Ethiopia Zare (ቅዳሜ ግንቦት 9 ቀን 2000 ዓ.ም. May 17, 2008)፦ በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚመራው የቀድሞው የቅንጅት ፓርቲ፣ የአሁኑ የ”አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ” በነገው ዕለት የላዕላይ ም/ቤቱ ተሰብስቦ ፓርቲው ሕጋዊ ፈቃድ ለማግኘት ያስችለው ዘንድ ወሳኝ የሆኑ ውሳኔዎች ላይ እንደሚደርስ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች ገለጹ።

 

ላዕላይ ምክር ቤቱ በነገው ዕለት በሚያደርገው ስብሰባ የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ መቼ እንደሚጠራ ይወስናል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህም ሌላ ጠቅላላ ጉባዔው የት እንደሚደረግ፣ በምን ጉዳዮች ላይ እንደሚወያይ፣ … እንደሚወስን እነኝሁ የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች አስረድተዋል።

 

ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ ዛሬ እንደዘገብነው ከሆነ አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ የተሰኘው ፓርቲ እስካሁን ድረስ ሕጋዊ እውቅና ከምርጫ ቦርድ አለማግኘቱ ይታወቃል። ከዚህም ሌላ ፓርቲው ሕጋዊ ፈቃድ እና እውቅና እንዲሰጣቸው ለምርጫ ቦርድ ማመልከቻ እንዳላስገቡ ይታወቃል።

 

በነገው ዕለት የሚሰበሰበው የላዕላይ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔው የሚደረግበትን ቀን ወስኖ ሲያበቃና ጠቅላላ ጉባዔው ሲካሄድ ፓርቲው ሊቀመንበሩን፣ ምክትል ሊቀመንበሩን፣ ዋና ፀሐፊውን፣ የሕዝብ ግንኙነቱን፣ … በአጠቃላይ የፓርቲውን ከፍተኛ አመራር አባላት እና አካላት እንደሚመርጥ ይጠበቃል።

 

አንድነት ለዲሞክራዲና ለፍትህ የፓርቲውን አመራሮች መርጦ ሲያበቃና ምርጫ ቦርድ የሚጠይቃቸውን ፎርማሊቲዎች አሟልቶ ሲያጠናቅቅ የፓርቲውን ሕጋዊ ፈቃድ ለማግኘት ለምርጫ ቦርድ ማመልከቻ እንደሚያስገባ ለማወቅ ችለናል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ