Ethiopia Zare (ዓርብ ነሐሴ 15 ቀን 2001 ዓ.ም. August 21, 2009)፦ በኢትዮጵያ የእስልምና ዕምነት ተከታዮች የረመዳንን ፆም ዛሬ ዓርብ ነሐሴ 15 ቀን 2001 ዓ.ም. ጀምረዋል። የአውሮፓ ሙስሊሞችም እንዲሁ በዛሬ ዕለት ፆሙን የሚጀምሩ ሲሆን፣ የሰሜን አሜሪካ ሙስሊሞች ደግሞ ነገ ቅዳሜ ነሐሴ 16 ቀን እንደሚጀምሩ ታውቋል።

 

ትናንት ምሽት ላይ ስትጠበቅ የነበረችው ጨረቃ ባለመታየትዋ የረመዳን ፆም ነገ ቅዳሜ ነሐሴ 16 ቀን 2001 ዓ.ም. የሚጀመር መሆኑን ለመረዳት ችለናል። የረመዳን ፆም የሚጀመረው ጨረቃን መሠረት ባደረገው የእስልምና የቀን መቁጠሪያ (ሒጅራ) ዘጠነኛው ወር ላይ ሲሆን፣ ይኸውም ቅዱስ ቁርዓን ለነብዩ መሐመድ የተገለጸለት እንደሆነ የእስልምና እምነት አዋቂዎች ይናገራሉ።

 

የእስልምና የቀን መቁጠሪያ (ሒጅራ) 12 ወራቶች ያሉት በጨረቃ ላይ የተመሰረተ የቀን መቁጠሪያ ሲሆን፣ በዓመት 354 ወይንም 355 ቀናት ሲኖሩት፤ በርካታ የሙስሊም ሀገራት የሚጠቀሙበት ከመሆኑም በላይ የእስልምና በዓላትን ለመቁጠር በመላው ዓለም ያለው ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ይገለገልበታል።

 

በዚህ የአንድ ወር የረመዳን የፆም ወቅት በተለይም አዋቂዎችና በጉዞ ላይ ካልሆኑና ካልታመሙ በቀር መፆም እንዳለባቸው የእስልምና እምነት ይደነግጋል። በፆሙ ወቅት አንድ ሙስሊም ከንጋት (ፀሐይ ከመውጣትዋ በፊት) ጀምሮ እስከ ምሽት (ፀሐይ እስከምትጠልቅ ድረስ ከምግብ፣ ከመጠጥ፣ ከሲጋራ፣ ከሺሻ እና ከወሲብ መቆጠብ የሚኖርበት ሲሆን፤ እነኝህ የተከለከሉትን ነገሮች ፀሐይ ከጠለቀችበት እስከ ከመውጣትዋ በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ መጠቀምና ማድረግ ይችላል።

 

በእስልምና ዕምነት ፆም ምዕመኑን ትዕግሥት፣ ትህትና እና መንፈሣዊ ትምህርት ይሰጠዋል ተብሎ ይታመናል። ረመዳን ለአላህ ሲባል የሚፆም ፆም እንደሆነና ሙስሊሙ ምዕመን ለሠራው ኃጢያት ምህረትን የሚጠይቅበት፣ ዕለት ተዕለት ለሚሠራቸው ኃጢያቱና ከሠይጣን ፈጣሪው ይጠብቀው ዘንድ የሚፀልይበት እንደሆነና ራሱን ከኃጢያት የሚያነፃበት ወቅት መሆኑን የእምነቱ ሊቃውንት ያስረዳሉ።

 

የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ለመላው የእስልምና ዕምነት ተከታዮች መልካም የረመዳን ፆም ይሆንላችሁ ዘንድ ከልብ ትመኛለች።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ