የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች በአደጋ ውስጥ ናቸው ተባለ
ታምሩ ገዳ (ከለንደን)
“የኢትዮጵያ ገዳማት፣ አድባራት እና የአብነት ት/ቤቶች (የቆሎ ት/ቤቶች) ያሉበትን ነባራዊ ሁኔታ” በሚል ርዕስ ዙሪያ አጭር ጥናታዊ ጽሑፍ በቅረብ ለግንዛቤ ያህል ለንደን ውስጥ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አማኞች እና ጥሪ ለተደረገላቸው እንግዶች ባለፈው ሣምንት ገለጻ ያደረጉት እንግሊዝ ሀገር ውስጥ በተለዋጭ የተፈጥሮ ሀብት ዙሪያ ከፍተኛ ምርምር በማድረግ ላይ የሚገኙት አቶ በላቸው ጨከነ ናቸው።
በአሁኑ ወቅት በርካታ ዓመታት ያስቆጠሩት ሕንፃ አብያተ ክርስቲያናት በእድሳት እጦት ምክንያት በውስጣቸው የሚገኙት ውድ እና ብርቅዬ ቅርሶች መበላሸት፣ ዘራፊዎች እነዚህ ብርቅዬ እና ውድ የሆኑ ንዋየ ቅድሳት ለመስረቅ ማተኮራቸው፣ በተለያዩ ጊዜያት በገዳማት እና በዙሪያቸው በሚገኙ ደኖች ላይ የእሳት አደጋ መድረስ እንዲሁም የቆሎ ተማሪዎች እና መምህራኖቻቸው በምግብ እጦት እና በእርዛት ምክንያት ቀያቸውን እየለቀቁ ወደ ከተሞች መሠደድ በታሪካዊ የኢትዮጵያ ቅርሶች ላይ ካነጣጠሩት ዋነኛ ችግሮች የሚጠቀሱ ናቸው ሲሉ አቶ በላቸው አስረድተዋል።
አቶ በላቸው ከዚህ ፀሐፊ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እነዚህ ታሪካዊ እና ብሔራዊ ቅርሶችን ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ማስረከብ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ኃላፊነት እንዳልሆነ፤ ይልቁንም ሀገራችንን፣ ባህላችን፣ ቅርሳችንን እንወዳለን የሚሉ ወገኖች በሙሉ በግል፣ በቤተሰብ እና በቡድን በመሆን በቅርሶች ላይ የተጋረጡትን አደጋዎች ሊታደጉ ይገባቸዋል ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።
ይህንን የማሰባሰብ ዘመቻን በተመለከተ በአሜሪካ የሚገኙ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እያደረጉት ያለውን ጥረት አቶ በላቸው ሳያመሰግኑ አላለፉም። በተለያዩ ወቅቶች ከኢትዮጵያ በድብቅ መጥተው በእንግሊዝ፣ በአሜሪካ፣ በቫቲካን (ኢጣሊያ) ... ወዘተ በመሳሰሉት ስምንት ሀገሮች ከሦስት ሺህ በላይ ብርቅዬ የኢትዮጵያ ንዋየ ቅድሳት እና የብራና መጻሕፍት ለባዕዳኑ ሙዚየሞች ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ማስገኛ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ ሲሉ አቶ በላቸው በቁጭት ተናግረዋል።
በየዓመቱ ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ወደ ሀገር ቤት ጎራ ከሚሉት ጎብኚዎች መካከል ከ85% በላይ የሚገመቱት አመጣጣቸው እነዚህኑ በመጥፋት ላይ የሚገኙትን ታሪካዊ፣ ኃይማኖታዊ እና ብሔራዊ የኢትዮጵያ አሻራዎች የሆኑትን ቅርሶች ለመመልከት ብቻ እንደሆነ በጥናታዊ ጽሑፋቸው ላይ አካትተዋል።
አቶ በላቸው በቅርቡ ከአማርኛ ወደ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሣይኛ እና ጀርመንኛ የተተረጎመ ዘመናዊ የሕፃናት መማሪያ ዲቪዲ በማዘጋጀት የዜግነት ድርሻቸውን መወጣታቸውን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸው አይዘነጋም።



