የብልጽግናና የዶክተር ዐቢይ ድጋፍ ሰልፍ
 
		በለገጣፎ ለገዳዲ ለብልጽግናና ለዶክተር ዐቢይ የተካሔደው የድጋፍ ሰልፍ በከፊል
ታዋቂው ፖለቲከኛ ቡልቻ ደመቅሳ በድጋፍ ሰልፉ ላይ ተገኝተዋል
ኢዛ (ረቡዕ የካቲት ፲፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 19, 2020)፦ በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ ከተሞች ለብልጽግና ፓርቲና ለዶክተር ዐቢይ አሕመድ ድጋፍ ለመሥጠት የሚካሔዱ ሰላማዊ ሰልፎች ቀጥለዋል።
ሰሞኑን በጅማ፣ አጋሮ፣ አዳማ፣ ምዕራብ ሐረርጌና በሌሎችም ከተሞች መካሔዳቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ትናንትና ዛሬም በባሌ ሮቢ፣ በምዕራብ ሐረርጌ ባቢሌ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ መቱና ሌሎች ከተሞች ተመሳሳይ ሰላማዊ ሰልፎች ተካሒደዋል። ዶክተር ዐቢይን በሚያወድሱና ብልጽግና ፓርቲን የሚደግፉ መልእክቶችን የያዙ መፈክሮችን በመያዝ በተደረጉት ትዕይንተ ሕዝቦች፤ በሺዎች የሚቆጠሩ የየከተማው ነዋሪዎች እየተሳተፉበት ነው።
ዛሬ የካቲት 11 ቀን በለገጣፎ ለገዳዲ በተካሔደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ታዋቂው የኢኮኖሚ ባለሙያና በፖለቲካው አንፃርም ሊጠቀሱ የሚችሉት አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የተገኙበት ነበር። ዶክተር ዐቢይ መደገፍ ያለበት ስለመኾኑ በቦታው ለነበሩ ሚዲያዎች በሠጡት ቃለምልልስ ገልጸዋል። አቶ ቡልቻ በፖለቲካ ተሳትፏቸው ኦፌኮ የሚል መጠሪያ ያለውን ፓርቲ በመመሥራትና በመምራት፤ እንዲሁም የፓርላማ ተመራጭ በመኾን ማገልገላቸው ይታወሳል።
ለኦፌኮ ፓርቲ ከፍተኛ ወጪ በማውጣትና ከፍተኛ ሚና የነበራቸው ሲሆን፤ አሁን ፓርቲ ውስጥ የሉም። ኦፌኮ ዛሬ በፕሮፌሰር መረራ ጉዲናና በአቶ በቀለ ገርባ የሚመራ መኾኑ ይታወቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ዶ/ር ዐቢይ ከስልጤ ዞን ነዋሪዎች ጋር ለመምከር በስልጤ ዞን ወራቤ ከተማ ሲገቡ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር የወራቤና የአካባቢው ነዋሪዎች አቀባበል አድርገውላቸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወራቤ ከደረሱና በወራቤ ስቴዲየም መልእክት ካስተላለፉ በኋላ ከዞኑ ወረዳዎች ከተውጣጡ ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገዋል። (ኢዛ)




