ፕ/ት ባራክ ሁሴን ኦባማ የመልካም ምኞት መግለጫ አስተላለፉ

23 ሚሊዮን ሙስሊሞች ረመዳንን በአስቸጋሪ ሁኔታ አሳለፉ

Ethiopia Zare (እሁድ መስከረም 10 ቀን 2002 ዓ.ም. September 20, 2009)፦ ኢትዮጵያውያን የእስልምና ኃይማኖት ተከታዮች የአንድ ሺህ አራት መቶ ሠላሳኛውን የኢድ አልፈጥር (ረመዳን) በዓል ዛሬ እሁድ መስከረም 10 ቀን 2002 ዓ.ም. ያከብራሉ። በመላው ዓለም ያሉ ሙስሊሞችም 1430ኛው የረመዳን በዓል ያከብራሉ። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማና ባለቤታቸው የመልካም ምኞት መግለጫ ሰጥዋል።

 

የሙስሊም መሠረት እንዳላቸው የሚታወቁት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ባራክ ሁሴን ኦባማ ትናንት ረመዳንን በሰሜን አሜሪካ ላከበሩትና በዓለም ላይ ላሉ ሙስሊሞች በራሳቸው፣ በባለቤታቸውና በመንግሥታቸው ስም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። “በአሜሪካን እና በመላው ዓለም ይህንን የተቀደሰ በዓል ለሚያከብሩ ሙስሊሞች በሙሉ፤ በእኔና በሚሼል ስም የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክቴን ላስተላልፍ እወዳለሁ” በማለት ፕ/ት ኦባማ መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል።

 

የዚህን የረመዳንን ፆም በዓለም ላይ የሚገኙ 23 ሚሊዮን የሚጠጉ ሙስሊሞች በአስቸጋሪ ሁኔታ ማለፋቸው ከሌሎች ጊዜያት ለየት እንደሚያደርገው ታዋቂ የዓለም በጎ አድራጎት ድርጅቶች ገልፀዋል። እንደ ኦክስፋም እና “ሙስሊም ኤይድ” የተሰኙት ድርጅቶች ኦፊሴላዊ መግለጫ ከሆነ፤ ብዙኀን ከአንዲት ዳቦ ፈቀቅ ያለ ምግብ በረመዳን የ30 ቀን የፆም ቀናት ማግኘት የቻሉ ቢሆንም፤ የተቀሩት ግን በአፍጢራ ሰዓት የሚበሉት አልነበራቸውም በማለት የዘንድሮውን የረመዳን ፆም ገልፀውታል።

 

ኦክስፋም እና የሙስሊም በጎ አድራጎት ድርጅት በአፍጋኒስታን፣ በጋዛ እና በሶማሊያ በሚገኙ 13 ክልሎች የሚገኙ ነዋሪዎችን ያነጋገሩ ሲሆን፤ ነዋሪዎቹ በተመሳሳይ ድምፅ “ይሄኛው የረመዳን ፆም እስከዛሬ ዝቅተኛ (ከመጠን ያነሰ) ምግብ ያገኘንበት ነው” ማለታቸውን ምዕራባውያን የመገናኛ ብዙኀን ዘግበዋል።

 

የሙስሊም በጎ አድራጎት ድርጅት ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅ ሐሚድ አዛድ፤ “በዚህ ዓመት የረመዳን ፆም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች ካለምግብ ውለው አድረዋል። በኢራቅ ብቻ አምስት ሚሊዮን ወላጅ አልባ ሕፃናት፣ ሁለት ሚሊዮን ባሎቻቸው የሚቱባቸው ሴቶች በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ። እኛን እያሳሰበን ያለው ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስፈላጊውና አጣዳፊውን እርዳታ በአፋጣኝ አለማግኘታችን ነው።” በማለት ያላቸውን ስጋትና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተጋረጠውን ችግር ሳይሸሽጉ በግልጽ ተናግረዋል።

 

ኦክስፋም እና የሙስሊም በጎ አድራጎት ድርጅቶች ለዓለም አቀፍ የሰብዓዊና የእርዳታ ድርጅቶችና ተቋማት፣ እንዲሁም ለለጋሽ ሀገራትና ግለሰቦች በሚሊዮን ለሚቆጠሩ በዓለም ላይ ለሚገኙና አስቸኳይ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ሙስሊም ወገኖች ለምግብ፣ ለመጠለያ፣ ለንፁኅ መጠጥ እና ለሕክምና የሚውል እርዳታ እንዲለግሱ ጠይቀዋል።

 

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ ጥናትና መረጃ መሠረት ሶማሊያ፣ በኃይል የተያዘችው ፍልስጥኤም እና አፍጋኒስታን አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው የሙስሊም ዓለሙ ሀገራት መሆናቸውን ይጠቁማል።

 

ነሐሴ 16 ቀን 2001 ዓ.ም. የተጀመረው የረመዳን ፆም የተጀመረው ጨረቃን መሠረት ባደረገው የእስልምና የቀን መቁጠሪያ (ሒጅራ) ዘጠነኛው ወር ላይ ሲሆን፣ ይኸውም ቅዱስ ቁርዓን ለነብዩ መሐመድ የተገለጸለት እንደሆነ መዘገባችን አይዘነጋም። በ1430ኛው የረመዳን ፆም ሙስሊሙ ማኅበረሰብ 30 ቀናትን ፆሟል።

 

በመላው ዓለም የሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ኢድ አልፈጥርን (ረመዳንን) የሚያከብሩት በደማቅ ሥነሥርዓት ሲሆን፣ በዕለቱ በዓሉን አስመልክቶ ከሚዘጋጁት የምግብ አይነቶች ውስጥ ጣፋጭ ምግቦች ቀዳሚውን ስፍራ እንደሚይዙ ይታወቃል። በተለይም በኢትዮጵያ ሙስሊም ምዕመናን ዘንድ ባቅላባ፣ ሣንቡሳ፣ ሙሸበቅ፣ ሐላዋ፣ ፓስቲ፣ … የመሳሰሉት ጣፋጭ ምግቦች እንደሚዘወተሩ ይታወቃል።

 

የእስልምና የቀን መቁጠሪያ (ሒጅራ) 12 ወራቶች ያሉት በጨረቃ ላይ የተመሰረተ የቀን መቁጠሪያ ሲሆን፣ በዓመት 354 ወይንም 355 ቀናት አሉት። በርካታ የሙስሊም ሀገራት የሚጠቀሙበት ከመሆኑም በላይ የእስልምና በዓላትን ለመቁጠር በመላው ዓለም ያለው ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ይገለገልበታል።

 

በረመዳን የአንድ ወር የፆም ወቅት በተለይም አዋቂዎች በጉዞ ላይ ካልሆኑና ካልታመሙ በቀር መፆም እንዳለባቸው የእስልምና እምነት ይደነግጋል። በፆሙ ወቅት አንድ ሙስሊም ከንጋት (ፀሐይ ከመውጣትዋ በፊት) ጀምሮ እስከ ምሽት (ፀሐይ እስከምትጠልቅ ድረስ ከምግብ፣ ከመጠጥ፣ ከሲጋራ፣ ከሺሻ እና ከወሲብ መቆጠብ የሚኖርበት ሲሆን፤ እነኝህ የተከለከሉትን ነገሮች ፀሐይ ከጠለቀችበት እስከ ከመውጣትዋ በፊት ባለው ጊዜ ውስጥ መጠቀምና ማድረግ ይችላል። ትናንት ቅዳሜ መስከረም 9 ቀን 2002 ዓ.ም. የረመዳን ፆም የመጨረሻው ቀን ነበር።

 

በእስልምና ዕምነት ፆም ምዕመኑን ትዕግሥት፣ ትህትና እና መንፈሣዊ ትምህርት ይሰጠዋል ተብሎ ይታመናል። ረመዳን ለ”አላህ” ሲባል የሚፆም ፆም እንደሆነና ሙስሊሙ ምዕመን ለሠራው ኃጢያት ምህረትን የሚጠይቅበት፣ ዕለት ተዕለት ለሚሠራቸው ኃጢያቱና ከሠይጣን ፈጣሪው ይጠብቀው ዘንድ የሚፀልይበት እንደሆነና ራሱን ከኃጢያት የሚያነፃበት ወቅት መሆኑን የእምነቱ ሊቃውንት ያስረዳሉ።

 

የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ለመላው የእስልምና ዕምነት ተከታዮች በሙሉ ኢድ አልፈጥር! ትላለች።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ