የባሥልጣናት የሹም-ሽር በመስከረም ማግስት ይካሄዳል ተባለ
Ethiopia Zare (ረቡዕ ሐምሌ 8 ቀን 2001 ዓ.ም. July 15, 2009)፦ በአዋሳ ከተማ ከ10 ወር በፊት በተካሄደው የኢህአዲግ ጠቅላላ ስብሰባ ድርጅቱን በወጣት አመራር እገነባለሁ ያለው ገዥው ፓርቲ በመጪው መስከረም የህወሓት ኢህአዲግ ጠቅላላ ጉባዔ በኋላ ጡረታ የሚወጡ የድርጅቱ አንኳር ሰዎች መኖራቸው ተጠቆመ።
ለሥርዓቱ ቅርብ የሆኑ ሰዎች አስቀድመው በሰጡት ጥቆማ መሠረት፤ ጡረታ ከሚወጡት የህወሓት ቀዳማይ አባላት መካከል አሁን የደህንነት ጉዳዮች ሚኒስትር ሆነው የሚሠሩት አቶ ዓባይ ፀሐዬ አንደኛው መሆናቸው ታውቋል።
የኢህአዲግን ሥርዓት “በወጣት አመራር መለወጥ ያስፈልጋል” በተባለው እና ካለፈው የድርጅቱ የአዋሳ ጉባዔ መርኅ መሠረት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ ሌሎች የመንግሥቱን ቁልፍ ሰዎች ሥልጣን የማሸጋሸግ እና ከወንበራቸው የማስነሳት ዕቅድ መኖሩን ምንጮቹ ጠቁመዋል።
በዚሁ ዕቅድ መሠረት የአቅም ግንባታው ሚኒስቴር አቶ ተፈራ ዋልዋ የዓባይ ፀሐዬ ዕድል ይገጥማቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ አቶ አዲሱ ለገሰም ሥፍራቸውን ሊለውጡ ይችላሉ። የኦሮሚያው ክልል ርዕስ መስተዳደር እና የህወሓት ኦህዲድ ዋንኛ ሰው ናቸው የሚባሉት አቶ አባዱላ ገመዳም ከርዕሰ መስተዳደር እና ከፕሬዝዳንትነት መቀመጫቸው ተነስተው፤ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት ለመሆን ራሳቸውን እያዘጋጁ መሆኑ ተጠቁሟል።
ጠቅላይ ሚኒስቴር መለስ ዜናዊን ማን ይተካቸዋል? ለሚለው ጥያቄም እስካሁን ምላሽ ያላገኘ ሲሆን፣ “ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍንን ጨምሮ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ አቶ ግርማ ብሩ እና አቶ አዲሱ ለገሰ ሊተኳቸው ይችላሉ” የሚለው መልስ ተቀምጧል።
በአሁኑ ሰዓት ድርጅታቸውን ከድተው በካናዳ የሚኖሩ የኢህአዴግ ቀደምት ካድሬ አቶ መለስን ሊተካ የሚችለውና በተንኮልም ሆነ በባህሪ የሚስተካከለው አቶ አዲሱ ለገሰ ብቻ ነው ሲል አስተያየቱን ለኢትዮጵያ ዛሬ ሰጥቷል። ጠ/ሚ መለስ ባለቤታቸውን የሚተኩ ከሆነ ቀደማዊቷ እመቤት የመጀመሪይቱ የኢትዮጵያ ሴት ጠ/ሚንስትር ይሆናሉ።



