ኢ/ር ኃይሉ ሻውል አዲስ አበባ ገቡ
Ethiopia Zare (እሁድ ግንቦት 24 ቀን 2000 ዓ.ም. June 1, 2008)፦ የቀድሞው የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር ኢንጂንየር ኃይሉ ሻውል በትናንትናው ዕለት አዲስ አበባ መግባታቸውን ለኢትዮጵያ ዛሬ የደረሰው ሪፖርት አስረዳ።
ትናንት ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ቤተሰቦቻቸው እንደተቀበሏቸውና ወደ ቤታቸው እንደሄዱ የደረሰን ዘገባ ይጠቁማል።
ኢ/ር ኃይሉ ባለፈው ዓመት ጳጉሜን 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ ሰሜን አሜሪካ ተጉዞ ከነበረው የቅንጅት ልዑካን ቡድን ጋር ሳይጓዙ ቀርተው፤ ከቀናት በኋላ በዚያው በጳጉሜን ወር ለብቻቸው ወደ አሜሪካ ተጉዘው የልዑካን ቡድኑን ሳይቀላቀሉ መቅረታቸው አይዘነጋም።
የቀድሞው ቅንጅት በአሁኑ ሰዓት በሀገር ውስጥ ብቻ አምስት ቡድኖች ሲኖሩት፣ አንዱ በኢንጂንየር ኃይሉ ሻውል የሚመራው መሆኑ ይታወቃል። ይኸው ቡድን “ቅንጅት” የሚለው ስም ለእኔ ይገባኛል በማለት ክስ መስርቶ እየተከራከረ እንደሆነ ይታወቃል።
የኢንጂንየሩ ቡድን ጠቅላላ ጉባዔ ለመጥራት የኢንጂንየሩን ወደ ሀገር ቤት መመለስ የሚጠባበቅ ሲሆን፣ በቅርቡ ጠቅላላ ጉባዔ ይጠራል ተብሎ ይጠበቃል።
ከኢንጂንየሩ ጋር የተሰለፉት የቀድሞ የቅንጅት የላዕላይ ምክር ቤት አባላትና አመራሮች የሚከተሉት ናቸው።
1. መኢአድ የነበሩት - አቶ አባይነህ ብርሃኑ
2. መኢአድ የነበሩት - ሻ/ቃ ጌታቸው መንግሥቴ
3. መኢአድ የነበሩት - ወ/ሮ መሶበወርቅ ቅጣው
4. መኢአድ የነበሩት - ዶ/ር ታዲዎስ ቦጋለ
5. መኢአድ የነበሩት - አቶ አሰፋ ሀ/ወልድ
8. መኢአድ የነበሩት - አቶ ገ/ፃዲቅ ኃ/ሥላሴ
9. መኢአድ የነበሩት - አቶ ማሙሸት አማረ
8. ኢዴአፓ መድን የነበሩት - አቶ ወንደሰን ተሾመ



