አንድነት ፓርቲ በረቂቅ ሰነዶቹ ላይ ቅዳሜ ይወያያል
Ethiopia Zare (ኀሙስ ሚያዝያ 9 ቀን 2000 ዓ.ም. April 17, 2008)፦ በተቀዳሚት ምክትል ሊቀመንበሯ ወ/ት ብርቱካን የሚመራው የቀድሞው የቅንጅት የአመራር አባላት ለማቋቋም ላይ የሚገኙት አንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ፕሮግራም፣ በመመስረቻ ሰነድ እና በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ የፊታችን ቅዳሜ ውይይት ሊካሄድ እንደሆነ ታወቀ።
ፓርቲውን ለመመስረትና ሕጋዊ ፈቃድ አግኝቶ ለመንቀሳቀስ ያስችል ዘንድ የፓርቲውን የአመሠራረት ሂደት በተመለከተ ሰነዶችን እንዲያሟላ ኮሚቴ መቋቋሙ አይዘነጋም። ይኸው የተቋቋመው ኮሚቴ ከዚህ በፊት የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲን ፕሮግራም፣ መመሥረቻ ጽሁፍና መተዳደሪያ ደንብ መርምሮ ያሉትን ጉድለቶች በማሟላት አስተካክሎ እንዲያቀርብ በታዘዘው መሠረት ሥራውን ማጠናቀቁን ለማወቅ ችለናል።
በዚህም መሠረት ቅዳሜ በሚደረገው ውይይት ላይ የቀድሞው ቅንጅት የላዕላይ ም/ቤት አባላት፣ የአዲስ አበባና የፓርላማ ተመራጮች የነበሩ እና ለድርጅቱ ድጋፍ በማድረግ የሚታወቁ በአጠቃላይ 100 ሰዎች ይገኙበታል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ኮሚቴው አጠናቅቆ አስተካክሎ በሚያቀርበው ረቂቅ የፓርቲው ፕሮግራሞችና ሌሎች ሰነዶች ላይ ይወያያሉ።