የአማራ ክልል ሹምሽር አካሔደ
የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ላቀ አያሌው (በግራ)፣ አዲሱ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ (በቀኝ)
የሹመቱ አሠጣጥና የአመራሮች መቀያየር ከፍተኛ ሙግት አስነስቷል
ኢዛ (ረቡዕ የካቲት ፲፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 19, 2020)፦ የአማራ ክልላዊ መንግሥት ባካሔደው አስቸኳይ ስብሰባ የተለያዩ ሹመቶችን ያጸደቀ ቢሆንም፤ የሹመቱ አሠጣጥና የአመራሮች መቀያየር ከፍተኛ ሙግት አስነስቷል።
በትናንትናው ዕለት (የካቲት 10 ቀን 2012 ዓ.ም.) በዚህ የክልሉ አስቸኳይ ስብሰባ የክልሉ ከፍተኛ የሚባሉ አራት ባለሥልጣናት ከክልሉ ወደ ፌዴራል እንደሚዛወሩና በእነርሱ ምትክ አዳዲስ ተሿሚዎች እንዲተኩ የተደረገ ቢሆንም፤ ከጉባዔው ተሳታፊዎች ለክልሉ ሊሠሩ የሚችሉ አመራሮች ወደ ፌዴራል መሔድ የለባቸውም የሚል ሙግት እስከማስነሳት ደርሶ ነበር።
ኾኖም የአብዛኛው ሹመት በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል። በተለይ የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ለመሰየም በተደረገው የድምፅ አሠጣጥ አብላጫው ተሳታፊ ሹመቱ እንዲጸድቅ ድምፅ የሠጠ ቢሆንም፤ 3 ተቃውሞና 44 የሚኾኑ የጉባዔው አባላት ድምፀ ተዓቅቦ ማድረጋቸው ሹምሽሩን በተመለከተ የነበረውን ልዩነት ያመለከተ እንደኾነ እየተጠቀሰ ነው። “በዚህ ወቅት ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች ከክልሉ ኃላፊት መልቀቅ የለባቸውም” እስከማለትም ተደርሶ ነበር።
በትናንትናው ሹምሽሩ ወደ ፌዴራል ለከፍተኛ ኃላፊነት እንደሚሔዱ ተገልጾ፤ ከክልል ኃላፊነታቸው የለቀቁት የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት፤ አቶ ላቀ አያሌው (የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት)፤ አቶ መላኩ አለበል (በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ፣ አሁን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር)፤ የአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ቧያለው፤ እንዲሁም የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ፈንታ ደጀን ናቸው።
የእነዚህን ነባር አመራሮች ወደ ፌዴራል መሔድ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ በፓርቲ ውሳኔ የተፈጸመ ስለመኾኑ ጠቅሰዋል። ከእነዚህም ውስጥ አቶ ፈንታ ደጀን፤ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ሿሚነት የፌዴራል መንግሥቱ የከተማና ልማት ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ዴኤታ ኾነው መሾማቸው ታውቋል።
በእነርሱ ምትክ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኾነው እንዲሠሩ ዶ/ር ፋንታ ማንደፍሮ ተሹመዋል።
የክልሉ የሰላምና ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ በመኾን ሲያገለግሉ የነበሩት አቶ አገኘሁ እንግዳ ደግሞ በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኾነዋል።
አቶ አገኘሁ እንግዳን ተክተው የክልሉ ሰላምና የሕዝብ ደኅንነት ቢሮ ኃላፊ በመኾን አቶ ሲሳይ ዳምጤ ተሹመዋል።
ከዚህም ሌላ ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የማኅበራዊ ክላስተር አስተባባሪ፣ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊ፤ ዶክተር ሰይድ ኑሩ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የከተማ ልማትና ቤቶች ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ፤ አቶ ተፈራ ወንድማገኝ የክልሉ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ኾነው ተሹመዋል። (ኢዛ)



