ጊንጪ ፖሊስ ካምፕ ላይ ቦምብ ተወረወረ
ጊንጪ ከተማ
በአራት ቀን ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ የተፈጸመው ጥቃት አሳስቧል
ኢዛ (ማክሰኞ የካቲት ፲፯ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 25, 2020)፦ በኦሮሚያ ክልል ጊንጪ ከተማ በአንድ የፖሊስ ካምፕ ውስጥ ቦምብ ተወረወረ። እንዲህ ያሉ ጥቃቶች መደጋገም አሳሳቢ ኾኗል።
ትናንት ምሽት ላይ ተፈጸመ በተባለው ጥቃት በወቅቱ በሥራ ላይ የነበሩ ሁለት የፖሊስ አባላት በጢስ ከመታፈናቸው በቀር የከፋ ጉዳት አልደረሰም ተብሏል።
ትናንት በጊንጪ የደረሰው የቦምብ ጥቃት በአንድ ሳምንት ውስጥ በኦሮሚያ ክልል በጦር መሣሪያ የታገዘ ሦስተኛው ጥቃት ኾኗል። የመጀመሪያው ዓርብ የካቲት 13 ቀን 2012 ዓ.ም. በቡራዩ የከተማው አስተዳደር የጸጥታ ዘርፍ ላይ በተተኮሰ ጥይት የኮማንደር ሰለሞን ታደሰን ሕይወት ያጠፉና ሦስት ሌሎች ሰዎችን ያቆሰሉ እንደነበር ይታወሳል።
ከሁለት ቀናት በፊት እሁድ የካቲት 15 ቀን በአምቦ ከተማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይንና ፓርቲያቸውን ለመደገፍ በወጡ ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ቦምብ ተወርውሮ 29 ሰዎች ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፤ ትናንት በጊንጪ ከተማ የተቃጣው ጥቃት በአራት ቀን ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ ጥቃቶች መፈጸማቸውን ያሳያል።
በጊንጪም ኾነ በሌሎቹ ሁለቱ ጥቃቶች ተጠርጣሪዎች ናቸው የተባሉ ሰዎች የተያዙ ሲሆን፣ እሁድ የካቲት 15 ቀን ማምሻውን በወጣ መረጃ ከዚህ ጥቃት ጀርባ ኦነግ ሸኔ የተባለው ቡድን እጅ እንዳለበት በኦሮሚያ ፖሊስ ኮምሽን መገለጹ አይዘነጋም። (ኢዛ)



