Ethiopia Zare (እሁድ ሚያዝያ 25 ቀን 2001 ዓ.ም. May 3, 2009)፦ ለአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጳጳስና ለብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ረዳት ለሆኑት አቡነ ሣሙኤል ተግዝቶ ሊሰጣቸው የነበረው የ1.5 ሚሊዮን ብር ሽልማት ውዝግብ አስነሳ።

 

የቤተክህነት ምንጮች ለኢትዮጵያ ዛሬ እንደገለጹት፤ ከሁለት ወራት በፊት የከምባታ፣ ሃዲያ፣ ጉራጌና ስልጤ ሀገረ ስብከት ጳጳስ ለሆኑት አቡነ መልከጸዲቅ የክልሉ ተወላጆችና የታወቁ ነጋዴዎች ናቸው የሸለሟቸው በሚል የ1.3 ሚሊዮን ብር ሞዴሉ ቶዮታ የሆነ ፕራዶ መኪና የሸለሟቸው ሲሆን፤ “በርካታ ቤተክርስቲያናት በተቸገሩበት ወቅት ለአንድ የኃይማኖት መሪ እንዲህ ያለ ሽልማት መስጠቱና መቀበሉ ከኃይማኖት ሰዎች የሚጠበቅ አይደለም” የሚል ትችት አስነስቶ ነበር።

 

ከሁለት ሣምንት በፊት ደግሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ በንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ ሰብሳቢነት አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ አዲስ አበባ ውስጥ ለሚገኙ ቅርንጫፍ ቤተክርስቲያናት፤ “… በቅርቡ አራት ኪሎ ብርሃን ሠላም ማተሚያ ቤት ጀርባ የሚገኘው የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ያሠራውን ህንጻ ያስመርቃል። በዚህ የምረቃ በዓል ላይ የአዲስ አበባውን የሀገረ ስብከት ጳጳስና የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ረዳት አቡነ ሣሙኤልን ሳያውቁት ሽልማት አዘጋጅተን ልንሰጣቸው ስለሆነ ከየአጥቢያችሁ የ15 ሺህ ብር እንድታዋጡ …” የሚል ነው።

 

አቡነ ሣሙኤል በአንዳንድ የአጥቢያ አስተዳዳሪዎች የተወደዱ በመሆናቸው ደብዳቤው ከደረሳቸው አጥቢያዎች የአንዱ አስተዳዳሪ ጠጋ ብለው ሳያውቁ ተዘጋጅቶ ሊሰጣቸው ስለታሰበው ሽልማትና አጥቢያዎቹ አዋጡ ስለተባሉት ገንዘብ ሹክ ይሏቸዋል።

 

አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ አጥቢያ ቤተክርስቲያኖች ወደ 100 ደርሰዋል፣ እነዚህ እያንዳንዳቸው 15 ሺ ብር ቢያዋጡ ወደ 1.5 የኢትዮጵያ ብር ይደርሳል። ሊገዛ የታሰበው መኪና ዋጋ ደግሞ 1.3 ሚሊዮን ሲሆን፣ አንደኛ፦ የተከበረ ስማቸው እንደአቡነ መልከጸዲቅ እንዳይጠፋ፣ መዋጮው ለሙስና የሚጋብዝ መሆኑን በመጠቆምም ወዳጆቻቸው ምክር ይለግሷቸዋል።

 

አቡነ ሣሙኤልም “አለመስማቴ ነው እንጂ ብሰማ እስካሁንም ዝም አልልም ነበር” በማለት እጅግ ተቆጥተው የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃን በማስጠራት፤ “በኔ ስም የጀመራችሁትን መዋጮ በአስቸኳይ እንድታቆሙ እኔ ሳላውቅስ እንዲህ ያለ ሥራ እንዴት ይሠራል በርካታ ቤተክርስቲያናት በችግር ላይና በምዕመና ዕርዳታ ላይ እያሉ እንዴት ይህን ያህል ገንዘብ ለማስወጣት ትንቀሳቀሳላችሁ?” ብለው እንዲያቆሙ ትዕዛዝ አስተላልፈውላቸዋል።

 

የጠቅላይ ቤተክህነት ሥራ አስኪያጅ ንቡረዕድ ኤልያስ አብርሃ በበኩላቸው ሽልማቱን ለማዘጋጀት የወሰኑት እሳቸው እየሠሩ ላሉት ሥራ ድጋፍ ይሆናል ብሎ በማሰብ መሆኑን በመግለጽ ይቅር ካሉ ማስቀረት እንደሚቻል ማስረዳታቸውን የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ተናግረዋል።

 

አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት፤ ከዚህ ቀደም አቡነ መልከጸዲቅን የክልሉ ተወላጆችና የታወቁ ነጋዴዎች ናቸው ያዘጋጁት በሚል የ1.3 ሚሊዮን ብር መኪና ሰጥተዋቸዋል። ሽልማት የሚጠላ ባይሆንም ስንት የሚሠራ ሥራ እያለ ያውም ለኃይማኖት አባት እንዲህ ያለ ስጦታ ገዝቶ መስጠቱ አግባብ አልነበረም ሲሉ ይደመድማሉ።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!