Aba Matiasበቫንኩቨር ከፍተኛ ተቃውሞ ይጠብቃቸዋል

Ethiopia Zare (ሐሙስ ግንቦት 13 ቀን 2002 ዓ.ም. May 20, 2010)፦ በቶሮንቶ ካናዳ የአባ ጳውሎስ ቀኝ እጅ የሆኑት አባ ማትያስ ንጉሴ ደስታ በዚህ በያዝነው ሣምንት (ሜይ 23-24) በህሆተ ሰማይ ቅ/ማሪያም ቤ/ክርስቲያን ጋባዥነት ወደ ቫንኩቨር እንደሚመጡና ቤተክርስቲያኗ ወደ አባ ጳውሎስ ስር እንድትገባ ተግተው ሲሰሩ የነበሩት ሰዎችም አባ ማትያስን ለመቀበል ሽር ጉድ እያሉ እንደሆነ ምንጮች ገለጹ።

 

አንዳንድ የቤተክርስቲያኗ ጠቅሎ በአባ ጳውሎስ ጉያ መግባት ያሳዘናቸውና እስካሁንም ድረስ በመታለላቸው በጣም የተጸጸቱ አባላት እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል በፍርድ ቤት ገለልተኞች ነን እያሉ ሲከራከሩ የነበሩት አንዳንድ ቀንደኛ አባላት ቀስ በቀስ የዋህ ምዕመናንን አታለው ወደ አባ ጳውሎስ ጎራ እንዲገቡ ማድረጋቸው እጅግ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።

 

ህሆተ ሰማይ ቅ/ማሪያም ቤተክርስቲያን የአባ ጳውሎስን ባለቤትነት የመጨረሻ ማኅተም ለመምታትና በቫንኩቨር የአባ ፓውሎስን መቀመጫ ለመትከል እየተሰናዱ እንደሆነ ምንጮቻችን አክለው ጠቅሰዋል።

 

አባ ማትያስን ወደ ቫንኩቨር እንዲመጡ ከፍተኛውን ሚና እየተጫወቱ ያሉት ከስዊድን ወደ ቫንኩቨር የመጡት አባ ወልደ መስቀል ሲሆኑ፤ ቀደም ሲል ካናዳ በነበሩበት ሰዓት የነዋሪነተቸውን ግዴታ ሳያሟሉ የታከሙበትን በሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ ሳይከፍሉ ሀገሪቱን ለቀው ከሄዱ ከዓመታት በኋላ ወደቫንኩቨር እንደተመለሱና ባሁኑም ሰዓት የካናዳ መኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው ይሄንኑ የአባ ጳውሎስን መቀመጫ በቫንኩቨር የመትከሉን ሥራ እየሠሩ እንደሆነ ምንጮች ገልጸዋል።

 

እነዚሁ የአባ ማትያስን የቫንኩቨር ጉዞ አጥብቀው የሚያወግዙ የቤተክርስቲያኗ አባል ኢትዮጵያዊያን፤ አዲሱ የቤተክርስቲያኗ ደንብ ራሱ በአንቀጽ ቁጥር አንድ ላይ የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ “በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ሥርዓት ቤ/ክርስቲያን መሰረት በተሾሙ ፓትሪያርክ ለካናዳ ሀገር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤ/ክ የተሾሙ ሊቀ ጳጳስ” ነው እያለና አባ ጳውሎስ የቤተክርስቲያንን ሕግና ሥርዓት ባፋለሰ መልኩ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር በአቶ ታምራት ላይኔ በዘራቸው ብቻ እንደተሾሙ እየታወቀ ከዚያም ባሻገር ሀገር ስትገነጠል፣ ዜጎች ሲታሰሩ፣ መሬት ሲቆረስ፣ ኢትዮጵያዊያን በዘር ሲከፋፈሉ ባርከው እያጸደቁ እየተመለከትን፣ የሳቸውን ተወካይ እንደ ቅዱስ አባት ወደ ቫንኩቨር መጋበዝ እንዳሳዘናቸው ለዝግጅት ክፍላችን ገልጸዋል።

 

የአባ ማትያስን ወደ ቫንኩቨር መምጣትና የሳቸውን በዚህ አካባቢ መገኘት በተቃውሞ ለመግለጽ የተሰናዳ ነገር እንዳለ ለመጠየቅ በቫንኩቨር አካባቢ በፀረ-ወያኔ እንቅስቃሴው የሚታወቀውን አቶ ከበደ አባተን ስልክ ደውለን በአካባቢው ባለመኖሩ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም። ምንጮቻችን ግን አንዳንድ በቫንኩቨር የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የማናቸውንም ዜጋ የአምልኮ መብት ሳይጋፉ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን በመጠቀም አባ ማትያስ በሚገኙበት ስፍራ በመገኘት ተቃውሞዋቸውን እንደሚገልጹ ተናግረዋል።

 

የአባ ማትያስን ወደ ቫንኩቨር ጉዞ በሚመለከት አስተያየት እንዲሰጥበት የጠየቅነው ሌላው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ልጅ ተክሌ “እያስጠቁን ያሉት ባንድ በኩል አውቀውም ይሁን ሳያውቁት ከወያኔዎቹ ጋር ተባብረው በምስክርነትና መዋጮ በመክፈል በሙያና በሞራል የጠላትን ሥራ እያገዙ ያሉት የራሳችን ሰዎችና በሌላም በኩል ሥራውን በትጋትና በንቃት እንዲሁም በ”ፓሽን” መሥራት ያልቻለው ያንድ አካባቢ ሰዎች የታጨቁበት የራሳችን በፓትሪያርክ መርቆሬዎስ የሚመራው ሲኖዶስ ነው” ሲል ተናግሯል።

 

ልጅ ተክሌ አክሎም “ለምሳሌ ሲኖዶሳችን በቅርቡ ስላደረገው ጉባዔ ባወጣው መግለጫ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ገዢ ሥርዓት ጠንቀኛ ፖለቲካ እያወቀና ለሲኖዶሱ አባላት መሰደድና ለነፃ ምርጫ አለመኖር ዋንኛው ተጠያቂ ወያኔ መሆኑን እየተረዳ፤ ከምርጫ ጋር በተያያዘ ተቃዋሚዎችንም ሥርዓቱንም እኩል የሚያስጠነቅቅ መግለጫ ማውጣቱ ጥሩ ምሳሌ ነው” ብሏል። እንዲሁም “በየአካባቢው በወያኔ ተሰርስረው እየተወሰዱ ያሉትን ቤተክርስቲያናት አመራር አጠናክሮ እንደመምራት በዓመት አንድ ግዜ ብቻ በሚካሄድ ጉባዔና መግለጫ ብቻ የሚፈታ ነገር ያለ ይመስል መግለጫ ላይ ማተኮሩ እጅግ አዳክሞናል።” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

 

ሌላ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አስተያየት ሰጪና የቫንኩቨሩን መነኩሴ ሕገ ወጥ የካናዳ ቆይታ በቅርብ እንደሚያውቁ የገለጹ ግለሰብ፤ “እንደ አባ ወልደመስቀል ቆብ አጥልቀው የሚያታልሉንንና ከጠላት ተመሳጥረው የሚጎዱንን መነኮሳት ጠቁመን ሕግ ፊት ማቅረብና የራሳችን ሲኖዶስ ደግሞ ጥሩ ሲሠራ ለማመስገን ድካም ካለበትም ለመውቀስና ለመተቸት መድፈር አለብን” ካሉ በኋላ  "በአሁኑ ሰአት ቤተ ክርስቲያኗ በአባ ጳውሎስ ትመራ፣ በአቡነ መርቆሪዎስ ትቀጥል እንዲሁም ገለልተኛ ሆነን ሳንከፋፈል እንቀጥል በሚሉ ምእመናን በተወጠረችበት ሰአት የአባ ፓውሎስ ወኪል የሆኑት አቡነ ማትያስ መምጣት ሆን ተብሎ የተሰናዳና የፖለቲካ ተልእኮ ያለው ያስመስለዋል።" በማለት አስተያየታቸውን አጠናቀዋል።  

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ