የደራሲ አበራ ለማ ታሪካዊ ልብ-ወለድ መጽሐፍ በአዲስ አበባ ተመረቀ
ማትያስ ከተማ (ከስዊድን)
Ethiopia Zare (ሐሙስ የካቲት 17 ቀን 2003 ዓ.ም. February 24, 2011)፦ ”ጥሎ ማለፍ” የተሰኘው የአንጋፋው ጋዜጠኛና ደራሲ አበራ ለማ አዲስ ልብ-ወለድ መጽሐፍ እና በቅርቡ የወጣው ”እውነትም እኛ ...” የተሰኘው የግጥም ዲቪዲ የካቲት 12 ቀን 2003 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ተመረቁ።
ምርቃቱ የተካሄደው በአዲስ አበባው የሀገር ፍቅር ትያትር አዳራሽ ሲሆን፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የደራሲው አድናቂዎች፣ ቤተሰቦች፣ የኪነ ጥበብ ሰዎች እና የጥበብ አፍቃሪዎች በተገኙበት መሆኑን ለመረዳት ችለናል።
ይህን የምረቃ በዓል ያስተባበረው የፀሐፌ ተውኔት ተስፋዬ አበበ ፕሮሞንሽን ሲሆን፣ ሥነ-ሥርዓቱን የመሩት ረዳት ፕሮፌሠር ተስፋዬ ገሠሠ ነበሩ። ፕሮፌሠር ተስፋዬ በመክፈቻ ንግግራቸው የደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማን ቀደምት ሥራዎች አስተዋውቀው፤ በተለይም በጋዜጠኝነት የሥራ ዘመናቸው እጦር ሜዳ ድረስ እንደዘመቱ በመግለጽ፣ በወቅቱ በነበራቸው ቆራጥነትና ድፍረት ”የጦር ሜዳው ቀሲስ” ተብለው ይጠሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
በመቀጠልም የደራሲ አበራ ለማ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ርዕሰ መምህር የነበሩት አቶ ኃይሉ አቢ ”ጥሎ ማለፍ” የተባለውን የደራሲውን ልብ-ወለድ መጽሐፍ በመመረቅ ንግግር አድርገዋል። እንዲሁም ”እውነትም እኛ …” የተሰኘውን የግጥም ቪዲዮ የድምፅና የምስል ቅንብር የሠሩት የአቶ ክብረት መኮንን ወላጅ እናት ዲቪዲውን መመረቃቸውን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዜና ያስረዳል።
![]() |
የመጽሐፍና የዲቪዲው ምረቃ በተካሄበት ወቅት |
በተጨማሪም ደራሲ ሙሉ ሠለሞን በአፍሪካውያን ሴት ደራስያን ማኅበር እና በድርጅታቸው በሙሉ ሠለሞን ፍኖተ ምስጋና የበጎ አድራጎት ስም ደራሲው በ”ጥሎ ማለፍ” እና በ”እውነትም እኛ ...” ሥራቸው ለኢትዮጵያ ሥነ-ጽሑፍ እድገት ላበረከቱት አስተዋፅዖ የአድናቆት የምስክር ወረቀት አበርክተውላቸዋል።
![]() |
በምረቃው ላይ ከተገኙት እንግዶች በከፊል |
”ጥሎ ማለፍ” በደርግ ዘመነ መንግሥት በተፈጸመ እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ታሪካዊ ልብ-ወለድ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ዕትሙ በዓይናለም የመጻሕፍት አከፋፋይ ድርጅት አማካይነት በገበያ ላይ ውሏል። የዚህ መጽሐፍ ሽያጭ እኩሌታ ገንዘብ በደራሲው መልካም ፍቃድ ለተስፋዬ አበበ የኪነጥበባት በጎ አድራጎት ድርጅት እንዲውል መፈቀዱንም የደረሰን ዜና ያስረዳል።
![]() |
ደራሲ ሙሉ ሠለሞን ሽልማታቸውን ለደራሲ አበራ ለማ ሲያቀርቡ |
የደራሲ አበራ ለማ ”እውነትም እኛ …” የግጥም ዲቪዲ በአውሮፓ ልዩ ልዩ ሀገሮች ምረቃ ተደርጎለት እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም። ቀጣዩ የምረቃ ሥነ-ሥርዓት በሰሜን አሜሪካ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።






