Eng. Takele Uma

ነኀሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባነታቸው የተነሱትና አሁን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር የኾኑት ኢንጂንየር ታከለ ኡማ

የኢዜማን መግለጫ ኮንነው፤ ለአርሶ አደሮች የሰጠነው 20 ሺህ ቤት ነው ብለዋል
የመሬት ወረራ ላይ እርምጃ ስንወስድ ነበር

ኢዛ (ማክሰኞ ነኀሴ ፳፮ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. September 1, 2020)፦ ትናንት ረፋድ ላይ ጀምሮ የብዙዎችን ዓይንና ጆሮ የያዘው በአዲስ አበባ ተፈጸመ ስለተባለው ሕገወጥ የመሬት ወረራና ያልተገባ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እደላን ለተመለከተው የኢዜማ መረጃ በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል ተብለው የሚታመኑት የቀድሞው የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂንየር ታከለ ኡማ፤ የኢዜማን መግለጫ በመኮነን ድምፃቸውን አሰሙ።

ዛሬ ማክሰኞ ነኀሴ 26 ቀን 2012 ዓ.ም. በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው “ሐሰተኛ መረጃ አገር ማፍረስ ይቻል ይኾናል እንጂ፤ አገር አይገነባም፤ የፖለቲካ ትርፍም የለውም” በሚል ርዕስ ባሰፈሩት መልእክት፤ የኢዜማ መግለጫ ሐሰተኛን የተጋነነ ስለመኾኑ ጠቅሰዋል።

ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ እርሳቸውና ካቢኔያቸው ጠንካራ እርምጃ ሲወስዱበት የነበረ ጉዳይ ስለመኾኑ የጠቀሱት ኢንጂንየር ታከለ፤ በመሬት ወረራ ላይ እርምጃ ሲወሰድ ግን የዛሬ ተቺዎች (ኢዜማዎችን ማለታቸው ነው)፤ ሰብአዊ መብት ተነካ፤ ዜጎች ተፈናቀሉ በማለት ዘመቻ የከፈቱብን ናቸው ብለዋል።

በሕገወጥ መንገድ ቆጣቢ ላልኾኑ ሰዎች የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) ስለመታደላቸው ለሚጠቅሰው የኢዜማ መግለጫ፤ ኢንጂንየር ታከለ በሕገወጥ መንገድ የተላለፈ ቤት ያለመኖሩን በመግለጽ፤ 20 ሺህ ኮንዶሚኒየም ቤቶች እደላ መደረጉንና ይኽም ግን ከአንድ ዓመት በፊት በካቢኔ የተወሰነና የተተገበረ መኾኑን አመልክተዋል። እንደውም በራሳቸው መሬት ላይ በተሠራ ሕንፃ ዘበኛ እና ተሸካሚ ከሚኾኑ 67 ሺህ አባወራዎች መኻከል የተሰጠው ለ20 ሺህ ብቻ መኾኑን ያመለከቱት ኢንጂንየር ታከለ፤ ለቀሪዎቹ ያለመሰጠቱም የሚቆጫቸው መኾኑን በዚሁ መልእክታቸው አስፍረዋል።

በዚህ የኢዜማን መግለጫ በኮነኑበት የዛሬው መልእክታቸው ላይ ማሰሪያ ያደረጉት፤ “ሐሰተኛ መረጃ ድካማችንን ለማጠልሸት ቢሞከርም፤ ሥራችን ይናገራልና ፍርድ የሕዝብ ነው!” በማለት ነው።

በትናንቱ የኢዜማ መግለጫ 95 ሺህ የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚንየም) ያለአግባብ የተላለፉ ስለመኾኑ፤ እንዲሁም ከ213 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት በወረራ ስለመያዙና ለዚህም የአዲስ አበባ አስተዳደር ባለሥልጣናት ሊጠየቁ ይገባል ብሎ መግለጹ ይታወሳል። በተወሰኑ አካባቢዎች በተደረገ ጥናት የታየው የመሬት ወረራ፤ ከዚህ ቀደም ታይቶ የማይታወቅ ስለመኾኑም ገልጿል።

ኢንጂንየር ታከለ ኡማ ባለፈው የዛሬ ሁለት ሳምንት ነኀሴ 12 ቀን 2012 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባነት ተነስተው የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትር ኾነው ሲሾሙ፤ በምትካቸው ወ/ሮ አዳነች አቤቤ መተካታቸው አይዘነጋም። የኢንጂንየር ታከለ ኡማ አጭር መልእክትት ከዚህ በታች ሰፍሯል። (ኢዛ)

“በሐሰተኛ መረጃ አገር ማፍረስ ይቻል ይኾናል እንጂ፤ አገር አይገነባም፤ የፖለቲካ ትርፍም የለውም!!” ኢንጂንየር ታከለ ኡማ

ለዚህ ምላሽ ለመስጠት ተገቢው ቦታ ላይ ባልገኝም ከዚህ የመጓተት ፖለቲካ አስተሳሰብ መውጣት አለመቻል ግን ትልቅ ሕመም እንደኾነ ይሰማኛል።

የመሬት ወረራን በተመለከተ ከመጀመሪያዋ ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻዋ ዕለት ድረስ ጠንካራ የኾነ እርምጃ ስንወስድበት የቆየንበት ጉዳይ ነው።

በተለያዩ ጊዜዎች የወሰድናቸው እርምጃዎችም ሕያው ምስክሮች ናቸው።

እኛ ሕገወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል እርምጃ ስንወስድ፤ የዛሬ ተቺዎች የሰብአዊ መብት ተነካ፣ ዜጎች ተፈናቀሉ ብለው ዘመቻ ከከፈቱብን ውስጥ ነበሩ።

ለ20 ሺህ አርሶ አደሮች የተሰጡ የኮንዶሚኒየም ቤቶችን በተመለከተም፤ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት በካቢኔ የተወሰነና የተተገበረ ነው። በድብቅ የተተገበረም ሳይኾን በመንግሥት ሚዲያም በይፋ የተገለጸ ነበር።

ከመሬታቸው ተፈናቅለው ሜዳ ላይ ከወደቁ በራሳቸው መሬት ላይ በተሠራ ሕንፃ ዘበኛ እና ተሸካሚ ኾነው ከቀሩ 67 ሺህ አባወራዎች መኻል የከፋ ችግር ላይ ለወደቁት 20 ሺህ ኮንዶሚንየም ቢያንስ እንጂ የሚበዛ አይደለም። ስሕተትም ከኾነ ለ67 ሺህውም አለመስጠታችን ነው። ከዚህ ውጭ በሕገወጥ መንገድ የተሰጠ ምንም ዐይነት ቤት የለም።

ይህ ሥራችን በተደጋጋሚ በይፋ ስንናገር እንደነበረው የምናፍርበት ሳይኾን የምንኮራበት ነው። በግፍ የተገፋን፣ በግፍ ከመሬቱ የተፈናቀለን አርሶ አደር መካስ ያኮራናል!

በዙሪያዋ ካሉት አርሶ አደሮች ጋር በፍቅር ተሳስባ የምትኖር የተሰናሰለች ከተማ እንጂ በዙሪያዋ ካሉት ሕዝቦች ጋር የተቀያየመች ከተማ እንድትኖር አንሻም ነበርና። ይህ ደግሞ የከተማዋ ነዋሪዎች ፍላጎት መኾኑንም እንገነዘባለን።

አንድም ቀን በግፍ ለተፈናቀሉ አርሶ አደሮች የመቆርቆር ስሜት አሳይቶ የማያውቅ ቡድን፤ ዛሬ የአርሶ አደሮችን ጉዳት ለተቀባይነት ማግኛ መጠቀሚያ ሲያደርገው ማየት ያሳዝናል። ነገር ግን በሐሰተኛ እና በተጋነነ መረጃ ጠንካራ መምሰል እንጂ መኾን አይቻልም።

በሐሰተኛ መረጃ ድካማችንና ሥራችንን ለማጠልሸት ቢሞከርም፤ ሥራችን ይናገራልና ፍርድ የሕዝብ ነው!

የቀድሞው የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢንጂንየር ታከለ ኡማ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!