ኢትዮጵያ ነገ በአሜሪካ ሊካሔድ በነበረው የህዳሴ ግድብ ውይይት ላይ አልገኝም አለች
ታላቁ ህዳሴ ግድብ
ምክንያቷ ከባለድራሻ አካላት ጋር የምታደርገውን ውይይት ባለመጨረስዋ መኾኑን አስታውቃለች
ኢዛ (ረቡዕ የካቲት ፲፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 26, 2020)፦ በዋሽንግተን ዲሲ ነገ ሊጀመር በነበረው የታላቁ የህዳሴ ግድብ ላይ ኢትዮጵያ እንደማትገኝ ዛሬ አስታወቀች።
በአሜሪካ ነገ የካቲት 19 እና 20 ቀን 2012 ዓ.ም. የህዳሴ ግድቡን አስመልክቶ በግብጽ፣ በሱዳንና በኢትዮጵያ መካከል ሊካሔድ ታቅዶ በነበረው ስብሰባ ላይ ኢትዮጵያ እንደማትገኝ ያስታወቀው የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ነው።
ባለፉት ተከታታይ ወራት በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ሲደረግ በቆየው ውይይት ላይ ከሦስቱ አገራት ባሻገር የአሜሪካ የትሬዠሪ ቢሮ ሴክሬተሪና የዓለም ባንክ ፕሬዝዳንት በተዛቢነት የተገኙበት የሦስትዮሽ ድርድር በአሜሪካ ሲካሔድ የቆየ መኾኑ ይታወቃል።
ይህ ነገና ተነገወዲያ (የካቲት 19 እና 20) ኢትዮጵያ አልገኝበትም ያለችው ስብሰባ የተጠራው በአሜሪካ የትሬዠሪ ቢሮ ሴክሬተሪ ሲሆን፣ እንደተለመደው በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ነበር ሊካሔድ ታስቦ የነበረው።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ኢትዮጵያ የማትገኝበት ምክንያት ነው ብሎ ያቀረበው፤ የሶስትዮሽ የድርድር መድረክ የኢትዮጵያ ተደራዳሪ ቡድን በአገር ውስጥ ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚያደርገውን ውይይት ባላማጠናቀቁ መኾኑን ገልጿል። በመኾኑም ጥሪውን ላስተላለፈው የአሜሪካ የትሬዠሪ ቢሮ ምክንያቱን በመጥቀስ በተጠቀሰው ጊዜ መገኘት እንዳማይችል አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ድርድር ሲያደርጉ የነበሩት የኮሚቴ አባላት፣ ምሁራን፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተወከሉ ተሳታፊዎችን ጨምሮ፤ በአገሪቱ ውስጥ ባለድርሻ ናቸው የተባሉ አካላትን ጨምሮ የካቲት 9 ቀን 2012 ዓ.ም. ውይይት ማድግ መጀመሯን መዘገባችን አይዘነጋም። (ኢዛ)



