አቶ አየለ ጫሚሶ አራተኛ ጋዜጣ ከሰሱ

Ethiopia Zare (ዓርብ ግንቦት 22 ቀን 2000 ዓ.ም. May 30, 2008)፦ በየሣምንቱ ቅዳሜ መታተም ከጀመረ 32 ሣምንታትን ያስቆጠረው “አዲስ ነገር” ጋዜጣ በእነ አቶ አየለ ጫሚሶ ከሳሽነት በዛሬው ዕለት አዘጋጁና ም/ዋና አዘጋጁ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥጥር ስር እንደዋሉ ለኢትዮጵያ ዛሬ ከአዲስ አበባ የደረሰው ዘገባ ያስረዳል። ከሳሻቸው አቶ አየለ ጫሚሶ መሆናቸው ታውቋል።

 

ዋና አዘጋጁ አቶ መስፍን ነጋሽ እና ም/ዋና አዘጋጁ አቶ ግርማ ተስፋው የታሰሩት “የፖለቲካ ፖርቲዎች አሜሪካን ኤምባሲ ሲጋበዙ፣ አቶ አየለ ጫሚሶ ግን አልተጋበዙም” በሚል ባቀረቡት ዘገባ ላይ ምንጮቻቸውን ጠቅሰው “አምባሳደር ያማማቶ እነ አቶ አየለ ጫሚሶን እንደ ተቃዋሚ ቆጥረውት እንደማያውቁ ገለጹ” የሚል ዘገባ በማስነበባቸው እንደሆነ ታውቋል።

 

በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ሰዓት የነፃው ፕሬስ አስጊና አስፈሪ በሆነ ሁኔታ ታፍኖ ባለበት ሰዓት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከነፃው ፕሬስ ጎን መቆም ሲገባቸው የአቶ አየለ ጫሚሶ ፓርቲ "ውሃ ቀጠነ" በሚል የነፃውን ፕሬስ ጋዜጦችና ጋዜጠኞች በክስ እያዋከቡ መገኘታቸው ብዙዎችን እጅግ አሳዝኗል። አቶ አየለ ጫሚሶ ከዚህ ቀደም "አውራምባ ታይምስ"፣ "ጎግል" እና "ሶሬሳ" የተሰኙ ጋዜጦችን "የእነ ብርቱካን፣ ... ቅንጅት እያላችሁ ትዘግባላችሁ፣ ቅንጅት የእኔ ነው" በማለት መክሰሳቸውና ለእንግልት መዳረጋቸው አይዘነጋም።

 

ዛሬ ጠዋት አራት ፖሊሶች ሁለቱን ጋዜጠኞች ወደ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወስደው እንዳሰሯቸው ለማወቅ ችለናል። ጋዜጠኞቹ የተወሰዱት ከቢሯቸው መሆኑን ለማረጋገጥ ችለናል። የፖሊስ ኮሚሽኑ የሚገኘው ሰሜን ሆቴል አጠገብ እንደሆነ ይታወቃል።

 

ፖሊስ ጋዜጠኞቹን ዋስ እንዲያቀርቡ የጠየቃቸው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የምሳ ሰዓት ላይ በዋስ ሊያስፈቷቸው የሞከሩ ሰዎች እንዳሉ የተረዳን ቢሆን፤ ፖሊሶቹ ለምሳ ወጥተው ስለነበር ጋዜጠኞቹ ሳይፈቱ ቀርተዋል። ምናልባትም ከሰዓት በኋላ ሊፈቱ የሚችሉ ሲሆን፣ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ካልተፈቱ ግን ሰኞ ይፈታሉ ተብሎ ይጠበቃል።  

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ