መንግሥት በትግራይ ክልል የተናጠል የተኩስ አቁም አወጀ
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት
የእርሻ ወቅት እስኪጠናቀቅ ድረስ ይቆያል የተባለው ተኩስ አቁም ከዛሬ ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ይጀምራል
ኢዛ (ሰኞ ሰኔ ፳፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. June 28, 2021)፦ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከዛሬ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ በትግራይ ክልል ካለምንም ቅድመ ሁኔታ የተናጠል የተኩስ አቁም ማወጁን አስታወቀ። የተኩስ አቁሙ የእርሻ ወቅት እስኪጠናቀቅ ድረስ ይቆያል።
መንግሥት ይህንን ያወጀው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥያቄ ማቅረቡ ከተሰማ ከደቂቃዎች በኋላ ነው።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረግ ጥያቄ ያቀረበው ባለፈው ሳምንት ሲሆን፤ በይፋ የተነገረው ከአንድ ሰዓት በፊት ነው። ይህ መረጃ ከተሰማ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ከጊዜያዊ አስተዳደሩ የቀረበውን ጥያቄ ተመርኩዞ፤ ያለቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም አውጇል።
የተኩስ አቁሙ ይህ የእርሻ ወቅት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚቆይ ስለመኾኑም አስታውቋል። የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጠው ሙሉ መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)
ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በትግራይ የተናጠል ተኩስ አቁም ስመወሰኑ የሰጠው መግለጫ
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ባለፉት ሰላሳ ዓመታት በአገሪቱ ላይ ትውልድ ገዳይ መከራ ማስከተሉ ይታወቃል። ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከዳር ባደረጉት መራራ ትግል ይህ መከራ ተወግዷል።
ያለፉ በደሎችን በይቅርታ ለመሻገር የለውጡ ኃይል አድርጎት የነበረውን ተደጋጋሚ ጥረት ማንም የሚያስታውሰው ነው። በፍቅር እንደመር፣ በይቅርታ እንሻገር በሚለው መርሐችን መሠረት፣ ሁልጊዜ እያፈረስን ከምንገነባ፣ ያለፈውን በይቅርታ፣የሚመጣውን በካሣ ለማለፍ ጥረት አድርገን ነበር። የኢትዮጵያ ሕዝብም ለሁላችንም የመታረሚያ እድል ሰጥቶን ነበር።
ይሁን እንጂ የሕወሓት ቡድን ኢትዮጵያን አፈራርሼ ፍርስራሹን እየሸጥኩ ካልተጓዝኩ በሚል የሕዝቡን ይቅርታ ከቁብ አልቆጠረውም። ራሱንም ከለውጥ ሒደቱ ከማውጣት አልፎ ለውጡን ለማደናቀፍ መሰናከል ማብዛት ጀመረ። በዚህ አቋሙም ተደጋጋሚ የኾኑ የመታረሚያ ዕድሎችን አበላሸ። ይባስ ብሎ ግጭቶችን እየጠነሰሰ፣ እልቂት እየደገሠ አገር ለማፍረስ መሥራት ቀጠለ። በኢሕአዴግ እና በመንግሥት መድረኮች ችግሩን በውይይት ለመፍታት የነበረውን እድል አጨናገፈው። በአገር ሽማግሌዎች፣ በሃይማኖት አባቶች እና ሕወሓትን ከፌዴራል መንግሥት ጋር ሊያቀራርቡ ይችላሉ በተባሉ አካላት በኩል የተሞከሩ የሽምግልና ሙከራዎች ሁሉ በሕወሓት አልጠግብ ባይነት ከሸፉ።
ይህ ሁሉ ቢኾንም እንኳን የከፋ አገራዊ ቀውስ እስካልተፈጠረ ድረስ ችግሩን በሆደ ሰፊነት ማየት ይገባል የሚል አቋም መንግሥት ነበረው። የሕወሓት ቡድን ለክልሉ የተላከውን በጀት ለጦርነት ድግስና ለጥፋት እያዋለው መኾኑ እየታወቀ ሕዝቡ እንዳይጎዳ ሲባል የክልሉ በጀት ሳይቋረጥ እንዲያውም ተጨማሪ በጀት ተሰጥቶታል፤ ክልሉ በፌዴራል መንግሥት የነበረው ውክልና ሳይነካ በሰላም ለመቀጠል ተሞክሯል። በአገሪቱ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ግጭትና መፈናቀል እያስከተለ እንኳን የትግራይን ክልል ከማስተዳደር ያገደው አልነበረም።
ይሄንን ሁሉ የመንግሥት ትእግሥት እንደ ፍርሃት የቆጠረው የሕወሓት ቡድን በጥቅምት ወር በሰሜን ዕዝ ላይ አገር ሊያፈርስ የሚችል ጥቃት ፈጸመ። ከሃያ ዓመታት በላይ ድንበር ሲጠብቅና የትግራይን ሕዝብ ሲረዳ በኖረው የሰሜን ዕዝ ላይ አሰቃቂ ግፍ ሠራ። አንዳንዶችን ገደለ፤ አንዳንዶችን አረደ፤ በአንዳንዶች ላይ ኢሰብአዊ ተግባር ፈጸመ፤ ሴት ወታደሮችን አዋረደ። የሰሜን ዕዝን መሣሪያ ወስዶ በኢትዮጵያ ላይ ግልጽና ቅርብ አደጋ ደቀነ።
የመከላከያ ሠራዊታችን በሕገ መንግሥቱ በተጣለበት የአገርን ሉዓላዊነትና ህልውና የመጠበቅ ኃላፊነት መሠረት፣ በወሰደው ሕግ የማስከበር ርምጃ የሕወሓት ቡድን ከጥቅም ውጭ ኾነ። መዋቅሩ ፈረሰ፤ ወታደራዊ አቅሙ ተደመሰሰ፤ አመራሩ ምርኮኛ ሙትና ቁስለኛ ኾነ፤ የቀረውም ተበተነ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሕግ የማስከበር ዘመቻ ሲከፍት ዓላማው የሕወሓትን ቡድን ከጥቅም ውጭ ማድረግና ኢትዮጵያን መታደግ ነበር። በዚህ ዓላማም ቡድኑ ከዚህ በኋላ አገራዊ አደጋ ከማይደቅንበት ደረጃ ወርዶ፣ የተረፈው ኃይል የተበተነ ርዝራዥ ኾኗል። አደጋ ሊያደርስበበት የነበረውን የጦር መሣሪያም ተነጥቋል። የኢኮኖሚና የፖለቲካ ዐቅሙም ኢምንት ኾኗል። በአጎራባች አገሮችና ክልሎች የነበረው የጥፋት ሃይሉ ማምለጫ መንገድ በመከላከያ ሃይል ስለተዘጋ ወንጀለኞች ያሚያመልጡበት እድል ተመናምኗል። በዚህም የተነሳ ፈፋ ለፈፋ እንደ (ዝንጀሮ) እየዘለለ የሚኖር ሽፍታ ኾኗል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሕግ የማስከበር ዘመቻውን በዋናነት ካጠናቀቀ በኋላ ፊቱን ወደ መልሶ ግንባታ በማዞር የሕወሓት ቡድን ባደረሰው ጥፋት የወደሙትን መሠረተ ልማቶች ለመገንባት የሕይወት መስዋእትነት ጭምር ተከፍሎ ሰፊ ርብርብ አድርጓል። በግጭቱ የተጎዱ ወገኖችን ለመርዳትና አገልግሎቶች እንዲጀመሩ ለማድረግም ሰፊ ሥራ ሠርቷል። ይሄንን የእርዳታና የመልሶ ግንባታ ሥራ ለማገዝ የፌዴራል መንግሥቱና የክልል መንግሥታት ከመቶ ቢልዮን ብር በላይ ወጭ አውጥተዋል።
ከሰላሳ በላይ የእርዳታ ድርጅቶችና አራት መቶ የሚጠጉ ሠራተኞቻቸው ክልሉን ገብተው እንዲረዱ አድርጓል። ሌላው ቀርቶ የመገናኛ ችግር እንኳን እንዳይፈጠር በተለየ መልኩ ለዓለም አቀፍ ድርጅቶች የራሳቸው የመገናኛ መሣሪያዎችን ለመጠቀም የሚያስችል እድል ተፈጥሯል። አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የሚዲያ ተቋማት ሒደቱን እንዲዘግቡ ተፈቅዷል። የቪዛና የጉዞ ፈተናዎች እንዳይኖሩ ሁኔታዎች ሁሉ ተመቻችተዋል።
በዚህ ጉዞ ውስጥ ግን አንዳንድ ዓለም አቀፍ አጋሮቻችን ችግሩን ለመገንዘብ ፍላጎት አላሳዩም። ለእርዳታ የከፈትንላቸውን መሥመርም ላልተገባ ተግባር ሲጠቀሙበት ታይተዋል። አንዳንድ ሚዲያዎችም ከእውነት በተቃራኒ መቆምን መርጠዋል።
ከሚደርሱት እርዳታዎች ከሰባ በመቶ በላይ የሚሸፍነው የኢትዮጵያ መንግሥት መኾኑ እየታወቀ ለመንግሥት ተግባር ዕውቅና ነፍገዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የትግራይ ሕዝብ ከሚጎዳ ጫናውን ተሸክሞ ማለፍ ይሻላል በሚል መርሕ ይሄን ሁሉ ጫና ተቋቁሞ አልፏል።
የትግራይን ሕዝብ ችግር የመፍታት ቀዳሚውና ዋናው ኃላፊነት የኢትዮጵያ መንግሥት እንጂ እርዳታ ሳይሰጡ ስለ እርዳታ የሚያወሩ አካላት እንዳይደለ በማመን የተቻለውን ሁሉ አድርጓል።
ከሕግ ማስከበር ዘመቻው በኋላ የነበረው ጊዜ እርዳታ ለማድረስ፣ መንግሥታዊ አገልግሎቶችን ለማስጀመር፤ የጸጥታና የፍትሕ አካላትን ለማሠልጠንና ለማሠማራት፣ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት፣ ለመንግሥት ሠራተኞች ደመዝ ለመክፈል፣ ሕዝቡን አስቀድሞ ሕወሓት ካቆራረጠው ወገኑ ጋር ለማገናኘት ውሏል። ከዚሁ ጎን ለጎን የተበተነውን ሽፍታ አመራር ለመያዝ ባደረግነው ዘመቻ ዋና ዋናዎቹ አንድም ተደምስሰዋል፤ ወይም ተይዘዋል። የቀሩትም በአገር ላይ አደጋ ከማድረስ አንፃር ትርጉም የሌላቸው ኾነዋል።
ከላይ የተገለጸው ሁኔታ እንዳለ ኾኖ ሕግ ማስከበር ሁኔታ ጎን ለጎን የክልሉን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት በኢትዮጵያውያንና በኢትዮጵያ ወዳጆች ሲቀርቡ የነበሩ የመፍትሔ ሐሳቦችን የፌደራል መንግስት ስያጤናቸው ቆይቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በተካታታይ ያቀረበውን ጥያቄ መንግሥት ከተለያየ አቅጣጫ ተመልክቶታል። በአንድ በኩል አካባቢው ከሚመራ አካል የቀረበ በመኾኑ፤ በሌላ በኩል ጥያቄው ከመቅረቡ በፊት በተለያየ ጊዜ ከክልሉ ተወላጆች፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት የተደረገበት መኾኑን ከግምት ውስጥ አስገብተናል።
በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ሕዝብና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከመቸውም በላይ ለአገራችን ሰላም የሰጡት ልዩ ትኩረት ከግምት ውስጥ ገብቷል። ይህንንም ሰላም የኢትዮጵያ አንዱ አካል የኾነውን የትግራይ ሕዝብ ተቋዳሽ ሊኾን ይገባል ተብሎ ስለሚታመን። የትግራይም ሕዝብ ሰላምና ለውጥ ፈላጊ መኾኑ በተለያዩ መንገዶች ሲገልጽ የቆየ መኾኑን ስለሚታወቅ። የአገሪቱን ሉዓላዊነት ከውጭ ኃይሎች ከተሰነዘሩ ትንኮሳዎች ለመከላከልና ሁለተኛውን ዙር የሕዳሴ ግድብ ለመሙላት ትኩረት መስጠት የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ በመኾኑ።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንደገለጠው፣ መላው ሕዝብም እንደሚረዳው፣ የተበተነው የሕወሓት የጥፋት ኃይል በሚሽሎከሎኩባቸው አካባቢዎች ገበሬው ተረጋግቶ ወደ እርሻ ሥራ መግባት አልቻለም።
ባለፈው አመት የአምበጣ መንጋ በስፋት ያጠቃው ክልል በመኾኑ የግብርና ሰብል ምርት በበቂ ሁኔታ አላገኝም፤ ከአንበጣ የተረፈውን መሰብሰብ እንዳይችል በመሰብሰብያ ግዜው በሕዝብ ስም የሚነግደው ሕወሓት አከባቢውን የግጭት ቀጣና አደረገው። በዚህ ሁኔታ ይሄንን ክረምት ያለ እርሻ ሥራ የሚያሳልፍ ከኾነ፣ ለገበሬው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይኾንበታል። የሕወሓት የጥፋት ኃይል በሚነዛው ሽብር የተነሳ ሕዝቡ የጦርነት ጋሻ ኾኖ እየተማገደ ይገኛል። ሲዋጋ ሚሊሻ ሲጠቃ ሲቪል የሚኾን ኃይል እየተፈጠረ ነው። በዚህ የተነሳ ሕወሓት በፈጠረው ቀውስ ቤታቸው የፈረሰባቸው፣ እርሻቸው የተስተጓጎለባቸው፣ አካባቢያቸውን ለቅቀው የተፈናቀሉ ሁሉ የተረጋጋ ኑሮ ለመኖር አልቻሉም።
በአንድ በኩል እነዚህን ነገሮች ከግምት ውስጥ በማስገባት፤ በሌላ በኩል ደግሞ በረሐ ከተበተነው ኃይል ውስጥ ሁኔታዎች ቢመቻቹለት ወደ ሰላም ሊመጣ የሚችል ኃይል ይኖራል ተብሎ ስለታመነ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩን ጥያቄ መንግሥት በአዎንታዊነት ተቀብሎታል።
ይህ እንደተጠበቀ ኾኖ ዋነኞቹን የጥፋት መሪዎች ለሕግ የማቅረብ ስራ እና፡የተጀመረው የምርመራ ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይኾናል።
በዚህም መሠረት ገበሬው ተረጋግቶ የእርሻ ሥራውን እንዲከውን፣ የእርዳታ ሥራው ከወታደራዊ እንቅቃሴ ነጻ ኾኖ እንዲሠራጭ፣ ሰላምን የሚመርጡ የሕወሓት ርዝራዥ አካላት ወደ ሰላም መንገድ እንዲመጡ፤ ሳያውቁ ርዝራዡን የጥፋት ኃይል የተከተሉ እንደገና ለማሰብና ወደ ሰላማዊ መንገድ ለመምጣት እድል እንዲያገኙ ለማስቻል፣ ይህ የእርሻ ወቅት እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚቆይ ያለቅድመ ሁኔታ በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ በተናጠል የተኩስ አቁም ከዛሬ ከሰኔ 21 ቀን 2013 ጀምሮ መንግሥት አውጀዋል።
ሁሉም የፌዴራልና የክልል ሲቪልና ወታደራዊ ተቋማት፣ ከመንግሥት በሚሰጣቸው ዝርዝር አፈጻጸም መሠረት ይሄን የተኩስ አቁም እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ ታዝዘዋል። ይሄን መልካም እድል ለክፉ የሚጠቀሙ ወገኖች ካጋጠሙ ግን አስፈላጊው ሕግን የማስከበር ተግባር እንደ አግባቡ የሚከናወን ይኾናል።
የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት



