20210302 adwa

Ethiopian Democratic Party - Press Release

የኢዴፓ አመራሮች ጋዜጣዊ መግለጫውን ሲሠጡ

ቀዳሚ ትኩረት ለአገራዊ ሕልውና!!

ኢዴፓ በሃያ ዓመታት የትግል ጉዞው ለሦስተኛ ጊዜ የገጠመውን የሕልውና አደጋ እልህ አስጨራሽ የሆነ ትግል በማካሔድ አክሽፎታል። በገዥው ፓርቲ፣ በኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ፣ በግንቦት 7 እና በአራት የራሳችን የፓርቲ አባላት ትብብርና ቅንጅት የፓርቲያችንን ሕልውና ለማጥፋት ላለፉት ሦስት ዓመታት የተካሄደብንን ዘመቻ በማያዳግም ሁኔታ አክሽፈን ወደ ትግሉ ጎራ እነሆ ተቀላቅለናል።

የኢዴፓ አመራር አባላት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አምስት አባላት ጋር ኅዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም ሰፊ ውይይት ካደረግን በኋላ ቦርዱ ታኅሣሥ 6 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ እነ ዶ/ር ጫኔ ከበደ ከኢዴፓ አመራርነታቸው በፓርቲው ሕገ-ደንብ መሰረት የተነሱ መኾኑን በማመን፣ እነ ዶ/ር ጫኔ አካሔድነው ያሉት ጠቅላላ ጐባኤና ከኢዜማ ጋር አደረግነው ያሉት ውህደትም ሕገ-ወጥና በተጭበረበረ መንገድ የተፈጸመ መኾኑን በማረጋገጥ፣ በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያለው የኢዴፓ አመራርም በፓርቲው ሕገ-ደንብ መሰረት የተመረጠ መኾኑን በማረጋገጥ፣ በአጠቃላይም ኢዴፓ ቀድሞውንም ቢሆን ያልፈረሰና አሁንም ህጋዊ እውቅና ያለው ፓርቲ መኾኑን ቦርዱ በሙሉ ድምፅ ተቀብሏል። የምርጫ ቦርዱ ይህንን ውሳኔውንም ለተለያዩ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ተቋማት በደብዳቤ አሳውቋል።

ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በፓርቲያችን ላይ ላለፉት ሦስት ዓመታት የፈጸመው ደባ እጅግ አሳዛኝና ከአንድ ትልቅ አገራዊ ኃላፊነት ከሚጠበቅበት የዴሞክራሲ ተቋም የማይጠበቅ አሳፋሪ ተግባር ቢሆንም በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሾሙት አምስቱ የቦርዱ አባላት በመጨረሻ የወሰኑት ይህ ውሳኔ ግን ትክክለኛና በሴራ የተቀማነውን ፍትሕ ወደ ቦታው የመለሰ ኾኖ አግኝተነዋል። ለዚህ ውሳኔያቸውም ኢዴፓ ለአምስቱ የምርጫ ቦርድ አባላት ያለውን ልባዊ ምስጋና በዚህ አጋጣሚ ያቀርባል።

በግፍ የተቀማችሁትን ፍትሕ በእልህ አስጨራሽ ትግላችሁ መልሳችሁ ለማግኘት ለበቃችሁ የኢዴፓ አባላት፣ የኢዴፓን ሃቀኛ አቋሞችና ምክንያታዊ አስተሳሰቦች ስትናፍቁ ለኖራችሁ ደጋፊዎቻችን እንኳን ደስ አላችሁ! እያልን ከዛሬ ጀምሮ በሙሉ ትኩረትና አቅም ወደ ትግሉ ሜዳ መመለሳችንን በከፍተኛ ደስታ እንገልጻለን። በዚህ አስቸጋሪ ሒደት የተጓደለብን ፍትሕ ወደ ቦታው እንዲመለስ ሁለንተናዊ እገዛ ላደረጋችሁልን በውጭ የምትኖሩ የድጋፍ ሰጪ ኮሚቴዎች፣ ጋዜጠኞችና የሚድያ ተቋማት በሙሉ ያለንን አክብሮትና ልባዊ ምስጋና በዚህ አጋጣሚ እንገልጻለን።

ከዚህ አስደሳች የምርጫ ቦርድ ውሳኔ በኋላ አስቸኳይ ስብሰባ ያካሄደው የኢዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴና የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት በተለያዩ የፓርቲው ውስጣዊ ጉዳዮችና በአገሪቱ አጠቃላይ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት አካሒደው የወሰዷቸውን አቋሞችና የደረሱባቸውን ውሳኔዎች እንደሚከተለው እንገልጻለን።

የፓርቲውን ውስጣዊ ሁኔታ በተመለከተ

ኢዴፓ የዕለት-ተዕለት ሥራውን በአግባቡ ማካሔድ እንዲችል በቅድሚያ በሕገ-ወጥ መንገድ በኢዜማ እጅ የሚገኙትን ቢሮዎቹን፣ የተለያዩ ኃብትና ንብረቶቹን የማስመሰል ሥራ ለመሥራት ወስኗል። በዚህ ውሳኔ መሰረትም የፓርቲው ምክር ቤት በቅድሚያ በጤናማ የመግባባት መንፈስ የኢዜማ አመራሮችን ቀርቦ በማነጋገር ችግሩ እንዲፈታ ጥረት እንዲደረግ፣ በዚህ መንገድ ችግሩን መፍታት ካልተቻለ ግን በአስተዳደራዊና ህጋዊ መንገዶች ንብረቶቹን ለማስመለስ ወስኗል። ነገር ግን ከዚህ ውሳኔ በኋላ የኢዜማ አመራሮችን አግኝተን ለማነጋገርና ችግሩን በመግባባት ለመፍታት ያደረግነው ጥረት በኢዜማ በኩል በጐ ምላሽ ሳይገኝ ቀርቷል። በኛ ዕምነት አገራችን እጅግ አሳሳቢ የሕልውና አደጋ ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት ከኢዜማም ሆነ ከማንኛውም ፓርቲ ጋር በትብብር እና በመከባበር መንፈስ የመሥራት እንጂ አላስፈላጊ ቅራኔና ግጭት ውስጥ የመግባት ፍላጐት የለንም።

ስለሆነም አላስፈላጊ የሆነ ጊዜና ጉልበት ሁለታችንም ከማባከናችን በፊት በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ፍትሕ አመጣለሁ ብሎ የሚታገለው ኢዜማ በሕገ-ወጥ መንገድ የያዛቸውን ንብረቶቻችንን በሰላምና በመግባባት መንፈስ በማስረከብ ፍትሕን እንዲያከብር በዚህ አጋጣሚ ይፋዊ ጥያቄያችንን እናቀርባለን። በኛ እምነት ብልህ ፓርቲ ጠቃሚ አስተሳሰቦቻችንን እንጂ ሀብትና ንብረታችንን በመቀማት የሚያገኘው ጥቅም አይኖርም። በዚህ ረገድ የገጠመንንም ችግር ተከታትሎና አጣርቶ ሐቁን ለሕዝብ በማሳወቅ ረገድ መገናኛ ብዙኀን አስፈላጊውን ትብብር እንድታደርጉልን በዚህ አጋጣሚ በአክብሮት እየጠየቅን በእኛ በኩል በወቅታዊና በወደፊቱ የአገራችን አሳሳቢ ችግሮች ላይ የማተኮር እንጂ ከእንግዲህ ወደ አሳለፍነው አስቸጋሪ ሒደት ተመልሰን የመግባት ፍላጐት የሌለን መኾኑንም ለማሳወቅ እንወዳለን።

ፓርቲው በአሁኑ ወቅት የሚጠበቅበትን ከፍተኛ አገራዊ ኃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችል ምንም ዐይነት ቢሮም ሆነ ሀብትና ንብረት በእጁ የሌለ መኾኑን በመገንዘብም የኢዴፓን ዓላማ የምትደግፉ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ኗሪ የሆናችሁ አገር ወዳድ ዜጐች አቅማችሁ በፈቀደ መጠን የገንዘብና የቁሳቁስ እርዳታ እንድታደርጉልን በዚህ አጋጣሚ እንጠይቃለን።

የፓርቲውን ጠቅላላ ጉባዔ በተመለከተ

የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት ከአምስት ወራት በፊት የፓርቲው 7ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባዔ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ እንዲካሔድ ወስኖ የነበረ መኾኑ ይታወቃል። ቢሆንም ከሕልውናው ጋር በተያያዘ በገጠመው ችግር ምክንያት ባለፉት አምስት ወራት ለጉባዔው መሳካት የሚያግዙ በቂ ሥራዎችን መሥራት ሳይችል ቀርቷል። ይህንን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የፓርቲው 7ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባዔ አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎችን በፍጥነት በማከናወን ከአሁን ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ እንዲካሔድ ብሔራዊ ምክር ቤቱ በድጋሚ ወስኗል። ከአምስት ወራት በፊት ጉባዔውን እንዲያዘጋጅ ተመርጦ የነበረው ኮሚቴም ባለበት ሁኔታ ሥራውን እንዲቀጥልና ለጉባዔው ስኬታማነት አስፈላጊ የሆኑትን ሥራዎች በፍጥነት እንዲጀመር ወስኗል።

ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ

በዚህ አጀንዳ ላይ በተደረገው ውይይት በቅድሚያ ትኩረት የተሠጠው የወቅቱን “የለውጥ ሒደት” መገምገም ነበር። ምክር ቤቱ ባካሄደው ሰፊ ውይይትና ግምገማም- ላለፉት 18 ወራት በአገራችን ሲካሔድ የነበረውና በሕዝብ ውስጥ ከፍተኛ የለውጥ ተስፋ ፈጥሮ የነበረው “የለውጥ ሒደት” በሚያሳዝን ሁኔታ ወደ መክሸፍ ደረጃ መቃረቡን ምክር ቤቱ ተገንዝቧል።

“የለውጥ ሒደቱ” ሁሉን አቀፍ በሆነ የሽግግር ተቋምና ከእንዲህ ዐይነቱ የጋራ አገራዊ ተቋም ድርድርና ስምምነት በመነጨ ፍኖተ-ካርታ መመራት ሲገባው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በተለመደ አምባገነናዊ ባሕርይው ሒደቱን በራሱ መንገድና ፍላጐት ብቻ ሊመራው በመሞከሩ “የለውጥ ሒደቱ” የመክሸፍ አደጋ ገጥሞታል። “የለውጥ አመራር” ነኝ የሚለው ኃይል ላለፉት 28 ዓመታት በአገርና በሕዝብ ላይ የፈጸመውን ግፍና በደል የወቅቱን የለውጥ ሒደት ሕዝቡ በሚጠብቀው መጠን ስኬታማ በማድረግ መካስ ሲገባው ይባስ ብሎ ወደ የእርስ-በርስ የሥልጣን ሽኩቻ ውስጥ ራሱን በማስገባት ሕዝቡ በድጋሜ የሠጠውን አደራ እና ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ገዥው ፓርቲ የለውጥ ሒደቱን ስኬታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ተግባራትን ሳያከናውን ምርጫው እንዲካሔድ መወሰኑ የሚያሳየን ከእንግዲህ “በለውጥ አመራሩ” አማካኝነት ሊሳካ የሚችል የለውጥ ሒደት አለመኖሩ ነው። ይህም ሁኔታ ከዚህ ቀደም ኢዴፓ የሽግግር መንግሥት ማቋቋም ሳያስፈልግ አንድ ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽግግር ኮሚሽን በማቋቋም የለውጥ ሒደቱን ማሳካት እንደሚቻል ሲያራምድ የነበረውን አቋም እንደገና እንዲመረምር አስገድዶታል።

የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት ባካሄደው ሰፊ ውይይት ከአሁን በኋላ “የለውጥ አመራር” ነኝ የሚለው ገዥ ፓርቲ ወይም አዲሱ ብልጽግና ፓርቲ ይህንን ከፍተኛ የሕዝብ አደራ የመወጣት ፍላጐትና አቅም እንደሌለው ተገንዝቧል። ከአሁን በኋላም ይህ የመክሸፍ አደጋ የገጠመው የለውጥ ሒደት ከአጠቃላይ ክሽፈት ተርፎ ወደ ስኬት ሊሸጋገር የሚችለው አንድ ሁሉን አቀፍ የእርቅና የሽግግር መንግሥት በአስቸኳይ በማቋቋም ብቻ መኾኑን አምኖበታል። ስለሆነም በሕዝብ ትግል አሸናፊነት ምክንያት ተጀምሮ የነበረው የለውጥ ሒደት ስኬታማ የመኾኑና መሆን ያለመቻሉ ጉዳይ የአገራችንን አጠቃላይ ሕልውና የሚወስን አሳሳቢ ጉዳይ መኾኑን በመገንዘብ መንግሥት የፊታችን ግንቦት ወር ሊካሔድ የታሰበውን አገራዊ ምርጫ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ለሚደርስ ጊዜ በማራዘም ሁሉን አቀፍ የእርቅና የሽግግር መንግሥት በአጭር ጊዜ የሚቋቋምበትን ሁኔታ እንዲያመቻች እንጠይቃለን።

የኢትዮጵያ ሕዝብም ከእንግዲህ ሥልጣን ላይ ባለው ገዥ ፓርቲ አገራዊ ሕልውናችንን አስጠብቆ ለማስቀጠል የሚያስችል ዘላቂ መፍትሔ ሊመጣ እንደማይችል ተገንዝቦ እያቀረብነው ያለውን የእርቅና የሽግግር መንግሥት የማቋቋም ጥያቄ እንዲደግፍ ጥሪያችንን እናቀርባለን። በእርግጠኝነት ከምናውቀው የገዥው ፓርቲ ማንነትና ባሕርይ አንፃርም ይህንን አገራዊ ጥያቄ እንዲሁ ጥያቄ በማቅረብ ብቻ ማሳካት ስለማይቻል ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ አገር-ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በአስቸኳይ አንድ በአገር ሕልውና ላይ የሚመካከር ጊዜያዊ መድረክ ፈጥረው ሕዝቡን በማስተባበርና በመንግሥት ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር ይህ ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚያስችል ትግል እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን። ኢዴፓ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ አገር ወዳድ ዜጐች ይህንን ዓይነቱን መድረክ እንዲያቋቁሙ የበኩሉን ጥረት የሚያደርግ ሲሆን ሊቋቋም የሚገባው የእርቅና የሽግግር መንግሥትም መቼ? እንዴት? በማንና ለምን? ዓላማ መቋቋም እንዳለበት የውይይት መነሻ የሚሆን ሰነድ በአጭር ጊዜ አዘጋጅቶ ለውይይት የሚያቀርብ መኾኑን ይገልጻል።

በአጠቃላይ የኢዴፓ ወቅታዊ ትኩረት አገራዊ ሕልውናን በመታደግ /National Salivation/ ላይ የሚያተኩር እንዲሆን የፓርቲያችን ብሔራዊ ምክር ቤት ወስኗል። ይህንን አሣሣቢ አገራዊ ኃላፊነት ለመወጣት እንዲቻልም የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ትኩረት በእርስ በርስ የፖለቲካ ሽኩቻ ላይ መሆን እንደሌለበት በማመን ኢዴፓ ከማንኛውም የአገሪቱ ሕልውና ከሚያሳስበው የፖለቲካ ፓርቲ ጋር በመቀራረብና በትብብር መንፈስ መሥራት እንዳለበት አጠቃላይ አቅጣጫ አስቀምጧል። በዚህ ረገድ የፓርቲው አመራር ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ቀደም ሲል የጀመራቸው አንዳንድ ግንኙነቶችን አጠናክሮ እንዲቀጥልባቸው ምክር ቤቱ አሳስቧል።

ከዚህ ውሳኔ ጋር በተያያዘም የኢዴፓ አመራር በአሁኑ ወቅት ከበርካታ ፓርቲዎች ጋር ግንኙነት እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ከተወሰኑት ፓርቲዎች ጋር የጋራ የመግባቢያ ሰነድ የመፈራረም ደረጃ ላይ በቅርቡ ሊደርስ እንደሚችል ያለውን ግምትም በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ ይወዳል። ብሔራዊ ምክር ቤቱ ይህንን ተልዕኮውን ለማሳካት ከሌሎች ፓርቲዎች እና ሦስተኛ ወገኖች ጋር የሚደረግን ግንኙነትና ድርድር በኃላፊነት የሚመራ አንድ ኮሚቴ ያቋቋመ ሲሆን ይህንን ኮሚቴ እንዲመሩም አቶ ልደቱ አያሌውን መርጧቸዋል።

በአጠቃላይም በአሁኑ ወቅት እየተሰባሰቡና እየተጠናከሩ ያሉ የኮንፌዴሬሽን ኃይሎችን መቋቋም የሚችል አንድ እውነተኛ የፌደራል ጎራ የሆነ የፖለቲካ ኃይሎች ስብስብ በመፍጠር የአገሪቱን ሕልውና ለመታደግ የሚያስችል እንቅስቃሴ እንዲደረግ ብሔራዊ ምክር ቤታችን አቅጣጫ አስቀምጧል።

ከወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ምክር ቤታችን ባደረገው ውይይት በአሁኑ ወቅት አገሪቱን እየመራ ባለው ገዥ ፓርቲ ውስጥ እየታየ ያለው የዕርስ-በርስ ክፍፍልና ፍጥጫ የአገሪቱን ችግሮች የበለጠ የሚያባብስ ውጤት የሚያስከትል አሣሣቢ ጉዳይ እንደሆነ ተገንዝቧል። ቀደም ሲል በአዴፓና በሕወሓት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአዴፓ ከፍተኛ አመራሮች መካከል፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በአዲሱ ብልጽግና ፓርቲና በሕወሓት መካከል የሚታየው ቅራኔ ለአገራችን ሕልውና ከፍተኛ ጣጣ ሊያስከትል የሚችል ከባድ ችግር መኾኑ ታምኖበታል። ይህ በገዥው ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረ ቅራኔም ለአገራችን ሕልውና የመጨረሻ ደጀን የሆነውን የአገራችንን የመከላከያ ሠራዊት ችግር ውስጥ እንዳይከተው ከፍተኛ ሥጋት ፈጥሮብናል። ኢዴፓ ገዥው ፓርቲ ከሥልጣን ሽኩቻ ይልቅ የአገርን ሕልውናና ጥቅምን በማስቀደም አሁንም ውስጣዊ ችግሮቹን ቅድሚያ ትኩረት ሠጥቶ የመፍታት ጥረት እንዲያደርግ ጥሪውን እያቀረበ፣ ኢዴፓ ከሚታወቅበት የሚዛናዊነትና የምክኒያታዊነት ሚና አኳያም በገዥው ፓርቲ ዙሪያ ያሉ ቅራኔዎች በሰላም እንዲፈቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ የማበርከት ፍላጐት ያለው መኾኑንም በዚህ አጋጣሚ ይገልጻል።

ከአገር ሕልውናና ጥቅም አንፃር በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየታየ ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታም በዙሪያው አንዳንድ አሳሳቢ ክስተቶች እየታዩበት እንደሆነ ፓርቲያችን ተገንዝቧል። በተለይም የኮንስትራክሽን ሴክተሩ በተቀዛቀዘበት በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ከኢኮኖሚው አልፎ ፖለቲካዊ አለመረጋጋቱን የሚያባብስ ውጤት እንዳያስከትል ሥጋት አድሮብናል። በከፍተኛ ጥድፊያ የመንግሥት የንግድ ተቋማትን ለመሸጥ የሚደረገው ሙከራም ወደፊት ለባሰ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዳይዳርገን ሥጋት ፈጥሮብናል።

በአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ዙሪያ ገዥው ፓርቲ እየተከተለው ያለው ግልጽነት የጎደለውና ተቋማዊ ይዘት የሌለው አካሔድም ወደፊት የአገራችን ጂኦ-ፖለቲካዊ ስትራቴጂክ ጥቅም ላይ ከባድ አደጋ ይዞ እንዳይመጣ ሥጋት እየተሰማን መኾኑን እንገልጻለን። በዚህ ወቅት በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሊወስናቸው እና ሊያከናውናቸው የሚገቡ ተግባራት በዋናነት የሽግግር ሒደቱን ውጤታማ በማድረግ ላይ መወሰን ሲገባቸው በአሁኑ ወቅት ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ በግልጽ የምናውቃቸው እና የማናውቃቸው ታላላቅ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎች እየተሰጡ መሆናቸው አብዝቶ ያሳስበናል።

መጭውን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ

ከአሁን ቀደም ለመግለጽ እንደሞከርነው በአሁኑ ወቅት በአገራችን ሰላማዊና ለሕዝብ መንግሥት መመስረት የሚያበቃ ምርጫ ለማካሔድ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ አለ ብለን እናምንም። በአሁኑ ወቅት ፓርቲዎች፣ መንግሥትም ሆነ ሕዝቡ ሰላማዊ ምርጫ ለማካሔድ የሚያስችል የሞራልና የመዋቅር ዝግጅት የላቸውም። የፅንፈኝነትና የብሔርተኝነት ፖለቲካ ከፍተኛ ጡዘት ላይ በደረሰበት በአሁኑ ወቅት፣ አብዛኛዎቹ ማኅበራዊና መደበኛ መገናኛ ብዙኀን የአክራሪ ኃይሎች የአቋም ማራመጃ መድረክ በሆኑበትና፣ ከሁሉም በላይ ስኬታማ የሽግግር ሒደት ባላካሔድንበትና መሰረታዊ የፖለቲካ ቅራኔዎቻችንን ለማቻቻል የሚያስችል ብሔራዊ መግባባት ባልፈጠርንበት ሁኔታ የምናካሒደው ምርጫ የበለጠ ጉዳት እንጂ ጥቅም ሊኖረው አይችልም።

በዚህ ዐይነቱ ነባራዊ ሁኔታ ሆነን የምንካሒደው ምርጫ የለውጥ ሒደቱን የመጨረሻ ክሽፈት የሚያበስርና ወደ ቅድመ 2010 ሁኔታ የሚመልሰን እንጂ ከቶውንም ወደ መዋቅራዊ ዴሞክራሲ ሊያሸጋግረን አይችልም። አሁን ባለንበት ሁኔታ በምርጫ ወቅት የበለጠ ሊባባስና ሊወሳሰብ እንጂ ሊፈታ የሚችል ችግር የለም። ስለሆነም ከላይ ከፍ ሲል ለመግለጽ እንደሞከርነው የተሳካ የሽግግር ሒደት ማካሔድ እስከምንችል ድረስ መጭው ምርጫ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ለሚደርስ ጊዜ መራዘም አለበት ብለን እናምናለን።

ነገር ግን ገዢው ፓርቲ እንደተለመደው ከአገሪቱ ሕልውና ይልቅ የራሱን ጊዜያዊና ቡድናዊ ጥቅም በማስቀደም ምርጫውን በቅርብ ጊዜ የሚያካሂድ ከሆነ ሒደቱን ለፅንፈኛና ብሔረተኛ ኃይሎች ለቆ መተው ተገቢ ነው ብለን አናምንም። ከዚህ እምነት በመነጨ ምርጫው የሚካሔድ ከሆነ ኢዴፓ በምርጫው ይወዳደራል። ከአሁን ቀደም እንደገለፅነው ፓርቲያችን ከሚገኝበት የአቅም ውስንነት አንፃር በምርጫው የሚኖረው ዋና ትኩረት አዲስ አበባን አሸንፎ በመረከብ ላይ ይሆናል። ይህ ውሳኔያችን አሁንም የተጠበቀ ቢሆንም ከዚህ ቀደም ይህንን ውሳኔያችንን ለሕዝብ ይፋ ካደረግን በኋላ “ኢዴፓ በምርጫው የሚኖረው ሚና ለምን በአዲስ አበባ ብቻ ይወሰናል? ” የሚል ከፍተኛ ቅሬታና ግፊት በደጋፊዎቻችንና በሕዝቡ ውስጥ እንዳለ ለመገንዘብ ችለናል። ይህንን የሕዝብ ስሜት ግምት ውስጥ በማስገባት ኢዴፓ በአንድ በኩል በከፍተኛ ፍጥነት ድርጅታዊ ጥንካሬውን ለማጐልበት በመሞከር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከሌሎች ተቀራራቢ አቋም ካላቸው ፓርቲዎች ጋር ትርጉም ያለው ትብብር በመፍጠር በሚመጣው ምርጫ በአገር ደረጃ አሸናፊ ለመሆን የሚያስችለውን ጥረት ሁሉ ለማድረግ ወስኗል። ይህ አገራዊ ዓላማ ያለ ሕዝብ ሁለንተናዊ ድጋፍና ተሳትፎ ሊሳካ አይችልምና አገራዊ ሕልውናችን ተጠብቆ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ዜጐች ሁሉ የፓርቲ አባላት በመሆን፣ የሃሳብና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ከጐናችን እንዲቆሙ ጥሪያችንን በአክብሮት እናቀርባለን።

ሰላምና ህብረ-ብሔራዊነት ዓላማችን ነው!!

የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት

ታኅሣሥ 14 ቀን 2012 ዓ.ም.
አዲስ አበባ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!