሎስ ኞኞ፣ እነማሞ ውድነህ፣ የመሳሰሉት ሁሉ የኢትዮጵያን ታሪክ የፃፉት የታሪክ ትምህርት ዲግሪ ኖሮአቸሁ ነው እንዴ? እርስዎስ ቢሆኑ? በመቅድሙም ላይስ ቢሆን የተለመዱ አንዳንድ መሰረታዊ ግንዛቤዎችን ውድቅ ያደረገ ቢባልስ ምንድን ነው ችግሩ? ልብ እንበል አጠቃላይ ሁሉንም በሙሉ ነባር መሰረታዊ ታሪካችን ሙሉ በሙሉ ጠቅሎ ውድቅ ያደረገ አለማለቱን ያጤኗል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ታሪክ አዋቂዎች ጥቂት (ብቻ) ስለሆኑ ብለዋል። ምነው የኢትዮጵያ ሕዝብ አገሩንና የአገሩን ታሪክ አዋቂ ሆኖ፤ አገሩን፣ ድንበሩን፣ አንድነቱን ጠብቆ የቆየ ቅን ሕዝብ መሆኑን ዘነጉት እንዴ? እርስዎ ከጥቂቶች በስተቀር ታሪክ እውቀት የለውም የሚሉት 100 ሚሊዮን የአገርዎ ሕዝብ ታሪክ ሠርቶ፣ ታሪኩን ጠብቆ፣ ታሪኩን አውቆ የኖረ ሕዝብ ነው። ጥቂት ሰዎች አይደሉም ታሪኩን ያቆዩለትና የጠበቁለት። እንደውም እርሱ ሳይማር እርስዎን አስተምሮ ሊቅ ያደረገዎት ማን ሆነና ነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ታሪክ እንደማያውቅ የሚዘልፉት? እዚህ ላይ እስኪ በእርስዎ ጊዜ የነበረና እርስዎ በሚገባ የሚያውቁትን ታሪክ ልጥቀስና ላስታውሶት።

እ.ኤ.አ. በ1940ዎች መጨረሻ ላይ አንድ የቤተመንግሥት ዝርያ ልዕልት ________ የተባሉ ወደ አሜሪካ ለእረፍት ጉብኝት መጥተው ሳሉ፤ ጋዜጠኛ ቀርቦ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ስንት ነው ብሎ ቢጠይቃቸው ምናልባት አንድ 500 ሊሆን ይችላል እንዳሉት፤ እርስዎም በተመሳሳይ አገላለጽ የኢትዮጵያ ታሪክ አዋቂዎች ጥቂት ናቸው እያሉን ነው። ይህ ከእርስዎ አይጠበቅም።

ይህ ማለት እኮ ይህቺ በድሃ አቅሟ ያስተማረችዎትን ደሃ ኢትዮጵያና ደሃ ባላገር አባቶቻችንን መናቅ ማዋረድ ሆኖ አይታዮትም? ለኔ እጅግ በጣም ወለል ብሎ ይታየኛል፤ ባስተማሮት ሕዝብ ላይ መመፃደቅ ግፍ ነው።

“ዓላማ ዘዴን ያጽድቀዋል” እንዲሉ ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ ዓላማው አማሮችና ኦሮሞዎች በአንድ ነገር ውስጥ በወንድማማችነትና በሰላም እንዲኖሩ ምክንያት ለመስጠት ስለሆነ በምንም ዘዴ ቢጠቀም ክፋት አይኖርበትም የሚሉ አሉ። እንዳፋቸው ያድርግላቸው ብለዋል።

ይህ አባባል ምርቃት (ባርኮት) ወይስ ሟርት ወይስ እርግማን? መንገዱን ጨርቅ ያድርግላቸው ቢጤ ወይስ እርስዎ የኦሮሞና የአማራ ብሎም የኢትዮጵያ ሕዝብ ተፈቃቅሮ መኖሩን ለምን ጠሉት? ያሳዝናል። ሌላ ተጨማሪ ነገር ነበር ግን በማክበር ምንም ሳልተነፍስ ተከድኖ ይብሰል፣ ሆድ ይፍጀው ብዬ አልፈዋለሁ፣ ለእርስዎ እተውሎታለሁ።

እርስዎ እንደሚያፌዙበት ሳይሆን ይህ የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ ብሔራዊ ችግራችንን ለመፍታት መከራችን አሻቅቦ በወጣበት ፈጽሞ ከእንግዲ መፍትሄ የማይኖር መስሎ ድቅድቅ የሐምሌ ጨለማ ሆኖ ከፊታችን በተጋረጠበትና፤ በአብዛኛው ሕዝብና በተለይም ወጣቱ ግራ በተጋባበትና ተስፋ በቆረጠበት፤ ባለቀ ጊዜ በቅጽበት የደረሰለት ፍቱን መድኃኒት አድርጎ ሕዝቡ በሙሉ ተቀብሎታል። የዚህን መገለጫ ለማሳያ ያህል ካለ አንዳች ማስታወቂያና ካለምንም ማሟሟቂያ እና ካለምንም ቲፎዞና ግሩፕ መጽሐፉ እስከዛሬ በአገሪቱ በታሪክ ዙሪያም ሆነ በሌሎች ርዕስ ዙሪያ ከታተሙ መጻሕፍት ሁሉ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከአራት ጊዜ በላይ በመታተምም ሆነ በቁጥር ብዛት ክብረ ወሰን የያዘ መሆኑ ነው።

አሁን ደግሞ በዚህ በአሜሪካን አገር ውስጥ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በተደጋጋሚ ከመታተሙም በላይ በኢትዮጵያውያን ጥያቄ መሰረት በአፋን ኦሮሞ (ኦሮሚኛ) በላቲን ፊደል አዲሱን ወጣት ትውልድ ለማስተማር ሲባል እና በአፋን ኦሮሞ (ኦሮሚኛ) በራሱ ኢትዮጵክ ኦሮሚኛ ፊደል (በዘልማድ የግዕዝ ፊደል በሚባለው) እንዲሁም በእንግሊዘኛ ለመታተም ሂደቱና ሥራው ተጠናቋል፤ ደስ ብሎናል ደስ ይበልዎት! ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው ሕዝቡ ዘር እና ኃይማኖት ሳይለይ በኢትዮጵያዊነት ስሜት ለአገሩ አንድነትና ለአብሮነት ባለው ጥማትና ስሜት የተነሳ መሆኑን ያስገነዝባል።

ምነው እርስዎ ከኢትዮጵያ አንጋፋ ምሁሮች አንዱ ሆነው ሳሉ፤ ከእርስዎ ስለመጽሐፉ ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት ጎን የሚሉትን በናፍቆትና በተስፋ እየጠበቅን ሳለን፤ አንዲት መስመር እንኳን ያልጠቀሱት? ይሄ የፕሮፌሰር ፍቅሬ መጽሐፍ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያልነበሩ የሌሉና ግን በዚህ 25 ዓመታት የተፈጠሩ የተፈበረኩ የሃሰት ታሪኮችና የፈጠራ ልብ ወለድ ታሪኮችን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያጋለጠ ነው። ለምሳሌ የአማራ ገዢ መደብ የሚባል በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አልነበረም የለም፤ ምኒልክ ጡት አላስቆረጡም፤ የኦሮሞ የራሱ የኢትዮጵክ ፊደል እያለው እሱን ትቶ ላቲን ፊደል መጠቀም ተገቢ አይደለም፤ የፖለቲካ ሽኩቻ ያመጣው ነው፤ ወደፊትም ለሕዝቦች መቀራረብ፣ ለሞራልና ለሳይኮሎጂ በጎነት ሲባል በነባሩ የኦሮምኛ ፊደል መጠቀም እንደሚገባ በአድንቆት ይገልፃል። ታዲያ እርስዎ የቋንቋና የማኅበራዊ ዋነኛ ሊቅ ሆነው ሳለ ይህንኑ ከእርስዎ የበለጠ ማዳበር ሲጠበቅ ምንም ይሄንን ጠንካራ ጎን ትንፍሽ ሳይሉ ማለፍዎት ትችትዎ ሁሉ በቅንነት ላይ ያልተመሰረተ መሆኑን ያሳውቅቦታል። በተጨማሪ በዚህ በመከራ ቀን ሰዎች ኢትዮጵያዊነትን ይዘው በአደባባይ ለመቆም በሚሸማቀቁበት የዚህ መጽሐፍ ደራሲ ከብሔር (ዘር) አጥባቂ ወንድሞቹና ወገኖቹ ብሔርተኛ ምሁራን ተለይቶ ዛሬ ባለው የፖለቲካ ጫናና ፍርሃት የተነሳ ምናልባት ማንም ምሁር ሊያደርግ ያልደፈረውንና የማይደፍረውን የአንድነትና የሕብረት ኢትዮጵያዊነት አንግቦ ይዞ የኦሮሞ፣ የአማራና የተቀሩትም ኢትዮጵያውያን ሕዝቦች ከስር የመጣ የዘር አንድነትና አብሮ የረጅም ጊዜ መኖር ውሁድነት ያሳየ በሌሎችና በተለይ በዚህ መጽሐፍ አበርክቶሽ በኢትዮጵያና በውጭ ባሉ ኢትዮጵያዊያን ጭምር ”ሐቀኛ የኢትዮጵያ ልጅ”፣ ”ሐቀኛ የኦሮሞ ልጅ”፣ ”የመከራ ቀን ልጅ”፣ ”የመከራ ቀን ደራሽ”፣ ”የታሪክና የፍቅር አባት”፣ ”የታሪክና የሕብረት አባት”፣ ”የኢትዮጵያ መድን”፣ ”የሕዝብ ዕርቅ አባት”፣ ”አስታራቂ”፣ ”የኢትዮጵያ ቤዛ”፣ ”ፈላስፋ”፣ ”ነብይ” በማለት የተቀበለው መሆኑን በኢትዮጵያና በውጭ ባሉ ሚዲያዎች በሙሉ ማየት ተችሏል። አሁን በቅርቡ በአትላንታ በተካሄደው የኦሮሞ አጥባቂ ብሔርተኞች ጉባኤ ላይ እንኳን ሳይጠራ በራሱ አነሳሽነት በድፍረት በኦሮሞነት መብቱ ተከራክሮ ገብቶ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በተለይም የኦሮሞና የአማራ አንድነትን ለአዲሱ ትውልድ እና ለነባሩ ለቀድሞ ትውልድም አስተምሯል። ይህ ብቻ እንኳን በውስጡ ምን አይነት የሚነድ የሚምቦሎቦል ኢትዮጵያዊነት መንፈስ እንዳለው ከማሳየቱም በስተቀር፤ በራሱ በዚህ ብቻ የኢትዮጵያ ጅግና፣ የጅግና ጀግና ያሰኘዋል።

እርስዎ በብቃትና በጥረት ከማናቸውም በላይ እንደሚያውቁት እና የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚያስተምረን ከውጭ አገራት በቀድሞ ጊዜ በጂኦግራፊ ጥናት ወይም በታሪክ ጥናት ሰበብ በአገር አጥኝነት ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ፈረንጆች አንዳንዶች የየመንግሥታቸው ሰላይ መሆናቸውንና በተጨማሪም በቋንቋ እጥረት ወይንም ትክክለኛ የመረጃ ምንጭ ካለማግኘት የተሟላ የሕብረተሰብ ታሪክ አሟልተው ለመጻፍ ያልቻሉ እንደነበሩባቸው ያሳያል። ለምሳሌም አባ ማስያስንና ኢ.ቼሩሊ የመሳሰሉትን መጥቀስ ይበቃል።

በመጨረሻ ለመራሪስ አማን ... አንተም ያገኘኸው ታሪክ ነገስት ... የታሪክ ምሁራን እንዲመረምሩት እባክህ አሳያቸው፤ ከፈቀድክ ዋናውን ... ልትሰጥ ትችላለህ ብለዋል።

እስኪ እንደው እግዜብሔር ያሳይዎት በዛሬዋ ጊዜ ኢትዮጵያ የሀገር ጥንታዊ ቅርሶችና ሰነዶች በሕገ ወጥ አዘዋዋሪዎች በዓለም አቀፍ ስር ተወጥረው የተገኘ የብራና ዘርና ቅርሳ ቅርስ ሁሉ ከነባር ትላልቅ ሰዎች ቤት ሳይቀር በአሰሳ መልክ በዘርፉ በሌብነት እንደሚመዘበር ከየገጠር በተክርስቲያኖች እና ገዳማት ሁሉ በታጠቀ በተደራጀ ኃይል እየተዘረፈ ባለበት ወቅትና የነራስ አሉላ በወርቅ የተለበደ (የተለበጠ) ጎራዴ ከሙዚየም መጥፋት፤ እንዲሁም የሆለታ ገነት ማርያም ጽላትና ታቦት በታጠቀ ኃይል ለመዝረፍ የተደረገ ሙከራ በሕዝብ ጩኸት መክሸፉና ፈራሽ መሆኑ እየታየ እየተሰማ፤ ከዚህም በስተቀር የታሪክ ጸሀፊው የነተክለጻዲቅ መኩሪያ የታሪክ መጻሕፍት ቤተሰቦቻቸው እያሉ ማንም ያለ ፈቃድ አሳትሞ በገቢያ በሚቸበቸብበት ጊዜና የዘፋኞች ሙዚቃ ሲዲ እነሱ ዘፋኞቹ እያሉ ሌላ ሰው በሕገወጥ ቀማኝነት ሲከብርበት በሚታይበት ጊዜና ወቅት ማንንም ፈረንጅ ሆነ የአገር ሰው ፈጽሞ ለማመን በሚያሸግር በሚያጠራጥር በዚህ ጊዜ፤ መራሪስ አማን በላይ ያገኙትን እጅግ ጥንታዊ ብርቅዬ ሰነድ ሰውረው አፍነውና ሸሽገው መያዛቸው፣ መደበቃቸው የሚያስከብራቸው የሚያስመሰግናቸው ነው። የረጋ ጊዜ ሲመጣ፣ ሲፈጠር ሊያሳዩ ወይም ሊያስረክቡ ይችላሉና ነው። እርስዎ እንደሚያውቁት የጥንት አባቶቻችን የቤተክህነት ቅርሶቻችን በመከራ ከዘራፊና ቀማኛ ሰውረው ለዛሬ ጊዜ እንደ እርስዎ ላለ ተመራማሪ በማድረሳቸው በመመስገን መወደስም የሚገባቸው ይሆናል እንጂ “ሸሻጊዎች”፣ “ቀባሪዎች” ሊያስብላቸው አይገባም። እንደውም በቅርብ ዘመናት ጀምሮ እንደሚባለውና በስፋት እንደሚነገረው የኢትዮጵያ ታሪክ ብርቅዬ ጥንታዊ ቅርሳቅርሶችና የብራና መጻሕፍት አገራችን ባለባት አቅም ማጣትና ድህነት የተነሳ በአገር ውስጥ በቅጡ በዘመናዊና በተገቢው ቦታ ያልተቀመጡና በአግባቡ ያልተያዙ በመሆኑ በሚል አሳቢ በመምሰል አሳማኝ መሰል አማላይ፣ አባባይ፣ አዘናጊ፣ አሳች ምክንያት በማቅረብ በሚሊዮኖች ዶላር ኮሚሽን በማፈስ በተገኘው መንገድና ዘዴ ሁሉ በሕጋዊም ይሁን በተለይም በይበልጥ በሕገወጥ ዝውውር እየወጡ በአደጉ አገሮች እየተመረመሩ እየተደራጁ የራሳቸው የነሱ ሀብት እንዲሆኑ አንዳንድ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ የሚመራመሩ ፈረንጆችና ኢትዮጵያዊያን ሊቃውንት ጭምር በስተጀርባ በስውር ይገፋፋሉ፣ ይረዳሉ፣ ያጠናክራሉ እየተባለ በሰፊው መጠራጠር እንዳለ እየተነገረ ባለበት ወቅት፤ የእርስዎ ስምም ከእንደዚህ ያለ እንዳይያያዝ መጠንቀቅ እንደሚገባ አበክረው እንዲያውቁት አመለክቶታለሁ፣ እመክርዎታለሁ።

በአገር ቅርሶች በዘረፋና በማጭበርበር ስንቶች ሚሊየነር እንደሆኑ ማንም የሚያውቀውና የሚንገበገብበት ሀቅ መሆኑን እርስዎም እንደማይዘነጉት ይገባኛል።

በመጨረሻም ልብ እንዲሉልኝ በማክበር የምለምነው እርስዎን እንደ አድባር እንደ የአገር አባት ስለ ማከብርዎት (ስለምናከብርዎት)፤ ይህን ማስታወሻ ስጽፍ ኢትዮጵያዊ ክብርና ጨዋነትን በጠበቀ መልኩ ለታላቅነትዎ እጅግ ተጠንቅቄ በታላቅ ትህትናና አክብሮት የጻፍኩ መሆኑን ያውቁልኝ ዘንድ እወዳለሁ።

ቸር ይግጠመን!
አብርሃም ቀጄላ
ዋሽንግቶን ዲሲ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!