“ሕጉ ሆን ተብሎ አንድነት ፓርቲን ለመምታትና ፈቃድ ለመከልከል የተነጣጠረ ነው”

የፖለቲካ ታዛቢዎች

Ethiopia Zare (ቅዳሜ ሚያዝያ 4 ቀን 2000 ዓ.ም. April 12, 2008) ኀሙስ ሚያዝያ 2 ቀን 2000 ዓ.ም. 23ኛ መደበኛ ስብሰባውን ያካሄደው የተወካዮች ምክር ቤት ያፀደቀው የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ኢህአዴግ ለፈለገው ቡድን ብቻ እውቅና ለመስጠት እንዲያስችለው ተደርጎ የተረቀቀ መሆኑ ታወቀ።

 

 

ከትናንት በስቲያ የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 2/2000 ሆኖ በፓርላማው የፀደቀው አዋጅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ሥልጣን ሙሉ ለሙሉ የምርጫ ቦርድ እንዲሆን በማድረግ ኢህአዴግ ለማይፈልጋቸው ፓርቲዎች ፈቃድ ላለመስጠት የሚያስችለውና ተቃዋሚዎችን ማጥቂያ መሣሪያው እንደሆነ ታውቋል። 

 

 

የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 2/2000 ሆኖ የፀደቀው ይህ አዋጅ የፓርቲዎች ምዝገባ ሥልጣን የምርጫ ቦርድ መሆኑን በግልጽ ባስቀመጠበት አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 2 ላይ “… በፖለቲካ ፓርቲነት ለመመዝገብ ማመልከቻ ባቀረበ አካል ላይ ተቃውሞ ያለው ማንኛውም ሰው ተቃውሞ ማቅረብ እንዲችል ቦርዱ የምዝገባ ማመልከቻ መቅረቡን በተለያየ ማስታወቂያ ለህዝብ ይገልጻል” ይላል።

 

 

አንቀጽ 3 ደግሞ “በንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት ተቃውሞ ያለው ሰው ማስታወቂያው በወጣ በ14 ቀን ውስጥ ተቃውሞውን ለቦርዱ ማቅረብ ይኖርበታል። ቦርዱ በዚህ ጊዜ ውስጥ ለአመልካቹ ፈቃድ አይሰጥም” ይላል።

 

 

በዚህ ተሻሽሎ በፀደቀው አዋጅ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይ የሚያገኙትን የገንዘብ መዋጮና እርዳታ በሚመለከትም ማሻሻያ ተደርጎበታል። ፓርቲዎቹ የሚያገኙትን የገንዘብ ልክ፣ የለጋሹን ሙሉ ስም እንዲያሳውቁ ያስገድዳቸዋል። የቀድሞው ሕግ ላይ ግዳጅ እንዳልነበረበት ይታወቃል።

 

 

የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ በአዋጁ ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡ ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያ “አዋጁ እንደሚለው የፓርቲ ፈቃድ ለማግኘት የጠየቀን አካል ማንም ሰው ተነስቶ ተቃውሞ በማቅረብ ፍቃድ እንዳይሰጠው የሚያስከለክል ከሆነ ቦርዱ ለፈለገው አካል ብቻ የፓርቲ ፈቃድ እንዲሰጥ የሚያስችለውን ሙሉ እና ፍፁም ሥልጣን አዋጁ ሰጥቶታል” ሲሉ ያላቸውን ስጋት ገልጠዋል።

 

 

አዋጁን ለማጽደቅ በተወካዮች ምክር ቤት በተደረገ ውይይት ላይ ፓርላማ ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች ያላቸውን ተቃውሞ አሰምተው ነበር። ከእነዚህም ውስጥ የኦፌዲን ሊቀመንበር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ አንዱ ናቸው።

 

 

አቶ ቡልቻ አዋጁ የሠለጠኑትና ከምዕራባውያን ሀገሮች ሕጎች ጋር ተመሳሳይነት እንደሌለውና ከሁሉም ሀገራት የከፋና ጨቋኝ የሆነ ሕግ ተመርጦ የተዘጋጀ እንደሆነ ገልፀዋል።

 

 

አቶ ቡልቻ “ገዥው ፓርቲ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲቀጭጩና እንዲጠፉ ፍላጎት አለው፤ እኛ ግን ከህዝብ ጋር ስለሆንን አንጠፋም” ብለዋል። አቶ ቡልቻ አዋጁ የምርጫ ቦርድ ውሳኔን ያልተቀበለ ፓርቲ ወደ ፍርድ ቤት ይሄዳል የሚል ግልጽ ዓረፍተ ነገር እንዳልተቀመጠበት ገልፀው፤ “ይሄ ሁኔታ የምርጫ ቦርድ ሰዎች አይሳሳቱም ብሎ መደምደም ይሆናል” ብለዋል።

 

 

አዋጁ ህዝብን ሳይሆን ገዥውን ፓርቲ ብቻ የሚጠቅም እንደሆነ የገለፁት ደግሞ አቶ ተመስገን ዘውዴ ናቸው። ሕጉ በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ከፍተኛ ጣልቃ-ገብነት ያለውና ፓርቲዎች እንዳያድጉ የሚያደርግ መሆኑን አቶ ተመስገን ተናግረዋል።

 

 

“አብዛኞቹ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሀገር የተሰደዱት በደርግና በዚህ መንግሥት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ ተደርጎባቸው ነው። እነዚህን ሰዎች ገንዘባችሁን አምጡ፣ ፖለቲካ ውስጥ ግን አትግቡ የሚል ነገር አያስኬድም” ሲሉ አቶ ተመስገን በአዋጁ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ አሰምተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጡት ያነጋገራቸው አንድ የፖለቲካ ታዛቢ የአዋጁን በዚህ ወቅት መጽደቅ ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ የፈቃድ ጥያቄ ጋር አያይዘው ፍራቻ እንዳላቸው ገልፀዋል። “ከወያኔ የሥልጣን ዘመን በመነሳት ይህኛውን አዋጅ/ሕግ ‘የአቶ ስዬ ሕግ’ ከሚባለው ጋር ማመሳሰሉ የሚቀል ይመስለኛል” በማለት ነበር አስተያየታቸውን የጀመሩት።

 

 

“በምርጫ 97 የተሳተፈውንና ታሪክ የሠራው ቅንጅት ዋና ሰዎች የሚባሉት አሁን አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ በሚል ፈቃድ ላማውጣት እየተንቀሳቀሱ ያሉት ሰዎች ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች እንደተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ፈቃድ ተሰጥቷቸው እንዲቀጥሉ የወያኔ ባለሥልጣናት አይፈልጉም። በመሆኑም ይህንን ሕግ ቀድመው በማጽደቅ ፓርቲው ለረዥም ጊዜ ሳይመዘገብ እንዲቆይ ለማድረግ የወጠኑት ተንኮል ነው የሚል ስጋት አለኝ።” ብለዋል እኚሁ የፖለቲካ ታዛቢ። 

 

 

አክለውም “ሕጉ አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲን ሆን ብሎ ለመምታትና ፈቃድ ለመከልከል ያነጣጠረ መሆን አለመሆኑን በተጨባጭ ለማየት ጥቂት ሣምንታት መጠበቅ ይኖርብናል። ምክንያቱም ፓርቲው ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት ለመመዝገብ የሚያስችለውን ዝግጅት እንዳጠናቀቀና ወደ ምርጫ ቦርድ ለምዝገባ እንደሚሄድ ይታወቃልና” ሲሉ እኚሁ የፖለቲካ ታዛቢ ለኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ገልጠዋል።

 

 

ፓርቲዎች የሚያገኙትን የገንዘብ መዋጮና እርዳታን በሚመለከት ያዋጣውንና የረዳውን ማንነት፣ ስም፣ … የማሳወቅ ግዴታ እንዲኖርባቸው ተሻሽሎ የፀደቀው አዋጅ ማካተቱን አስመልክቶ እኚሁ ታዛቢ አስተያየታቸውን ሰጥተውናል። “የተቃዋሚ ፓርቲዎች በተለይም የአንድነት ፓርቲ ከፍተኛ የገንዘብ ምንጭ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ይታወቃል። እናም ፓርቲዎች የገንዘብ ምንጫቸውን የማሳወቅ ግዴታ ካለባቸው፤ በተለይ በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚያደርጉት የገንዘብ ድጋፍ እጃቸውን እንዲሰበስቡ ለማስፈራራት ያነጣጠረ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

 

"ከሁሉም በላይ ደግሞ በሀገር ውስጥ ያሉትና ለተቃዋሚ ፓርቲዎች የገንዘብ መዋጮ የሚያደርጉን ግለሰቦች ለማስፈራራትና ብሎም ለመበቀል ወያኔ ያሰላው እንደሆነ ለመገመት አያስቸግርም። በሀገር ውስጥ ያሉ ባለሀብቶች በተለይ ነጋዴዎች በምርጫ 97 በተለይ ከቅንጅት ጎን ተሰልፈው እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው" ሲሉ ያላቸውን ስጋት ገልጠዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ