የጋዜጣና የመጽሔት ፈቃድ መስጠት ተቋረጠ
አዲሱ ሕግ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እስኪወጣ እየተጠበቀ ነው
Ethiopia Zare (ቅዳሜ መስከረም ፲ (10) ቀን ፳፻፩ (2001) ዓ.ም. September 20, 2008)፦ በማስታወቂያ ሚኒስቴር የፕሬስ ፈቃድና የሚዲያ ግንኙነት አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ይሰጥ የነበረውን የፕሬስ ሥራ የብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ አዲሱ ዐዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እስኪወጣ ድረስ መስጠት አቆመ።
ፈቃድ ጠይቀው እንዲጠብቁ የተነገራቸው አንዳንድ ባለጉዳዮች አዲሱ ሕግ ታትሞ በነጋሪት ጋዜጣ እስኪወጣ ሥራው መቋረጥ እንዳልነበረበት ሲገልጹ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በበኩሉ በአዲሱ ዐዋጅ መሠረት ነባሮቹ ድርጅቶች እንደገና መመዝገብ ስለሚገባቸው፣ ከምልልሱ በአንድ ወጥ አሠራር ለመሥራት ብሎ እንደሆነ ይገልፃል።
ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር በመሄድ የአዲሱን ዐዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ መውጣትን እንዲጠባበቁ የተነገራቸው አስተያየት ሰጪዎች፣ “አዲሱ ዐዋጅ ፀድቆና በዐዋጁ ላይ ይህ ዐዋጅ በነጋሪት ጋዜጣ ላይ ታትሞ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ተግባራዊ” ይሆናል በሚል ከተፃፈበት በኋላ፣ ዐዋጁ ፀድቆ ተግባራዊ እስከሚሆን ባለው ሕግ ይሠራል እንጂ ሥራ እንዲቆም መደረግ የለበትም” ይላሉ።
“ነገር ግን ማስታወቂያ ሚኒስቴር በምን ምክንያት እንደሆነ ባልታወቀ ሁኔታ ዐዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ የሚወጣበትን ቀን እንድንጠባበቅ አሳስቦ ፈቃድ ሊሰጠን አልቻለም” ሲሉ አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
በማስታወቂያ ሚኒስቴር የመንግሥት ኢንፎርሜሽንና ሚዲያ ግንኙነት ጊዜያዊ ኃላፊ አቶ ዘመድኩን ተክሌ ስለጉዳዩ ተጠይቀው፣ አዲሱ የመረጃ ነፃነትና የሚዲያ ሕግ በፕሬስ ፈቃድ አወሳሰድ የምዝገባ ሕግ ላይ አዳዲስ አንቀፆችን መደንገጉን ገልጸው፣ ይኼ ሕግ ደግሞ ነባሮቹንም እንደ አዲስ እንዲመዘገቡ የሚያዝ መሆኑን አስረድተዋል።
አዲሱ ሕግ በነጋሪት ጋዜጣ የሚወጣበት ቀን በትክክል ባለመታወቁ፣ ፈቃድ በተሰጠባቸው አንድ ቀን ልዩነት እንኳ ቢፀድቅ ደንበኞች እንደገና የሚወዛገቡበት ኺደት የማይቀር መሆኑን አብራርተዋል።
በተጨማሪም ሕጉ በነጋሪት ጋዜጣ ላይ በአጭር ጊዜ ይወጣል የሚል እምነት ስለነበራቸው፣ እስከዛው በአዲሱ አሠራር ለመሥራት ራሳቸውን በማዘጋጀት ላይ እንደነበሩ አስረድተዋል።
ዞሮ ዞሮ አንዴውኑ በአዲሱ ዐዋጅ ተመዝግቦ ፈቃድ ማግኘት ከተጨማሪ ጊዜና ወጪ እንደሚያስቀር ጠቁመው አሁንም ቢሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ዐዋጁ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ይወጣል የሚል እምነት እንዳላቸው አስረድተዋል።
ማስታወቂያ ሚኒስቴር አዲሱ ረቂቅ ዐዋጅ ከፀደቀበት አንስቶ ለአዳዲስ ተመዝጋቢዎች ፈቃድ መስጠት ማቋረጡ ታውቋል።



