ጠ/ሚ መለስ ሚኒስትሮቻቸውን አጸደቁ
አቶ ስዩም መስፍን በአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ተተክተዋል
Ethiopia Zare (ማክሰኞ መስከረም 25 ቀን 2003 ዓ.ም. October 5, 2010)፦ በ2002 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ መሰረት በብቸኛው ፓርቲ ኢህአዴግ ለመጭው አምስት ዓመታት የምትመራው ኢትዮጵያ ከትላንት ሰኞ ጀምሮ በተካሄደ የፓርላማ ተመራጮች ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ አፈ ጉባዔ፣ ም/ጠቅላይ ሚኒስትርና ሌሎች የካቢኔ አባላትን አጸደቀ።
ትላንት በአፈ ጉባዔነት በተመረጡት በአቶ አባ ዱላ ገመዳ የተከፈተውና ጠቅላይ ሚኒስትር መለስን ለመጭው አምስት ዓመታት በድምሩ ለ24 ዓመታፈት እንዲመሩ የመረጠው የፓርላማ ስብሰባ፤ ዛሬ ደግሞ አቶ መለስ የመረጧቸውን ካቢኔዎች በሙሉ ድጋፍ አጽድቋል። ወ/ሮ ሽታዬ ምናለ ደግሞ ምክትል አፈ ጉባዔ ሆነው ተመርጠዋል።
በዚሁም መሰረት ቱባ ቱባ የኢህአዴግ ባለሥልጣናት ለ19 ዓመታት ያለምንም ተፎካካሪ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የቆዩት አቶ ስዩም መስፍንን ጨምሮ አቶ አዲሱ ለገሰ፣ ዶ/ር ካሱ ኢላላ፣ አቶ ተፈራ ዋልዋ፣ አቶ አባይ ፀሐዬ እና አምባሳደር ተሾመ ቶጋ ከነበሩበት የሥልጣን እርከን ተነስተዋል። በአቶ ስዩም ምትክ የምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ሆነው ተሹመዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ሲራጅ ፌጌሳ (በቀድሞ ቦታቸው)፣ የፍትህ ሚኒስትር አቶ ብርሃን ኃይሉ፣ በአንድ ላይ የተጨፈለቀው የሴቶች የህጻናትና ወጣቶች ሚኒስትር ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ፣ የጤና ሚኒስትር ደግሞ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኀኖም የተሾሙ ሲሆን ሌሎች የሚኒስትርነት ማእረጋት ሹመቶችም ተሰጥተዋል።
አቶ በረከት ስምኦን ቀድሞ በነበሩበት የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ተጠሪ ሆነው የተሾሙ ሲሆን፣ ከሥልጣናቸው የተነሱት ባለሥልጣናት በህዝባዊ ተቋማትና በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ በከፍተኛ አማካሪነት እንደሚሰሩ የውስጥ አዋቂዎች ጠቁመዋል።
በዛሬው ዕለት ሹመታቸው የፀደቀላቸው የሚከተሉት ናቸው:-
1) አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር (አዲስ ተሿሚ፣ ደኢህዴን/ኢህአዴግ፣ ወላይታ)፣
2) አቶ ሲራጅ ሬጌሳ የሀገር መከላከያ ሚኒስትር (ኢህአዴግ/ደኢህዴን፣ ስልጤ)፣
3) ዶ/ር ሽፈራው ተክለማርያም የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር (ኢህአዴግ/ደኢህዴን፣ ሐድያ)፣
4) አቶ ብርሃን ኃይሉ የፍትህ ሚኒስትር (ኢህአዴግ/ብአዴን፣ አማራ)፣
5) አቶ ጁነዲን ሳዶ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትር (አዲስ ተሿሚ፣ ኢህአዴግ/ኦህዴድ፣ ኦሮሞ)፣
6) አቶ ሶፊያን አህመድ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር (ኢህአዴግ/ኦህዴድ፣ ኦሮሞ)፣
7) አቶ ተፈራ ደርበው የግብርና ሚኒስትር (ኢህአዴግ/ብአዴን፣ አማራ)፣
8) አቶ መኮንን ማንያዘዋል የኢንዱስትሪ ሚኒስትር (አዲስ ተሿሚ፣ የፓርቲ አባል ያልሆኑ፣ አማራ)፣
9) አቶ አብዱረህማን ሼህ አህመድ የንግድ ሚኒስትር (አዲስ ተሿሚ፣ ሶህዴፓ፣ ሶማሌ)፣
10) አቶ ደሴ ዳርኬ የሣይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር (አዲስ ተሿሚ፣ ኢህአዴግ/ደኢህዴን፣ ሲዳማ)፣
11) አቶ ድሪባ ኩማ የትራንስፖርት ሚኒስትር (ኢህአዴግ/ኦህዴድ፣ ኦሮሞ)፣
12) አቶ ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር (አዲስ ተሿሚ፣ ኢህአዴግ/ህወሓት፣ ትግሬ)፣
13) አቶ መኩሪያ ኃይሌ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር (አዲስ ተሿሚ፣ ኢህአዴግ/ደኢህዴን፣ ጉራጌ)፣
14) አቶ አለማየሁ ተገኑ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር (አዲስ ተሿሚ፣ ኢህአዴግ/ኦህዴድ፣ ኦሮሞ)፣
15) ወ/ሮ ስንቅነሽ እጅጉ ማዕድን ሚኒስትር (አዲስ ተሿሚ፣ ኢህአዴግ/ኦህዴድ፣ ኦሮሞ)፣
16) አቶ ደመቀ መኮንን የትምህርት ሚኒስትር (ኢህአዴግ/ብአዴን፣ አማራ)፣
17) ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኀኖም የጤና ጥበቃ ሚኒስትር (ኢህአዴግ/ህወሓት፣ ትግሬ)፣
18) አቶ አሚን አብዱልቃድር የባህልና ቱሪዝም (አዲስ ተሿሚ፣ አፋር)፣
19) አቶ አብዱልፈታህ ሐሰን የሠራተኛና ማኅበራዊ ሚኒስትር (አዲስ ተሿሚ፣ ሶዴህፓ፣ ሶማሌ)፣
20) ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ የሴቶች፣ ወጣቶችና ህጻናት ጉዳይ ሚኒስትር (አዲስ ተሿሚ፣ ኢህአዴግ/ብአዴን፣ አማራ)፣
21) አቶ በረከት ስሞዖን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉ/ጽ/ቤት ኃላፊ ሚኒ/ርና የካቢኔ አባል (አዲስ ተሿሚ፣ ኢህአዴግ/ብአዴን፣ ትግሬ)፣
22) ወ/ሮ አስቴር ማሞ የመንግሥት ተጠሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ (አዲስ ተሿሚ፣ ኢህአዴግ/ኦህዴድ፣ ኦሮሞ)፣
23) አቶ መላኩ ፋንታ በሚኒስትር ማዕረግ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር (አዲስ ተሿሚ፣ ኢህአዴግ/ብአዴን)



