Shimelis Abdisa (Photo: The Reporter)

ከምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ወድ ርዕሰ መስተዳድርነት የተሾሙት አቶ ሽመልስ አብዲሳ

ጨፌው ከአሥራ አምስት በላይ ለሚኾኑ የቢሮ ኃላፊዎችና ለ65 ዳኞች ሹመት ሠጥቷል

ኢዛ (ረቡዕ የካቲት ፲፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 19, 2020)፦ የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በመኾን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በዛሬው ዕለት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በመኾን ተሹመው፤ ቃለ መሃላ ፈጸሙ።

አቶ ሽመልስ ከምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት፣ ርዕሰ መስተዳድር ኾነው እንዲሠሩ የተሾሙት የጨፌ ኦሮሚያ እያካሔደ ባለው መደበኛ ስብሰባ ላይ ነው። ጉባዔው የአቶ ሽመልስን ሹመት አጽድቆላቸው ቃለ መሃላም ፈጽመዋል።

ከለውጡ ወዲህ የኦሮሚያን ጨምሮ የአንዳንድ ክልሎች “ምክትል ርዕሰ መስተዳድር” በሚል ሹመት የርዕሰ መስተዳድሩን ኃላፊነት ወስደው ሲሠሩ መቆየታቸውና አሁንም በዚሁ እየሠሩ እንደሚገኙ ይታወቃል። አቶ ሽመልስም በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ሲሠሩ ቆይተው ዛሬ ርዕሰ መስተዳድር የሚለውን ሹመት አግኝተዋል።

አቶ ሽመልስ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በኢሬቻ በዓል ላይ በተናገሩት ንግግር ከፍተኛ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተው እንደነበር አይዘነጋም።

የጨፌ ኦሮሚያ ከአቶ ሽመልስ ሌላ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ አድርጎ ሾሟል።

በዛሬው ሹመት የኃላፊነት ቦታው አዲስ መኾኑ ለተነገረለት የክልሉ የመንግሥት ተጠሪ ለሚለው ቦታ፤ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ተሹመዋል። በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ በመኾን የተሾሙት ደግሞ አቶ አዲሱ አረጋ ሲሆኑ፣ በዚህ በዛሬው ሹመት በጥቅሉ ከአሥራ አምስት በላይ ለሚኾኑ የክልሉ ቢሮዎች ሹመት ተሠጥቷል። የ65 ዳኞችንም ሹመት ጨፌው አጽድቋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ