ጉዳዩ በፍርድ ቤት መታየት ጀምሯል

ውሳኔ በሚቀጥለው ሣምንት ይሰጣል

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ጥቅምት 8 ቀን 2001 ዓ.ም. October 18, 2008)፦ ከተመሰረተች ከ13 ዓመት በላይ የሆናት የቫንኩቨር ካናዳ ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተክርስቲያን ውስጥ በተነሳ አለመግባባት የተጀመረው ክርክር በብሪቲሽ ኮሎምቢያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ መታየት መጀመሩ ተገለጸ።

 

የችግሩ መነሻ ቤተክርስቲያኗን ስም ያለአባላት እውቅና ስምና ገንዘብ አዛውራችኋል፣ መተዳደሪያ ደንብ ቀይራችኋል በሚል በአንድ በኩል ሂደቱን በተቃወሙ አባላትና በካናዳ አቀፍ ቤተ ክርስቲያን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ስሙን አዛውራችኋል በተባሉ አምስት ግለሰቦችና ቤተክርስቲያኗ መካከል መሆኑ ታውቋል።

 

የቫንኩቨር ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በ1995 ዓ.ም. በቫንኩቨር ነዋሪዎች ጠያቂነት ቶሮንቶ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ካናዳ እውቅና አግኝቶ በስሩ የተቋቋመ ሲሆን፤ (በ2005) በኋላ የተመረጠው የሰበካ ጉባዔ የቤተክርስቲያኑን ስያሜ በአዲስ መልክ በማዞር "ኆኅተ ሰማይ ቅድስት ድንግል ማርያም" በሚል በብሪቲሽ ኮሎምቢያ (ቫንኮቨር) ያስመዘግባል።

 

የቤተ ክርስቲያኗን ስም መዛወር በሰበካ ጉባዔ አባላትና በዋናው ቄስ መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ከዓመት በኋላ ምዕመናንና አባላት ጋር ይደርሳል። የስሙ መዛወርና ከዛም አልፎ አዲስ ስያሜ የተሰጣት ቤተክርስቲያን በውጭ የሚገኙትንም ሆነ በሀገር ቤት ያሉትን ፓትርያርክ ሳንከተል ገለልተኛ ሆነን እንቀጥላን ቢሉም ምዕመናኑ ሳያውቁ ውስጥ ውስጡን ሀገር ቤት ካለው ሲኖዶስ አስተዳደር ጋር ግንኙነት ያደርጉ እንደነበር ታማኝ ምንጮች የገለጹ ሲሆን፤ የሰበካ ጉባዔው አካሄድም ያልጣማቸው ምዕመናንን አስቆጥቷል።

 

በአዲስ የተቋቋመውና ኆኅተ ሰማይ ቅድስት ድንግል ማርያም የተሰኘው ቤተ ክርስቲያን ንብረትና ገንዘብ በ1995 በካናዳ አቀፍ የተቋቋመችው ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ንብረትና ገንዘብ በመሆኑ ሰበካ ጉባዔው አዲሱን ስያሜ ይዞ መቀጠል ይችላል ንብረቱንና ገንዘቡን ለቀድሞዋና በእውነተኛው ፓትሪያርክ አቡነ ማርቆሪዮስ ለምትመራው በካናዳ አቀፍ ለተመሰረተችው ቤተክርስቲያን መመለስ አለበት በሚሉ ወገኖች የተነሳውን ጥያቄ በሽምግልና ለመፍታት ለሁለት ዓመታት ብዙ ጥረት ቢደረግም ውጤት አልባ በመሆኑ፤ ቫንኩቨር በሚገኘው የብሪቲሽ ኮሎምቢያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ መታየት ከመጀመሩም በላይ የቤተክርስቲያኒቱ ንብረትና ከ300 ሺህ በላይ የካናዳ ዶላር ካናዳ አቀፍ በሆነችውና በብጹዕ አቡነ ማርቆሪዮስ ስር በምትተዳደረው ቤተክርስቲያን እንዲመለስ የሚጠይቁት ወገኖች የእማኝነት ቃል ለአራት ቀናት ሲሰማ ቆይቷል።

 

ክሱ ቤተክርስቲያኗ ያለአባላት እውቅናና ሕጋዊ ባልሆነ መልኩ ስሟ በመቀየሩ፣ በነበረው ላይ አዲስ ቤተክርስቲያን መቋቋሙና በባንክ የነበረው ገንዘብ በመዛወሩ ወደቀድሞው ቦታ እንዲመለስ የሚል ሲሆን፣ የተከሳሽ ወገኖች የክሱን ሂደት በሚመለከት ምንም አይነት አስተያየት ለመስጠት ፍቃደኛ ሆነው አልተገኙም።

 

ሂደቱን በሚመለከት ያነጋገርናቸው ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ተንታኝ፣ የዚህ አይነት ችግሮች በተለይ አሁን ያለው አገዛዝ ሥልጣን ላይ ከመጣ ጀምሮ አሁን በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ ከብጹዕ አቡነ መርቆሪዮስ የሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ጋር መሥራት አንችልም በማለት በተደጋጋሚ በሚያሳድሩት ተጽዕኖ ምክንያት ፓትርያርኩ ተወግደው አቡነ ጳውሎስ ከተተኩበት ጊዜ ጀምሮ በቤተክህነት ውስጥ ከፍተኛ ችግር መፈጠር መጀመሩን አውስተው፤ የዚህ አይነት ችግር በተለያዩ ዓለማት በሚገኙ አጥቢያ ቤተክርስቲያን ውስጥ ከመፈጠሩም በላይ አገዛዙ የየቤተ ክርስቲያኑን ገንዘብና ንብረት ለመቆጣጠር ብሎም በውጭ የሚገኘውን ኅብረተሰብ የተጠናከረ እንዳይሆን ከፍተኛ በጀት በማውጣት ሲሠራበት የቆየ መሆኑን ጠቁመዋል። አክለውም በካናዳም ይሁን በሌሎች ሀገራት የሚገኙ ምዕመናን አካባቢያቸውን ከእንደዚህ አይነት አደጋ በንቃት እንዲጠብቁ አሳስበዋል። እንዲሁም ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ በተለይ በካናዳ ፍርድ ቤቶች ለሚነሱ ተመሳሳይ ክርክሮች ገዥ ወይንም ጠንካራ የሚሆን ሕጋዊ መሰረት እንደሚጥል አስምረውበታል።

 

የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ደንብና ሕግ በሚመለከት ያነጋገርናቸው አባት እንደሚሉት ደግሞ ፓትሪያርክ የሌለው ቤተክርስቲያን በምንም መልኩ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ተብሎ ሊጠራ እንደማይችል በአጽንዖ ያስቀመጡ ሲሆን፤ ገለልተኛ ሆኖ ያለፓትሪያርክ መቀደስ እንደማይቻልና ገለልተኞች ነን በማለት የሚያደናግሩ ካሉም ምዕመናን በትኩረት እንዲከታተሉ አሳስበዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!