Ethiopia Zare (ሰኞ ታህሳስ 5 ቀን 2002 ዓ.ም. December 14, 2009)፦ ቅዳሜ ኅዳር 26 ቀን የሁለት ዓመት ከወራት ጉዞዋን ያጠናቀቀችውን “አዲስ ነገር” ጋዜጣ ከገበያ መውጣት አስመልክቶ በአዲስ አበባ የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚኖሩ የጋዜጣው አንባቢያንን እንዳስደነገጠ ምንጮች ገለጹ።

 

የአዲስ ነገር ጋዜጣ ዋና አዘጋጆች ከሀገር ሲወጡ ሪፖርተሮቹ እስከ ረቡዕ ድረስ ያላወቁ ሲሆን፣ ረቡዕ ዕለት በሰሙት ወሬ መደናገጣቸውንና በማግስቱ ከሀገር መውጣታቸውን ለማወቅ ተችሏል።

 

ባለፈው ኀሙስ ኅዳር 24 ምሽት ላይ የ“አዲስ ነገር” ጋዜጠኞች ከሀገር መሸሽ መወራት ከተጀመረ አንስቶ ሣምንቱን ሙሉ የከተማዋ ምሁራንና የጋዜጣው አንባቢያን ውይይት በ“አዲስ ነገር” ዙሪያ ሆኖ ነበር የሠነበተው።

 

የጋዜጠኞቹን መሰደድ ከጥሩም ሆነ ከመጥፎ ጎኑ ያዩት አስተያየት ሰጪዎች መንግሥትን ከመኮነንና በነፃ ጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰውን ጫና ከማማረር አልቦዘኑም።

 

የ“አዲስ ነገር” ቋሚ አንባቢና አድናቂ መሆናቸውን የተናገሩት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲው መምህር አቶ ጌታቸው በጋዜጠኞች መበተን ያላቸውን ጥልቅ ኀዘን ሲገልጹ “መንግሥት በጋዜጠኞች ላይ የሚያደርሰው ወከባ ቀላል ነው ተብሎ የማይታለፍ ቢሆንም፤ ከሀገር መውጣታቸውን በምንም መሥፈርት አልደግፈውም። አደጋን መሸሽ መፍትሔ አይሆንም። በአጭር ጊዜ በቀላሉ ሊገኙ የማይችሉ አራትና አምስት የሚሆኑ አምደኞቻቸውን በትኖ መጥፋት ስህተት ነው። ከመንግሥት ጋር ችግር ውስጥ የገቡ፤ ከፍ አድርገን ካየነው ደግም መንግሥት ዓይኑን የጣለባቸው ጋዜጠኞች ካሉ እነሱን ገሸሸ በማድረግ ሌሎችን ወደ ላይ ከፍ አድርጎ ጋዜጣዋ እንድትቀጥል ማድረግ ነበረባቸው። ይህንንም ስል መንግሥት ካራ አዘጋጅቶላቸው ከነበር መታረድ አለባቸው አልልም። ኢህአዲግን ደህና አድርገው ፈትነው ሂሳብ ማወራረጃ ላይ መሰደዳቸው ኢህአዲግን አሸናፊ እንዲሆን ማድረግ ነው። … በዚህች ሀገር መጀመር እንጂ መጨረስ እንደሌለ አራምድ የነበረውን አመለካከቴን አዳብሮታል - የነሱ መሳደድ” ብለዋል።

 

አቶ ዳዊት ሽፈራው በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ነው የሚሠሩት። የጋዜጣው ቋሚ ደምበኛ መሆናቸውን ገልጸው፤ “እንደስማቸው በጋዜጣ አሠራር እስከ ዛሬ ከለመድነው የተለየ አዲስ ነገር ነበር ይዘው የመጡት። በ1993 ዓ.ም. ዕለታዊ አዲስ የሚባል ጋዜጣ ሥራ በጀመረ በ6 ወሩ ተቋረጠ። በጣም ልዩ ጋዜጣ ነበር። በ1998 የምርጫ ግርግር ከ10 ዓመት በላይ መንግሥት ሲኮረኩሙ የነበሩ እንደነጦቢያ፣ ጦማር፣ ኢትኦጵ፣ … ጋዜጦች በተለያዩ ጫናዎች ቆሙ። አዲስ ነገርም ሦስት ዓመት ሳይሞላው ቆመ። ሁሉም ጋዜጦች በአስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ስለገቡ ሥራ አቁመው ሊሆን ይችላል። የአዲስ ነገርን ማቆም ግን የምደግፈው አይደለም። አቁሙ እስኪባሉ ወይም እስኪታሰሩ ድረስ መግፋት ነበረባቸው። በ20 ሺዎች የሚቆጠሩ አንባቢዎቻቸውን በትነው መጥፋት አልነበረባቸውም ብየ ነው የማምነው። አማረ አረጋዊ ከአዲስ አበባ ጎንደር ተወስዶ ታስሯል ተደብድቧል። በፍቃዱ ሞረዳ ጋምቤላ ተወስዶ ተደብድቧል። በርካታ የግል ፕሬስ ጋዜጠኞች ብዙ መከራ አይተዋል። ከመከራ በኋላም ወደ ሥራቸው የተመለሱ በርካታ ናቸው” ብለዋል።

 

አቶ አባቡ እንደሚባሉ ሌላ አስተያየት ሰጪ ደግሞ “ኢህአዲግ ባያስጨንቃቸው የሚሰደዱ አይመስለኝም። ኢህአዲግም ቢፈራቸው እውነት አለው። በቅርቡ የሚያካሂደው ምርጫ በነፃ ፕሬስ እንዲተችበት የፈለገ አይመስልም። እንደ አዲስ ነገር ያሉ የገባቸው ጋዜጠኞች እስከዶቃ ማሠሪያው ሊነግሩት ስለሚችሉ ቀድሞ ከሀገር እንዲወጡ በማስፈራራት ጫና እንዳደረገባቸው ነው የሚገባኝ። በዚህም ትርፋማ የሚሆን ይመስለኛል። በኔ እምነት እዚህ ቢቆዩ ቃሊቲ ነበር የሚወረውራቸው” ብለዋል።

 

“መንግሥት ከሀገር መውጣታቸውን የሚፈልግ አይመስለኝም” የሚሉት አቶ ሙሐመድ ያሲን ናቸው። “እስከማውቀው ድረስ አቶ በረከት ከጫፍ እስከ ጫፍ አዲስ ነገር ጋዜጣን ያነባል። ከሁሉም ጋዜጦች የሚመርጠው አዲስ ነገርን ነው። አንዳንድ የሱ ሰዎችንም በጋዜጣው እንዲጽፉ ያስደርጋል። በተዘዋዋሪ መንገድ የበረከት ሃሳብ በጋዜጣው ይወጣ ነበር። አንድ የሱ አማካሪ የነበረ ሰው ከነፎቶው ጋዜጣው ላይ ይጽፍ ነበር። ጋዜጣዋ የሁሉንም ወገን ሃሳቦች የምታራምድ በመሆንዋ እንድትጠፋ አይፈለግም ብዬ ነው የማምነው። ጋዜጠኞቹም ከሀገር እንዲሰደዱ አይፈልጉም። የሚፈልጉት ግን በኢህአዲግ ላይ የሚያሳርፉትን ጡጫ እንዲቀንሱ እና የኢህአዲጎች ሃሳብ በስፋት እንዲወጣ ነበር። በልጆቹ መውጣት ተጎጂው መንግሥት ነው ብዬ አምናለሁ” ብለዋል።

 

“ከአዲስ ነገር ውጪ በአሁኑ ጊዜ ያሉት ጋዜጦች በሙሉም ባይባሉ አብዛኞቹ የኢህአዲግ ሰዎች እጅ ያላባቸው ናቸው የሚሉት” ስማቸውን መንገር ያልፈለጉ መምህር፤ “በጋዜጣው መቆም የሚጎዳው አንባቢ ነው። በተለይም አንባቢው ሀገርን በመለወጥ ረገድ አስተዋጽዖ የሚያደርገው የኅብረተሰብ ክፍል በደንብ ትምህርት ያገኝ ነበር። የመጯጯህ ነገር ቀርቶ በስከነ መንፈሥ ሃሳብን መለዋወጥ እየዳበረ ነበር። ዕድሜ ለኢህአዲግ የሱ ብቻ እንጂ የሌላው ሃሳብ እንዳይደመጥ ትልቁን ዩኒቨርሲቲ ዘጋው። በ1997 የታቃዋሚዎች ድምፅ በግል ጋዜጦች መስማት ታላቅ ለውጥን ስላመጣ አሁን ፍርሃት ያዘው፤ ቀድሞ ዱላውን መዝዞ ልጆቹን “በአዲስ ዘመን” ቶርች እንደሚገለብጣቸው ዛተ። ልጆቹም ፈሩ። ምክንያቱም ብዙ ንጹኀን ሃሳባቸውን ስለገለጹ ብቻ ለእስራት፣ ለድብደባ መጋለጣቸውን አይተዋል ጽፈዋል። እኔ ለአንድ ዓመት ያህል አልቸገርም። ጋዜጣው መውጣት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ያጠራቀምኩት ስላለ በየሣምንቱ ቅዳሜ ከአንድ ጀምሬ ያንን እያነበብኩ ናፍቆቴን እወጣለሁ” በማለት የተሰማቸውን ኀዘን ገልጸዋል።

 

አንዳንድ ሰዎችም በድፍረት ኅብረተሰቡ በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰውን ወከባና እንግልት እንዳልተረዳና ከችግራቸው ጎን ለመቆም አለመቻሉን በማንሳት በተለይ በአሁኑ ሰዓት ከቅንጅት መሪዎች ጋር በ’ምህረት’ ተለቀዋል የተባሉት የሰርካለምና የሲሳይ አሳታሚዎች ላይ እስከ 120 ሺህ የሚደርስ ቅጣት እንዲከፍሉ እየተገደዱ ያለበትን ሁኔታ በሀገርም ሆነ በውጭ ሀገራት የሚኖሩ የፕሬሱ ወዳጆች በጽናት መከታተልና እየደረሰባቸው ያለውን ስቃይ ተካፋይ ለመሆን ቁርጠኝነቱን ማሳየት አለበት ሲሉ ተደምጠዋል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግሥት በጋዜጠኞቹ እና በሌሎችም የግል ጋዜጦች ላይ ያነጣጠረ የፕሮፓጋንዳ ምናልባትም የማወገዝ ሥራ ለሦስት ተከታታይ ምሽቶች ከዓርብ ታህሳስ 2 ጀምሮ እንደሚያቀርብ አስታውቋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ