PM Abiy Ahmed held a meeting with Tigray Prosperity

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትግራይ ብልጽግና ፓርቲ አባላት ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት

በትግራይ ብልጽግና ፓርቲን የሚወክል አካል መኖሩ ታወቀ

ኢዛ (ማክሰኞ የካቲት ፲ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 18, 2020)፦ የትግራይ ክልል የብልጽግና ፓርቲ አባላትና አመራሮች ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ጋር መምከራቸው ተገለጸ። እስካሁን በትግራይ ክልል የብልጽግና ቅርንጫፍ ስለመኖሩ ባይገለጽም፤ ዛሬ ይፋዊ መረጃ በትግራይ ክልል የብልጽግና ፓርቲን የሚወክል አካል መኖሩ ታውቋል።

ዛሬ ይፋ በኾነው መረጃ የትግራይ ክልል የብልጽግና ጽሕፈት ቤት አስተባባሪም ዶ/ር አብርሃም በላይ መኾናቸው ታውቋል። ዶ/ር አብርሃም የብልጽግና ፓርቲ አመራር አባል መኾናቸውንም ለማወቅ ተችሏል።

የትግራይ ቅርንጫፍ የብልጽግና አባላት ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ውይይት ያደረጉ ሲሆን፤ በዚህ ውይይት ላይ ከአባላቱ የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ መሥጠታቸው ታውቋል።

ከትግራይ የብልጽግና ተወካዮች በኩል ከቀረቡት ጥያቄዎች ውስጥ፤ ዶ/ር አብርሃም በላይ “በርካታ ባላሥልጣናት ለእስር ተዳርገው ጉዳያቸው በሕግ እየታ ይገኛል። እስረኞቹ ከሁሉም ብሔሮች መኾናቸው እሙን ቢኾንም፤ በርከት ያሉት ታሳሪዎች የትግራይ ተወላጆች መኾናቸው ሊታበል አይችልም። ከለውጡ በኋላ የታሰሩ ዜጎ ክስ ተቋርጦና ጉዳዩ የእርቅና የይቅር ባይነት ማሳያ ተደርጎ ቢወሰድ፤ ከትናንት ተምረን ነገን በተስፋ እንድንመለከት ስለሚረዳን፤ ይህንን ጥያቄ በአዎንታዊ እንዲመልሱልን ከፍ ባለትሕትና እናቀርባለን” ሲሉ ጠይቀዋል።

በዚሁ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሠጡት ምላሽ፤ ከለውጡ ወዲህ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተከስተው ከነበሩ ግጭቶች ጋር ተያይዞ የታሰሩ ዜጎች ጉዳያቸው ታይቶ ለፖለቲካ ምህዳሩ መስፋት ሲባል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ተገቢውን ማጣራት አድርጎ እንዲፈታ አቅጣጫ መቀመጡን ገልጸዋል።

አያይዘውም ወንጀለኛን ከብሔር ጋር ማገናኘት ግን አገርን የሚጎዳ መኾኑንን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። እስረኞች የመፍታቱ ሒደትም ሕግን ትንተርሶ የሚኾን እንደኾነና ከእስር የሚፈቱት ተጨባጭ የሕግና የሰብአዊ መብት ጥሰት አለመፈጸማቸው ተረጋግጦ፣ የተለይ የሙስና ችግር ካልኾነ፣ መረጃ ተገኝቶባቸው የፍርድ ሒደት ላይ ያሉ ሰዎች ካልኾኑ፤ አብዛኛው ከሕግ አንጻር ክፍተት የማያመጣ ከኾነና ሊታዩ የሚችሉ ጉዳዮችን ዓቃቤ ሕግ በፍጥነት የቀረቡትን ጥይቄዎች ዐይቶ እልባት እንዲሠጥ ይደረጋል ብለዋል።

ይኽም የሚኾነው ለውጡን ለማስቀጠል፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ጭምር እንደኾነም ገልጸዋል።

ከኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ ደግሞ፤ በተለይ ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ ፌዴራል መንግሥት ትግራይን የመጉዳት ሐሳብ ሊኖረው እንደማይችልና የበጀት ድልድሉም በፍትሐዊነት የሚከናወን በመኾኑ፤ “ፌዴራል መንግሥት ትግራይን ሊጎዳ ነው” ተበሎ የሚናዘው ወሬ መሠረተ ቢስ መኾኑን በማስረዳት፤ ከበጀት ድልድል ጋር በተያያዘ ለትግራይ የተሠጠውን በጀት በዝርዝር አስረድተዋል።

ከዚህ ውይይት በኋላ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት 45ኛውን ዓመት የካቲት 11 ቀን በማስመልከት መግለጫ አውጥቷል። የመግለጫውን ሙሉ ቃል ለማንበብ እዚህ ይጫኑ! (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ