ሰበር ዜና

Ethiopia Zare (ዓርብ መጋቢት 12 ቀን 2000 ዓ.ም. March 21,2008) በወ/ት ብርቱካን የሚመራው ቅንጅት "አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ" በሚል አዲስ ስም ለማቋቋም፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የፊርማ ማሰባሰቢያ የድጋፍ ደብዳቤ እንዲጻፍለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበው ጥያቄ ተቀባይነት አጣ።

 

የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ሥራ አስፈጻሚ ተሰብስቦ ባሳለፈው ውሳኔ የፓርቲውን ስያሜ ቅንጅቱን ለማይወክሉና ወያኔ ራሱ ላደራጃቸው ለእነ አቶ አየለ ጫሚሶ በመስጠቱ የፓርቲው ዓላማና ደንብ ሳይቀየር ስሙን ብቻ ቀይሮ ለመንቀሳቀስ በወሰነው ውሳኔ፤ በቦርዱ ሕግ መሰረት ፓርቲውን ለማቋቋም የሚያስችለውን ፊርማ ለማሰባሰብ የድጋፍ ደብዳቤ እንዲጻፍለት ቦርዱን መጠየቁ ይታወሳል።

 

ቦርዱ የተለያዩ ምክንያቶችን በመደርደር በቀጠሮ ሲያጉላላ ከቆየ በኋላ በዛሬው ዕለት ያለ ድጋፍ ደብዳቤ አስፈርማችሁ መምጣት ትችላላችሁ ሲል ደብዳቤውን ያለመጻፍ እንቢተኝነት ማሳየቱ ታውቋል።

 

ቀደም ሲል በነበረው አሰራር ቦርዱ የድጋፍ ደብዳቤ ይጽፍ እንደነበር በመግለጽ እነሱ ለምን ሊከለከሉ እንደቻሉ ለቦርዱ ጥያቄ ሲቀርብለት፤ "እስከ ዛሬ ድረስ ከሕግ ውጭ ሲሠራ ነበር፣ በሕጉ መሰረት ግን መብታችሁ በመሆኑ ያለድጋፍ ደብዳቤ 1500 ፊርማ አስፈርማችሁ መምጣት ትችላላችሁ" የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ታውቋል።

 

ነገር ግን የክልል የወያኔ ካድሬዎች እንኳን ያለቦርዱ ደብዳቤ ይቅርና የቦርዱ ደብዳቤ ተይዞ እንኳን ፊርማ ለማሰባብ ከፍተኛ ችግር መኖሩን ከዚህ ቀደም ልምድ ያላቸው አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ። ቦርዱም ይህን የድጋፍ ደብዳቤ መጻፍ የጀመረው በተደጋጋሚ ይቀርብለት በነበረ አቤቱታ እንደሆነ ታውቋል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ