አርቲስት መስፍን ጌታቸው አረፈ

አርቲስት መስፍን ጌታቸው
ለሞት የዳረገው ኮቪድ 19 ነው
ኢዛ (እሁድ ሚያዝያ ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 25, 2021)፦ በኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ምክንያት ታምሞ በኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የሕክምና እርዳታ ሲደረግለት የቆየው አርቲስት መስፍን ጌታቸው በተወለደ 50 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
አርቲስት መስፍን ጌታቸው በደራሲነት፣ በአዘጋጅነት እና በትወና በርካታ ሥራዎችን የሠራ ሲሆን፤ በራዲዮ ድራማዎች እና በፊልም ሥራዎቹ ታዋቂ ሁለገብ አርቲስት ነበር። በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ታዋቂ የኾነው “ሰው ለሰው” የተሰኘው ተከታታይ ድራማ ደራሲ እና ተዋናይ እንደነበር ይታወቃል።
በኢትዮጵያ ራዲዮ ዝነኛ የነበረ “የቀን ቅኝት” የተሰኘው ድራማ ደራሲ የነበረው አርቲስት መስፍን ጌታቸው፤ “መንታ መንገድ” የተሰኘው ተከታታይ የራዲዮ ድራማን ጨምሮ በርካታ የራዲዮ ሥራዎች ላይ ተውኗል።
አርቲስት መስፍን ጌታቸው “ዙምራ” የተሰኘው ፊልም አዘጋጅ ሲሆን፤ በቴሊቭዥን ከተላለፉት ተከታታይ ድራማዎች ውስጥ “ዘመን” በተሰኘው ፊልም ላይ ተውኗል።
አርቲስት መስፍን ጌታቸው ባለትዳር እና የሁለት ሴቶች እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበር።
የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ለአርቲስቱ ቤተሰቦች፣ ዘመዶች፣ ወዳጅ እና አድናቂዎች መጽናናትን ይመኛል። (ኢዛ)