ኢንጂንየር ኃይሉ ሻውል ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጡ
ስብሰባው በመኢአድ ቢሮ ነበር
"የፖለቲካ ሥራ በጋዜጣ ጡሩንባ በመንፋት አይደለም" ኢንጅነር ኃይሉ
Ethiopia Zare (ኀሙስ ግንቦት 28 ቀን 2000 ዓ.ም. June 5, 2008)፦ ከ9 ወራት በላይ በውጭ ሀገር የነበሩት ኢንጂንየር ኃይሉ ሻውል አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡ መሆናቸውንና አብረዋቸው ይሰሩ የነበሩ አመራሮችንም መተቸታቸውን የአዲስ አበባ ምንጮቻችን ገለጹ።
ኢንጂንየሩ ለግማሽ ሰዓታት ያህል ንግግር ያደረጉ ሲሆን፣ ጥቂት አፈንጋጮች ቢወጡም ፓርቲያቸው የተወሰደበትን ስም ለማስመለስ ክስ መመስረቱን የገለጹ ሲሆን፤ ደጋፊዎቻቸው ከሆኑ ጋዜጠኞችና እንዲሁም ነፃ ሆነው ከተጋበዙ ጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ሰጥተዋል።
እነ ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ፣ እነዶ/ር ያዕቆብ፣ እነዶ/ር ብርሃኑ ነጋና እነ ወይዘሪት ብርቱካንንና ሌሎችም ታላላቅ የህዝብ ድጋፍ ያላቸው ግለሰቦችን አፈንጋጭ ብለው ከመጥራት ተከፋፍለናል ወይንም ተለያይተናል ቢሉ አይሻልም ወይ? ተብለው ለተጠየቁት ጥያቄ ሲመልሱ እነኝህ የተጠሩት ሁሉ የዶ/ሮች ብዛት ናቸው። እውቀት ዲግሪ በጨበጠ አይደለም በሥራ ነው የሚለካው የፓለቲካ ሥራ በየጋዜጣው ጥሩንባ በመንፋት አይደለም ሲሉ መልሰዋል።
"ቅንጅት በአሁኑ ሰዓት ሰባት ቦታ ተከፋፍሏል፤ እርሶ ደግሞ የዚህ ድርጅት መሪ ነበሩ፤ ለዚህ ሁሉ ክፍፍል የእርስዎ የአመራር ድክመት አይደለም?" ተብለው ሲጠየቁም፤ "እኔ ቅንጅት ሰባት ቦታ መከፈሉን አላውቅም ምናልባት እኔ እስር ቤት ተቀብሬ አልሰማሁ ይሆናል። ድክመት ኖሮብኝ ይሆናል ዲሲፕሊን የሌለው ፓርቲ ደግሞ ለመምራት አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። የኔን የአመራር ችሎታ ለመናገር የኢትዮጵያ ባህል ስለማይፈቅድ ጓደኞቼ ይመረምሩታል" ካሉ በኋላ፤ አቶ አባይነህ ለጥያቄው መልስ ሲሰጡ የሳቸውን የአመራር ችሎታ ሌሎቹም የሚመሰክሩት መሆኑን ሲያስረዱ "ውጭ ሀገር ብዙ ገንዘብ ተሰብስቧል ይህ ገንዘብ ሲሰበሰብ ኢንጂንየር ኃይሉ ይመጣሉ እየተባለ ነው። ይህ ራሱ የሳቸውን የአመራር ችሎታ ያሳያል" ብለዋል።
ኢንጂንየሩ ስለ አዲሱ የአንድነት ፓርቲ ተጠይቀው ሲመልሱም "የተወሰኑ አፈንጋጮች በራሳቸው መንገድ ተሰባስበው 1500 ፊርማ አሰባስበው እንደአዲስ የሚመሰርቱት ፓርቲ ነው" ሲሉ የመለሱ ሲሆን፤ በቅርቡ የተመሰረተውን ግንቦት ሰባት ንቅናቄንም እነሱ በሠላማዊ ትግል ምን ሰርተው፣ ምን ችግር አጋጥሟቸው፣ ምን ውጤት አይተው ነው የትግል ስልት የሚቀይሩት? ከሀገር መውጣቱስ ለምን አስፈለገ? ሲሉ ተችተዋል።



