ዛሬ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በምርጫው መራዘም ላይ ይወያያል
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን በተመለከተ ያቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ ላይ ይመክራል
የምርጫውን ጉዳይ ጨምሮ አምስት አጀንዳዎችን ያጸድቃል ተብሏል
ኢዛ (ሐሙስ ሚያዝያ ፳፪ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. April 30, 2020)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ለማካሔድ የሚያስችል ሁኔታ ባለመኖሩ፤ ምርጫ 2012 በሰሌዳው መሠረት ምርጫውን ነኀሴ 23 ቀን 2012 ዓ.ም. ለማካሔድ እንደማይችል ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ መርምሮ ያጸድቃል ተብሏል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ሐሙስ ሚያዝያ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. በሚያካሒደው መደበኛ ስብሰባው፤ ምርጫውን በተመለከተ በቅርቡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበውን ውሳኔ ከማጽደቅ ባሻገር፤ ቀጣይ የመፍትሔ ሐሳብ እንዲቀርብ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይመራል ተብሎ ይጠበቃል።
ምክር ቤቱ በዛሬው ዕለት በሚያደርገው 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 15ኛ መደበኛ ስብሰባ ውሳኔ ከሚያሳልፍበት የምርጫ ጉዳይ ባሻገር፤ በሌሎች አራት አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሏል። (ኢዛ)



