ቫኛ ሉንድቢ ቬዲን (የአውሮፓ የሠራተኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት)ቫኛ ሉንድቢ ቬዲን እና አንድሪያ ቡደኩል ይገኛሉ

Ethiopia Zare (ኀሙስ የካቲት 11 ቀን 2002 ዓ.ም. February 19, 2010)፦ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የታሰሩበትን አንደኛ ዓመት በማሰብ፣ እሳቸው እና ሌሎች የኅሊና እስረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቅ ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ የፊታችን ቅዳሜ ፌብሩዋሪ 20 ቀን 2010 እ.ኤ.አ. በስቶክሆልም ከተማ ስቬያቬገን 47 በሚገኘው ኤ.ቢ.ኤፍ. ሁሰት አዳራሸ እንደሚደረግ ታወቀ።

 

በዚህ በርካታ ህዝብ እንደሚገኝበት በሚጠበቀው ስብሰባ ላይ ስልሳ ሚሊዮን ሠራተኞችን በመወከል የአውሮፓ የሠራተኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ስዊድናዊዋ ቫኛ ሉንድቢ ቬዲን እና በስዊድን የአምኒስቲ ኢንተርናሽናል ተወካይ አንድሪያ ቡደኩል ንግግር እንደሚያደርጉ በስዊድን የአንድነት ድጋፍ ማኅበር ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልጿል።

 

ከኢትዮጵያውያን በኩል ደግሞ የድጋፍ ማኅበሩን ሊቀመንበር አቶ የራስወርቅ መንገሻን ጨምሮ ደራሲ የሺወርቅ ወንድሜነህ እና ሌሎችም ንግግር እንደሚያደርጉ ለመረዳት ችለናል። በተጨማሪም የስዊድን የፓርላማ አባልና የቀይ መስቀል ተወካይ እንደሚገኙም ከድጋፍ ማኅበሩ ለማረጋገጥ ችለናል።

 

ጉባዔው ረፋዱን ላይ 12፡00 ሰዓት (በኢትዮ. አቆ. 6 ሰዓት) ተጀምሮ በ16፡00 ሰዓት (በኢትዮ. አቆ. 10 ሰዓት) የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ ግጥሞችና ሥነጽሑፎች እንደሚቀርቡ፣ ልዩ ልዩ ዝግጅቶችም እንደሚደረጉ ለመረዳት ችለናል። የድጋፍ ማኅበሩ በስዊድን እና በስቶክሆልም አካባቢ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ አፍቃሪዎች በሙሉ በዚሁ ስብሰባ ላይ ይገኙ ዘንድ ጥሪ አስተላልፏል።

 

በዚሁ ቀን ንግግር የሚያደርጉት ቫኛ ቬዲን ባለፈው ዓመት በስዊድን የዓለም አቀፍ የወዛደሮች ቀን ሲከበር ብዙ ሺህ ህዝብ በተሰበሰበበት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳን በማስታወስ እንዲፈቱ መጠየቃቸው አይዘነጋም።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ