Eng. Hailu Shawel“በሚዲያ የሚደረገው ታንቡርና ጩኸት የህዝብን አስተሳሰብ ይለውጣል ብላችሁ አታስቡ” ኢ/ር ኃይሉ ሻውል

Ethiopia Zare (እሁድ ሰኔ 1 ቀን 2000 ዓ.ም. June 8, 2008)፦ የቀድሞው የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር የነበሩት ኢንጂንየር ኃይሉ ሻውል ከሀገር ቤት ከወጡ ከዘጠኝ ወራት በኋላ ባለፈው ሣምንት ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2000 ዓ.ም. ተመልሰው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውንና ኀሙስ ግንቦት 28 ቀን መግለጫ መስጠታቸውን መዘገባችን ይታወሳል። የኢ/ር ኃይሉን ጋዜጣዊ መግለጫን አስመልክቶ ከደረሱን ዘገባዎች ውስጥ የሚከተለውን አቅርበነዋል።

 

በአራት ፓርቲዎች ውህደት ተመስርቶ በምርጫ 97 ተሳትፎ የነበረው ቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ የፓርቲው ሕጋዊ ፈቃድ ለአቶ አየለ ጫሚሶ ቢሰጥም፤ በፓርቲው አመራሮች የተፈጠረው ውዝግብ ግን ማብቂያ የሌለው መዘዝ ሆኖ ለሦስት ዓመታት ዘልቋል።

 

አመራሮቹ ከእስር ከተፈቱ በኋላ የተጋጋለው ልዩነቶቻቸው ባስ ብሎ በእስር የነበሩት ዋና ዋና የፓርቲ አመራሮች ለሦስት ተከፍለዋል። አሁንም ቅንጅት ነን ብለው ራሳቸውን የሚጠሩት እነ ኢ/ር ኃይሉ ሻውል፣ አንድነት ፓርቲን ለመመስረት በዝግጅት ላይ ያሉት 18ቱ የቀድሞ የላዕላይ ምክር ቤት አባላት እና “ግንቦት 7 ለነፃነት፣ ለፍትህና ለዲሞክራሲ” በሚል በውጭ ሀገር ንቅናቄ የመሰረቱት ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ናቸው።

 

ከዛሬ ነገ ወደ ሀገር ቤት ይገባሉ እየተባሉ ሲጠበቁ የነበሩት የቀድሞው የቅንጅት ፓርቲ ሊቀመንበር ኢ/ር ኃይሉ ሻውል “ግርግር ስለማልፈልግ ለቤተሰቦቼ ብቻ ነግሬ ድንገት መጣሁ” በማለት አመጣጣቸውን ገልፀው፣ ኀሙስ ግንቦት 28 ቀን 2000 ዓ.ም. (June 5, 2008) ቴዎድሮስ አደባባይ በሚገኘው የመኢአድ (የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት) ጽ/ቤት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

 

በሳቸው ስር የሌሉትን አባላት፤ “የኢትዮጵያ ህዝብ የፓርቲዎች መብዛት የሚያስደስተው ይመስል፣ ፓርቲያቸውን በውጫዊና በውስጣዊ ጫና እየሰነጣጠቁ፣ የተወሰኑ ግለሰቦች ከመካከላቸው እየወጡ፣ ትናንሽ ፓርቲዎችን እንደ ችግኝ በማፍላት የወጡ አፈንጋጮች ናቸው” የሚል ስያሜ ሰጥተዋቸዋል።

 

የህዝብ ድጋፍ ያላቸው እነ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ፣ ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም፣ ... እንዴት አፈንጋጮች ይባላሉ በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “ከተማ ውስጥ ተንፈራፍረን እስር ቤት ስለገባን ጀግና የሆንን ይመስለናል። የዶክተሮች ስም ቢደራረብ ምን ዋጋ አለው ሥራ የሚለካው በዲግሪ አይደለም፤ በሥራ ነው” ብለዋል።

 

ኢ/ር ኃይሉ ሻውል ከተለያዩ የግል ሚዲያዎች በርካታ ጥያቄዎች የቀረቡላቸው ሲሆን፣ የመረጥናቸውን ጥያቄዎችና የሰጧቸውን መልሶች እንደሚከተለው ቀርቧል።

 

ጥያቄ፦ መግለጫውን የሰጣችሁት በቅንጅት ስም ነው፣ ቦርዱ ደግሞ ይህን ስያሜ ለእነ አቶ አየለ ጫሚሶ ሰጥቷል። በዚህ ስም መግለጫ ለመስጠት ምን የሕግ ድጋፍ አላችሁ?

 

ኢ/ር ኃይሉ፦ እነ አቶ ተመስገንም ሆነ አቶ አየለ ጫሚሶ ያቋቋሙት አዲስ ፓርቲ ነው፣ መስከረም 14 ቀን 1998 ዓ.ም. በቅድሚያ የተቋቋመው የኛ ፓርቲ ነው። የቅንጅትን ዓርማና ስያሜ ከያዙት አብረን እንቀጥል ብንል እንኳን መቀጠል አንችልም። እነሱ ሌላ እኛ ሌላ ነን፤ የኛ ጥያቄ የፖርቲያችን ስያሜ ለምን ያለ አግባብ ለሌላ ተሰጠ የሚል ነው፤ እሱን በሚመለከት ደግሞ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት አቅርበነዋል።

 

ጥያቄ፦ የቀድሞው ቅንጅት አመራሮች ሦስት ቦታ ተከፋፍለዋል፣ የዚያ ፓርቲ ሊቀመንበር ደግሞ እርሶ ነበሩ፤ አመራሩ ለመከፋፈሉና በአንድ ላለመቀጠሉ የእርሶን የአመራር ድክመት አያሳይም?

 

ኢ/ር ኃይሉ፦ እኔ ቅንጅት ሦስት ቦታ መከፈሉን አላውቅም፤ ምናልባት እስር ቤት ተቀብሬ ሳልሰማ ቀርቼ ይሆናል። ቅንጅትን እነማን ናቸው የመሰረቱት ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። በ90 ቀናት ዝግጅት ምርጫውን አሸነፍን ብንል ራሳችንን ማታለል ይሆናል። የሦስት ወር ግርግር ቅንጅትን አልመሰረተም። ቅንጅት በሚሊዮን የሚቆጠር አባላት ነው ያሉት፤ እነሱ ደግሞ አልተከፋፈሉም ምናልባት መከፋፈሉ አለ ከተባለ በተወሰኑ አመራር አባላት ውስጥ ነው። እነሱ ደግሞ ከአዲስ አበባ ወጥተው፣ ከህዝብ ጋር ተነጋግረው የማያውቁ ናቸው። በሚዲያ የሚደረገው ታንቡርና ጩኸት፣ የህዝብን አስተሳሰብ ይለውጣል ብላችሁ አታስቡ። ከተማ ውስጥ ተንፈራፍረን እስር ቤት ስለታሰርን ጀግና የሆንን ከመሰለን ተሳስተናል። የአመራር ድክመትን በሚመለከት ኖሮብኝ ሊሆን ይችላል፤ ዲሲፕሊን የሌለው ፖርቲ የትም አገር ውጤታማ ሊሆን አይችልም፤ ማንም እንደፈለገ የሚጮኽበት ቦታ ውጤታማ መሆን አይቻልም። የኔን አመራር በሚመለከት ጓደኞቼ ይመረምሩታል፤ የኔን አመራር መዘርዘር የኢትዮጵያ ባህል አይፈቅድልኝም።

 

የአመራር ብቃት ላይ የተነሳውን ጥያቄ በሚመለከት አብረዋቸው መግለጫውን የሰጡት አቶ አባይነህ ብርሃኑ መልስ ሰጥተውበታል።

 

“የፕሬዝዳንታችንን አመራር ጉዳይ፣ እንኳን እኛ የፓርቲው አባላት፤ ለቀው የሄዱት ሳይቀሩ በአራቱ ማዕዘን እየዞሩ ከአቶ ኃይሉ ጋር ታርቀናል፣ የፓርቲያችን ሊቀመንበር እሳቸው ናቸው እያሉ ነው ፊርማ ሲያሰባስቡ የቆዩት፤ ይኼ ደግሞ ጠንካራነትን የሚያሳይ ነው።

 

ጥያቄ፦ በቅንጅት ስም በርካታ ገንዘብ ሲሰበሰብ ነበር፤ ምን ልታደርጉ አሰባችሁ?

 

ኢ/ር ኃይሉ፦ በውጭ አገር በቅንጅት ስም የተሰበሰበ በርካታ ገንዘብ አለ፤ ኃይሉ በሌለበት ኃይሉ ይመጣል እያሉ፣ ወንበር እየያዙና እያዘጋጁ፣ የኔን ፎቶግራፍ እየለጠፉ፣ ገንዘብ ሲያሰባስቡ ነበር፤ ይመጣል፣ ይናገራል እያሉ እኔ ፎቶዬን ሳይ በጣም ነው የገረመኝ የአገር ውስጡን ደግሞ አቶ አባይነህ ይናገር፡-

 

አቶ አባይነህ፦ በዚህ አገር ገንዘብ ለማሰባሰብ ተሞክሯል፤ በፓርቲው ስም እከሌን ለማቋቋም በሚል በብርቱካን ስም የተሰበሰበ ገንዘብ አለ፤ ይህን ተቃውመናል። ለወጣቶች ማጠናከሪያም በሚል በጋዜጣ አውጥተው ካርድ ለመሸጥ ሲሉ ደርሰንበት መንግሥት ጣልቃ እንዲገባበትና እንዲቋረጥ ተደርጓል።

 

ጥያቄ፦ በምርጫ 97 የምናውቃችሁ የቅንጅቱ አመራሮች በጋራ ሆናችሁ፣ እንደ አንድ ጠንካራ ፖርቲ ለህዝብ መግለጫ ስትሰጡ ነበር፤ በዛም ሂደት ህዝብ ከፍተኛ ድጋፍ ሰጥቷችኋል፤ ከእስር ከተፈታችሁ በኋላ ግን ራሳችሁን አጥርታችሁ መቀጠል አልቻላችሁም፤ ከዛ ይልቅ በየሚዲያው ላይ ስትወነጃጀሉ ነው የሚሰማው፣ ከዚህ ሁሉ በኋላ ወደ መድረክ ስትወጡ የህዝብ ድጋፍ አለን ብላችሁ ታምናላችሁ?

 

ኢ/ር ኃይሉ፦ የምናውቃችሁ አመራሮቹን ነው ተብሏል፤ የፖለቲካ ፓርቲ ትግል ስንል እንሳሳታለን ብዙ ታጋዮች አሉ። አዲስ አበባ ተቀምጠው ሳይሆን በበቅሎ፣ በእግር፣ በክፍት መኪና ተጭነው በየገጠሩ የሚዞሩ አባላቶቻችን አመራሩ እነኛን ለማቀናጀት የተቋቋመ እንጂ ለመሥራት አይደለም፣ ለመመፃደቅ አይደለም፤ አንዳንዶቹ እኮ እስከተመረጡበት ቀን ድረስ የፓርቲው አባል ያልነበሩ ናቸው። ስለ ህዝብ ድጋፍ በሚመለከት እናንተም የትም ቦታ ሄዳችሁ መጠየቅ ትችላላችሁ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ አልደከመም፣ አብሮን ቆሟል፣ በቃኝ፣ ደከመኝ አላለንም ሁሉም በትዕግስት እየጠበቀን ነው።

 

ጥያቄ፦ በምትጠሩት ጠቅላላ ጉባዔ የአመራር ምርጫ ይደረጋል ብለዋል፣ ለሊቀመንበርነት ይወዳደራሉ?

 

ኢ/ር ኃይሉ፦ ይህንን የሚወስነው ፓርቲዬ ነው እኔ አይደለሁም።

 

ኢ/ር ኃይሉ ከጋዜጠኞች ላቀረቡላቸው ሌሎች ጥያቄዎችም መልስ ሰጥተዋል። ተደጋጋሚነት ያላቸውን ጥያቄዎች ያላካተትናቸው ሲሆን፣ ለጋዜጠኞች በሰጡት ምላሽም ሆነ በፅሁፍ በሰጡት መግለጫ፣ ፓርቲያቸው በፍርድ ቤት የጀመረውን የስያሜ ጉዳይ እልባት እንደሚያሰጡለትና የጀመሩትን የሠላማዊ ትግል አጠናክረው እንደሚንቀሳቀሱ ገልፀዋል።

 

አንድነት ፓርቲን በሚመለከት፡-

 

የተወሰኑ ቡድኖች ከቅንጅቱ አፈንግጠው በራሳቸው መንገድ እንደ አዲስ 1ሺ 500 ፊርማ አስባስበው፣ አዲስ ጠቅላላ ጉባዔ ጠርተው የሚመሰርቱት ፓርቲ ነው።

 

የእነ ዶ/ር ብርሃኑን ንቅናቄ በሚመለከት

 

አንድ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የፓርቲውን ስልት ሊለውጥ ይችላል፤ ነገር ግን እነሱ በሠላማዊ ትግል ምን ሠርተው? ምን ችግር አጋጥሞአቸው? ምን ውጤት አይተው ነው ስልታቸውን የሚቀይሩት? ለምን መሄድ አስፈለገስ ብለዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ