አቶ ዮሐንስ ቧያለው ከአማራ ማስ ሚዲያ ጋር ባደረጉት ቆይታ

አቶ ዮሐንስ ቧያለው

የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ፕሬዝዳንት ኾነው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾሙት ትናንት ነበር

ኢዛ (ረቡዕ የካቲት ፲፰ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 26, 2020)፦ በትናንትናው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ ፕሬዝዳንት እንዲኾኑ የተሾሙት አቶ ዮሐንስ ቧያለው፤ ሹመቱን ለመቀበል እንደሚቸገሩ ዛሬ ገለጹ።

አቶ ዮሐንስ ይህንን የገለጹት ለአማራ ማስ ሚዲያ ኤጀንሲ ሲሆን፤ “አሁን ተቋሙ ባለው የሕዝብ አመለካከት በተቋሙ መሥራት የምችልበት ሁኔታ ስለሌለ የቀረበውን ሹመት ለመቀበል ያስቸግረኛል” በማለት መግለጻቸው ተዘግቧል።

በዚህ ተቋም ከመሾማቸው ቀደም ብሎ በፌዴራል ደረጃ እንደሚመደቡ እንጂ በየትኛው መሥሪያ ቤት እንደሚመደቡ ያወቁ እንዳልነበርም ገልጸዋል።

ምደባውን ከሰሙ በኋላ ምደባውን እንደማይቀበሉ ሪፖርት ማድረጋቸውን ገልጸዋል ተብሏል።

በዚሁ ዘገባ መሠረት፤ አቶ ዮሐንስ በዚያ ተቋም መሥራት ቢኖርብኝ እንኳን ተቋሙ አሁን ባለው የሕዝብ ተቀባይነት፤ በተቋሙ መሥራት የምችልበት ሁኔታ ስለሌለ፤ የቀረበውን ሹመት ለመቀበል እንደሚቸገሩ ነው። አያይዘውም የሕዝቡን ትግል በተለያየ መልኩ አስተዋጽኦ በማድረግ፤ የፓርቲው ጉዞ እንዲጠነክር በማድረግ በሌላ አግባብ ላገለግል እችላለሁ እንጂ፤ አሁን በተመደብኩበት ተቋም ባለው ስያሜና ብራንድ (በሕዝብ ዘንድ ባለው ተቀባይነት) ለማገልገል እንደማይችሉ ለሚመለከተው አካል ቦርድ ሰብሳቢ ዛሬ ጠዋት ማሳወቃቸውን ይኸው የአማራ ማስ ሚዲያ ኤጀንሲ መረጃ አመልክቷል።

የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ አብዛኛው አመራሮች የአስተሳሰብም የተግባርም አንድነት የተላበሰ፣ ብሎም ፍቅርና የጋራ አንድነት ያለው እንደኾነ የገለጹት አቶ ዮሐንስ፤ በአመራሩ መካከል መከፋፈል አለ ብለው የሚሉ ወገኞች የተሳሳቱ መኾናቸውን ገልጸዋል። ነገር ግን ክፍተት እንዲፈጠር፣ የቡድነኝነት ስሜት እንዲጦዝ፤ ጎጃም፣ ወሎ፣ ሸዋ፣ ጎንደር ተብሎ እንዲከፋፈልና ገና በማቆጥቆጥ ላይ ያለው የአማራ ብሔርተኝነት እንዲዳከም የሚፈልጉ ወገኖች ከውስጥም ከውጭም እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

አቶ ዮሐንስ በአማራ ክልል በምክትል መስተዳድር ማዕረግ የአዴፓ/ብልጽግና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ወደ ፌዴራል በኃላፊነት ይዛወራሉ ተብለው ከክልል አመራርነታቸው ከለቀቁት ባለሥልጣናት አንዱ መኾናቸው ይታወቃል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ