የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በዘጠኝ ወር 55.8 ቢሊዮን ብር ገቢ አገኘ
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
13.4 ቢሊዮን ብር አትርፏል
ኢዛ (ረቡዕ ሚያዝያ ፳ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. April 28, 2021)፦ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2013 ዓ.ም. በጀት ዓመት በዘጠኝ ወራት ከ55.8 (ሃምሳ አምስት ነጥብ ስምንት) ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማሰባሰቡን እና ከታክስ በፊት 13.4 (አሥራ ሦስት ነጥብ አራት) ቢሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ።
የበጀት ዓመቱ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ውጤታማ ሊባል የሚችል መኾኑንም ባንኩ ዛሬ በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት አቶ አቤ ሳኖ የዘጠኝ ወሩን የባንኩን የሥራ አፈጻጸም አስመልክተው እንደገለጹት፤ በዘጠን ወር ውስጥ ባንኩ ያሰባሰበው ገቢ በባንኩ ታሪክ ከፍተኛ የሚባል ነው።
በዘጠኝ ወር ውስጥ ካገኘው 55.8 ቢሊዮን ብር ውስጥ የአንበሳው ድርሻ የሚይዘው ከብድር ወለድ የተገኘ ገቢ ሲሆን፤ ይህም 46.5 (አርባ ስድስት ነጥብ አምስት) ቢሊዮን ብር ነው። ከኮምሽን እና የአገልግሎት ክፍያ ደግሞ 8.8 (ስምንት ነጥብ ስምንት) ቢሊዮን ብር ገቢ ሲያገኝ፤ 231 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከተለያዩ ገቢዎች የተገኘ መኾኑ ተገልጿል።
በዘጠኝ ወሩ ያገኘው ትርፍም በ2012 ዓ.ም በጀት ተገኝቶ ከነበረው ትርፍ አንጻር ወደ 3 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው። (ኢዛ)



