ኢዜማ

ኢዜማ (የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ)

የምንሰጠው ሕጋዊና ፖለቲካዊ አማራጭ ከወቅታዊው የኮሮና ወረርሽኝ የሚታደገን፣ አገረ-መንግሥቱን የሚያስቀጥልና ወደ ተረጋጋ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት የምናደርገውን ሽግግር የሚያግዝ ሊሆን ይገባል!

ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የተሰጠ የአቋም መግለጫ

የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከባድ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ ይታወቃል። ወረርሽኙ በሰዎች ጤና እና ደህንነት ላይ ካደረሰው እና እያደረሰ ካለው ጉዳት ባልተናነሰ የዓለምን እና የአገሮችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብሮች እና ሥርዓትን ከባድ አደጋ ውስጥ ከቷል። ወረርሽኙ በአገራችን ኢትዮጵያ እስከካሁን ያስከተለው ጉዳት ከሌሎች አገሮች ጋር ሲነጻጸር አስከፊ የሚባል ባይሆንም የደቀነው አደጋ ግን ከፍተኛ መሆኑ እርግጥ ነው። በሌሎች አገር ከታየው ተሞክሮ አንፃር ወረርሽኙ ድንገት በከፍተኛ ቁጥር ዜጎችን ሊያጠቃ እና የጤና ሥርዓት ቀውስ ውስጥ ሊከተን የሚችልበት አደጋ አሁንም አለ። የጎረቤት አገሮች (ሱዳን፣ ጅቡቲና ሶማሊያ) የኮሮና ቫይረስ ስርጭት በፍጥነት መዛመት የጀመረበትና በተለይ ከጅቡቲ ጋር ካለን የቀረበ የኢኮኖሚ ትስስር አንፃር በምስራቁ የአገራችን ክፍል ላይ የደቀነው ስጋት ከፍተኛ እንደሆነ ግልጽ ነው።

ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የሚወሰዱ እርምጃዎች በአገራችን ኢኮኖሚ ላይ የሚያሳርፉት ጫና ከአሁኑ እየታየ ነው። ወረርሽኙ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚያደርሰው ጫናም በወጪ እና ገቢ ንግድ ዘርፍ ላይ ጫና እያሳደረ ሲሆን ይህም በቶሎ ወደቀድሞ ሁኔታው የሚመለስ አይሆንም። የበረሀ አንበጣ በኢትዮጵያ የግብርና ምርት ላይ እንደዚሁም የአገር ውስጥ ጥቅል ምርት ዕድገት ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው። በተጨማሪም በኮሮና ምክንያት ከፍተኛ የኢኮኖሚ መቀዛቀዝና እስከ ሰኔ ድረስ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚደርሱ ዜጎች የስራ ዋስትና የማጣት ስጋት/አደጋ እንዳንዣበበባቸው በቅርቡ ተገልጿል። በአጠቃላይ ቫይረሱ በኢኮኖሚው ላይ የሚያስከትለው መጠነ ሰፊ መቀዛቀዝና የአገራዊ ጥቅል አመታዊ ምርትና እድገት ማሽቆልቆል አገራችን ላይ የከፋ ጉዳት ማስከተሉ አይቀሬ ነው፡፡

በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የወረርሽኙ ተጽዕኖ ከኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ ጫና በተጨማሪ በፖለቲካው ዘርፍም በታሪካችን አጋጥሞን የማያውቅ ሁኔታ ውስጥ ከቶናል።

ከወረርሽኙ በተጨማሪ ከዚህ ቀደም የነበሩ የውስጥ ፖለቲካዊ ችግሮች እና በዓባይ ወንዝ ላይ እየገነባን ካለነው የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጋር በተያየዘ ከሌሎች አገሮች የተደቀነብን አደጋ በፍፁም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። በተለይም ከግድቡ የውሃ ሙሌት ጋር ተያይዞ የሚመጣው ተጽዕኖ እየጨመረ እንደሚሄድ ይጠበቃል።

በኮቪድ 19 ወረርሽኝን ምክንያት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነሐሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ሊደረግ ታስቦ የነበረውን 6ኛው አገራዊ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. አስታውቋል። ምርጫው በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ አለመቻሉ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የክልል ምክር ቤቶች የሥራ ዘመን ከተጠናቀቀ በኋላ አገርን ማን ያስተዳድራል የሚል ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ አስነስቷል። በዚህም ምክኒያት የተለያዩ አካላት ለዚህ ጉዳይ መፍትሔ ነው የሚሉትን ሐሳብ እያቀረቡ ይገኛሉ።

ኢዜማ በዚህ ጉዳይ ላይ ከሕግ ባለሙያዎች ጋር በተለይም ከሕገ መንግሥት ጠበቆች (constitutional lawyers) ጋር ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡ ባለሙያዎቹ የተፈጠረውን ሕገ መንግሥታዊ ክፍተት በሕገ መንግስታዊ አግባብ እንዴት ሊፈታ ይችላል የሚለውን የወቅቱ ትልቅ ጥያቄ ጊዜ ሰጥተው እንዲመክሩበት የከፍተኛ የባለሙያዎች ጉባዔ (High Level Panel of Experts) በማቋቋም ለአንድ ወር ያህል ጉዳዩን ሲያስጠናና ምክክር ሲያስደርግበት ቆይቷል። ኢዜማ ከገባንበት የፖለቲካ አጣብቂኝ ለመውጣት ልንከተለው የሚገባው የመፍትሔ ሐሳብ የሚከተሉትን ታሳቢዎች ከግምት ያስገባ መሆን እንዳለበት በጽኑ ያምናል፤

1. አገራችን ከምትገኝበት የሕግም የፖለቲካ አጣብቂኝ በአጭር ጊዜ ለመውጣት የሚረዳ መሆን እንዳለበት፣
2. ተቋማዊ አሰራሮችን ከማጎልበት አንፃር የተሻለ እድል የሚፈጥር መሆን እንዳለበት፣
3. አጠቃላይ ችግሩ በአጭር ጊዜ ፈቶ አገራችን ወደተረጋጋ የምርጫ ሂደት ለመግባት የሚያስችል መሆን እንዳለበት፣
4. ከወጪም ከጊዜም አንፃር አገሪቱን ብዙ ዋጋ የማያስከፍል የተሻለው አማራጭ ላይ ትኩረት መደረግ እንዳለበትና በፍጥነት የተቀያየሩት የአገራችንንና የቀጠናውን ጂኦ- ፖለቲካዊና የደህንነት ስጋቶች በሚገባ ከግምት ውስጥ ያስገባ መሆን እንዳለበት።

ኢዜማ ከላይ የገለፅናቸውን አገራዊ ፈተናዎች ለማለፍ ሕዝብን አስተባብሮ ሊመራ የሚችል ጠንካራ መንግሥት እንደሚያስፈልገን ያምናል። ለዚህም እንደፓርቲ ልንከተለው የሚገባን የመፍትሔ ሐሳብ ይህንን የሚያረጋግጥ መሆን እንደሚገባው በፅኑ ይረዳል።

ለዚህም ይረዳ ዘንድ የፓርቲያችንን የሕግ ባለሙያዎች ጨምሮ በሌሎች አካላትም የቀረቡትን የመፍትሔ ሐሳቦች እንደሚከተለው ተመልክተናቸዋል።

1. ከሕግ አማራጭ ውጪ የፖለቲካ መፍትሔ በሚል በተለያዩ አካላት የቀረበ የመፍትሔ ሐሳብ

በዋናነት በዚህ ረገድ የቀረበው ሐሳብ አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሥልጣን ዘመን ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ የሚያበቃ በመሆኑ እና ሕገ መንግሥቱም ከመስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በፊት መንግሥት በሥልጣን ላይ የሚቆይበትን ሁኔታ ክፍተት ስለማይሰጥ በፖለቲካ ፓርቲዎች ንግግር ላይ የተመሰረተ የሽግግር መንግሥት አገሪቱን ሊመራ ይገባል የሚል ነው። ይህ መፍትሔ ሐሳብ አሁን ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነት እና የቁጥር ብዛት ከግምት ያላስገባ በመሆኑ ተግባራዊ ለማድረግ የማይቻል ነው። ከዚህም በላይ እንደ አገር ያሉብንን ከላይ የጠቀስናቸውን ፈተናዎች ተጋፍጦ ለማለፍ የሚያስፈልገንን ጠንካራ የመንግሥት መዋቅር የሚፈጥር አይደለም። ይህም የገባንበትን ችግር ከመፍታት ይልቅ ወደ ባሰ አገራዊ ቀውስ ሊከተን የሚችል አማራጭ ያደርገዋል።

2. በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ሥር ያሉ አማራጮች

2.1. በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 60/1 እና 3 መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን በትነው በ6 ወር ውስጥ ምርጫ ማድረግ፦ ይሄ አማራጭ በ6 ወር ውስጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ እና ሕግ ማውጣት የሚያስፈልጋቸው ድንገተኛ የአገር እና ሕዝብን ደህንነት እና ጥቅም አደጋ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ ሁኔታዎች ከግምት የማያስገባ፣ የፌደራል መንግሥትን እንጂ ሥልጣናቸው አብሮ የሚጠናቀቀውን የክልል ምክር ቤቶች ተመሳሳይ ችግር ያላገናዘበ አማራጭ በመሆኑ የምንፈልገውን ጠንካራ መንግሥት የሚፈጥር አማራጭ ሆኖ አላገኘነውም።

2.2. በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93 መሠረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ እና ምርጫውን ማራዘም፦ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመንግሥትን የሥልጣን ዘመን ለማራዘም የተቀመጠ አንቀጽ አይደለም። አስቸኳይ ግዜ ማዋጅም በቀጥታ የመንግሥትን ሥልጣን ማራዘምን አያስከትልም። እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጥላ ስር የሚደረግ ምርጫን ነፃ እና ፍትሃዊ ማድረግ አይቻልም።

2.3. በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 83 እና 84 መሠረት የሕገ መንግሥት ትርጉም ከፌደሬሽን ምክር ቤት መጠየቅ፦ በዚህ አማራጭ መሠረት የሕገ መንግሥት ትርጉም ሥራ የሚሠራው የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሙሉ ነፃነት እና ያለማንም ጣልቃ ገብነት የተመራለትን ጉዳይ በመመርመር የውሳኔ ሐሳብ አቅርቦ የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የሚሰጥ ከሆነ ያ ውሳኔ ምን ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት ማወቅ አይቻለም። አሁን ካለንበት አጣብቂኝ ክብደት አንጻር ጉዳዩን መዳረሻ ውጤቱ አስቀድሞ በእርግጠኝነት ለማይታወቅ እና ምናልባትም መልሶ እዚህ ከተጠቀሱት አማራጮች መካከል አንደኛውን እንድንከተል ሊያደርግ ለሚችል ሂደት መስጠት ተገቢ ሆኖ አላገኘነውም።

2.4. በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 104 እና 105/2 መሠረት የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ማድረግ፦ ይህ አማራጭ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ በግልጽ የተቀመጠ የማስፈጸሚያ ሥነ ሥርዓት ያለው እና አሁን ለገባንበት አጣብቂኝ የማያዳግም ምላሽ የሚሰጥ ሆኖ አግኝተነዋል።

ምንም እንኳን ኢዜማ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ሊሻሻሉ የሚገባቸው በርካታ አንቀጾች እንዳሉ በፅኑ ቢያምንም አሁን ያለንበት ወቅት ሁሉን አቀፍ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል አይደለም። አሁን ለገባንበት ሕገ መንግሥታዊ አጣብቂኝም ቀልጣፋ ምላሽ የሚሰጥ አይደለም። በኢዜማ ዕምነት ሁሉን አቀፍ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ለማድረግ አገራዊ መረጋጋት፣ በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እና ሰፊ ሕዝባዊ ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው። እንዲሁም በከፍተኛ በጥንቃቄ ሊሠራ እንደሚገባው አገራዊ ጉዳይ በዚህ ወቅት ሊከወን አይገባም ብለን እናምናለን። ሆኖም አሁን የገጠመንን አጣብቂኝ ለመሻገር የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የሥራ ዘመን እና ምርጫ የሚደረግበትን ወቅት የሚደነግገው አንቀጽ 58ን ጊዜውን ጠብቆ ምርጫ ለማድረግ የማያስችል ድንገተኛ እና ከአቅም በላይ የሆነ ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ1 ዓመት ላልበለጠ ጊዜ ምርጫውን ማራዘም እና ምርጫው እስኪደረግ ድረስ ዘላቂ ውጤት ያላቸውን እና በቀጣይ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን በሚይዘው መንግሥት ላይ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚጥሉ ተግባራትን ከመከወን በከለከለ መልኩ የመንግሥትን ቀጣይነት በግልፅ የሚደነግግ አድርጎ በማሻሻል ቀጥተኛ፣ ሕገ መንግሥታዊ፣ የማያዳግም እና ተቀባይነት ያለው መፍትሔ መስጠት አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 105/2 ሀ እና ለ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች እና የፌደሬሽን ምክር ቤቶች በጋራ ስብሰባ በ2/3ኛ ድምፅ ማሻሻያውን ሲያጸድቁ እንዲሁም ከክልል ምክር ቤቶች ውስጥ 2/3ኛ ክልሎች (6 ክልሎች) በአብላጫ ድምፅ ሲያጸድቁት በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ 3 ስር ከሚገኙት እና አንቀጽ 104 እና 105 ውጪ ያሉትን የሕገ መንግሥት አንቀጾች ማሻሻል እንደሚቻል ተደንግጓል። በዚሁ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን የሥራ ዘመን እና ምርጫ የሚደረግበትን ወቅት የሚደነግገው አንቀጽ 58/3 ከላይ በተገለጸው መሠረት ማሻሻል የተሻለ መፍትሔ እንደሆነ እናምናለን።

ይህ መፍትሔ ተግባራዊ ከተደረገ በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት ተከትሎ የሚፈፀም በመሆኑ ሕገ ምንግሥታዊ ጥያቄ የሚያስነሳ አይሆንም። እንዲሁም በቅርቡ ልናደርገው ከምናስበው ምርጫ እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አንፃርም አዎንታዊ ሚና ይኖረዋል ብለን እናምናለን። በዚህ አማራጭ ላይ በተለያዩ አካላት የሚነሳው ጥያቄ በዚህ የወረርሽኝ ወቅት በአንቀጽ 104 ድንጋጌ መሰረት ሕዝብን ለማወያየት አያስችልም የሚል ሲሆን ይህንን ክፍተት ግን ሕዝቡን በወኪሎቹ አማካኝነትና በተለያዩ የቴክኖሎጂ አማራጮች በማወያየት መሸፈን ይቻላል።

ከዚህ ቀደም በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የጋራ የታክስ እና የግብር ሥልጣንን የሚደነግገው አንቀጽ 98 እና የሕዝብ ቆጠራን በሚመለክት የሚካሄድበት የጊዜ ገደብን የሚደነግገው አንቀጽ 103/5 በሕገ መንግሥቱ የተጠቀሰውን የማሻሻያ ሥነ ሥርዓት ሙሉ በሙሉ ሳይከተሉ ለየብቻ በተለያየ ጊዜ ማሻሻያ ተደርጎባቸው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን አሁን መደረግ ያለበት ማሻሻያ ግን የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 104 እና 105/2 ያስቀመጡትን ድንጋጌዎች በሙሉ አሟልቶ ሊሆን እንደሚገባው እናምናለን።

ይህ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በተጨማሪ የክልል ምክር ቤቶችንና የፌድሬሽን ምክር ቤትንም የሥልጣን ዘመን በሚያራዝም መልኩ መተግበር አለበት።

የፓርቲያችን ዕምነት የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 58/3 ማሻሻል የተሻለ አማራጭ ነው የሚል ቢሆንም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከላይ በተራ ቁጥር 3 ላይ የጠቀስነውን አማራጭ በመውሰድ የሕገ መንግሥቱን አንቀጥ 54/1፤ 58/3 እና 93 ላይ ትርጉም እንዲሰጥ ለፌደሬሽን ምክር ቤት እንደመራው ታውቋል። ምንም እንኳን ኢዜማ ይህንን አማራጭ የተሻለ አማራጭ ነው ብሎ ባያምንም አማራጩ ተግባራዊ የሚደረግ ከሆነ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔው ሕገ መንግሥቱን በሚተረጉምበት ወቅት ከመንግሥትም ሆነ ከሌላ ማንኛውም አካል ተፅዕኖ ነፃ ሆኖ ተግባሩን ማከናወን አለበት። የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በሚያቀርበው የውሳኔ ሐሳብ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሚያጸድቀው ትርጉም የመንግሥትን ሥልጣን በማንኛውም መልኩ የሚያራዘም ከሆነ ማራዘሚያውን እጅግ ቢገፋ ከ1 ዓመት እንዳይበልጥ ማድረግ አለበት። ውሳኔው በዚህ የማራዘሚያ ወቅት ሥልጣን ላይ የሚቆየው መንግሥት ዘላቂ ውጤት ያላቸውን እና በቀጣይ ምርጫውን አሸንፎ ሥልጣን በሚይዘው መንግሥት ላይ ተጨማሪ ኃላፊነትን የሚጥሉ ተግባራትን ከመፈፀም እንዲቆጠብ የሚያስገድድ መሆንም አለበት።

በአጠቃላይ እንደአገር የሚወሰዱ ማንኛውም አማራጮች አሁን ያለንበትን አስቸጋሪ እና ፈታኝ ወቅት ከግምት ያስገቡ፣ የአገር መረጋጋት፣ ሰለም እና ቀጣይነትን የሚያረጋግጡ፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሂደቱን የሚያስቀጥሉ እንዲሁም አሁን ከገባንበት ሕገ መንግሥታዊ አጣብቂኝ በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስወጡን መሆን እንዳለባቸው ኢዜማ ለማሳሰብ ይወዳል። በተጨማሪም በተመሳሳይ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የሚወሰኑ ውሳኔዎች የተለያየ አመለካከት ካላቸውን የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በሚደረግ ውይይት መዳበራቸው መፍጠር የምንፈልገውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንድንለማመድ በር የሚከፍት እና ሁሉንም ኃይሎች የባለቤትነት ስሜት እንዲሰማን የሚያደርግ በመሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተመሳሳይ አገራዊ ጉዳይ ላይ በቂ እና ቀጣይነት ያለው ውይይት የምናደርግበት መድረክ እንዲመቻች ጥሪ እናቀርባለን።

 

ሚያዝያ 28 ቀን 2012 ዓ.ም.
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!